Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ የሰለጠኑ ሰርጎ ገቦችን አካቶ በምርኮኛ ስም ለማስገባት አሲሯል ተባለ

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ ሰሞኑንን ከአራት ሺህ በላይ ምርኮኞችን እንደሚለቅ ማስታወቁን ተከትሎ የቀይ መስቀል የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ማስታወቁን ቢቢሲ ማስታወቁ ይታወሳል። ቀይ መስቀል ” የማውቀው ነገር የለም” ሲል በጥድፊያ ምላሽ የሰጠበት የምርኮኞች መመለስ ጉዳይ ” የሰለጠኑ ሰርጎ ገቦችን ቀላቅሎ ለማስገባት ነው” ሲል መንግስት ጉዳዩን በመረጃ እንደደረሰበት አመልክቷል። የመንግስት መግለጫ ለታች እንዳለ ይነበባል።

በሐሰተኛ መረጃ እና ፕሮፖጋንዳ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ቦታ የለውም! – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት!

በሐሰተኛ መረጃ እና ፕሮፖጋንዳ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ቦታ እንደሌለው መንግሥት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ትክክለኛ ማንነቱን የዓለም ህዘብ እየተመለከተው መምጣቱንና በሐሰት ፕሮፖጋንዳ አሰልፎት የነበረው ድጋፍም መቀዛቀዙን ተከትሎ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ልብ እገዛበታለሁ ያለውን የምርኮኞችን መፈታት አጀንዳ ለማድረግ እየሞከረ ነው።

የወራሪነት፤ የአጥፊነትና የሃገር አፍራሽ ትክክለኛ ገጽታውን ለመሸፈንና ሰላም ፈላጊ መስሎ ለመቅረብ የሚያደርገው መፍጨርጨር አንዱ መገለጫ ይህ ምርኮኞችን ለቀቅኩ የሚለው የሐሰት ትርክቱ ነው።

የሽብር ቡድኑ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር ከዚህም በፊት የሐሰት መረጃዎችን በማቀነባበርና ተባባሪ ሃይሎችን እያሰለፈ የሴራው አካል ሲያደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

የህወሃት የሽብር ቡድን የአማራና አፋር አካባቢዎቸን በሃይል ወረራ ስር አደርጎ በቆየባቸው ወቅቶች በግዳጅ ይዞ ኢሰብአዊ ተግባራትን ሲፈጽምባቸው የነበሩ ሰዎችንና ለራሱ ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ለማዋል ምርኮኛ በማለት የሃገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማጭበርበር እየሞከረ ነው።

መንግሥት ጉዳዩን አስመልክቶ እያደረገ ባለው ማጣራት በሽብር ቡድኑ ምርኮኞች ናቸው ተብለው የተለቀቁት አብዛኞቹ ዜጎች የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ በወጣበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ታግተው የቀሩ የሰራዊቱ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል ከልዩ ልዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ለስራ ትግራይ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲቪል ነዋሪዎችን አግቶ የቆየው የሽብር ቡድኑ፤ አሁን የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ባለው የፕሮፖጋንዳ ድራማ የመከላከያንና የተለያዩ ጸጥታ ሃይሎችን መለዮ በማልበስ በምርኮኛ ስም አሰልፏቸዋል።

የህወሃት ሽብር ቡድን ከሰሞኑ የጦርነት ክተት እያወጀና በይፋም እየተዘጋጀ መሆኑን ማስታወቁን ተከትሎ ያለችውን እንጥፍጣፊ ስንቅ ወደ ጦርነት ለማዞርና ለዳግም ጥፋት ራሱን እያዘጋጀ ለመሆኑ የአሁኑ ድርጊቱ ሁነኛ ማሳያ ነው።

የዚህ እኩይ ሽብር ቡድን ተባባሪ የሆኑና በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ እንደ ሸኔና ሌሎችም ታጣቂ ጽንፈኛ ቡድኖች የዚህ ፕሮፖጋንዳ ተባባሪዎች ናቸው።

የህወሃት የሽብር ቡድን ከእነዚህ ዕንፈኛ ቡድኖች አባላትን በመመልመልና በማሰባሰብ ከሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በጋራ ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ሰርጎ ገብ ሃይሎችንም በምርኮኛ ስም አደራጅቶ የእኩይ ተልእኮው ማስፈጸሚያና መረጃ መቀበያ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመንግሥት በኩል የተደረገው ማጣራት አመልክቷል።

መላው ህዝብም ከዚህ ቀደም በሽብር ቡድኑ የሚነዙትን ሐሰተኛ ወሬዎች አላማና የህወሃትን የአጥፊነት ተልዕኮ በማስታወስ አሁንም የሚያሰራጫቸው ወሬዎች የጥፋት ተልእኮውን ለማስፈጸም የሚጠቀምባቸው መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት!

Exit mobile version