Site icon ETHIO12.COM

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2015 በጀት 786 ነጥብ 61 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ወሰነ


– ከ2014 ጋር ሲነጻጸር የ111 ነጥብ 94 ቢሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ9ኛ መደበኛ ስብሰባው የ2015 በጀት ብር 786 ነጥብ 61 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው የፌዴራል መንግስት በጀት ላይ ውሳኔ ያሳለፈው፡፡

የፌዴራል መንግስት የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ዝግጅት በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም አኳያ፣ የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳትና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን መልሶ ከማቋቋም፣ ቀጣይ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና ዓላማዎችን ማሳካት ማእከል በማድረጋ እንዲሁም የ2015-2019 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፉን መሰረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ለ2015 በጀት ዓመት ለመደበኛ ወጪ ብር 347.12 ቢሊዮን፣ ለካፒታል ወጪ ብር 218.11 ቢሊዮን እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ ብር 209.38 ቢሊዮን እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 12.0 ቢሊዮን የተያዘ ሲሆን አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት የ2015 በጀት ብር 786.61 ቢሊዮን ሆኖ ቀርቧል፡፡

ከ2014 በጀት ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር የብር 111.94 ቢሊዮን ወይም የ16.59 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበለት የፌዴራል መንግሥት የ2015 በጀት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

Exit mobile version