Site icon ETHIO12.COM

የፀጥታ ስጋት ዝርፊያና ሌብነት በትግራይ “ከጦርነቱ በላይ የከበደን ዘረፋ ሆኗል”

ግንቦት 2014 ዓ.ም በተደረገ አንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በክልሉ ከደኅንነትና ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ያለው ስጋት ትክክል እንደሆነ ተናግረዋል።

BBC Amharic

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በተለይ ትላልቅ በሚባሉት ከተሞች ውስጥ ከባድ የፀጥታ ስጋት አንዣቦ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ይገልፃሉ።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በርካታ ወጣቶች መሳርያ በመታጠቃቸው ነዋሪዎች ስጋት ላይ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

“ብዙ ነገር ይሰማል። ከሁሉ የከፋው ግን በየሰፈሩ የተቧደኑ ወጣቶች ‘አለው’ ብለው የጠረጠሩት ግን ምንም የሌለውን ሰው ሳይቀር አደጋ እያደረሱበት ነው” ይላል ዳንኤል።

በተለይ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የትግራይ ኃይሎች በድጋሚ መቀለ ሲገቡ “እነዚህን ሁሉ ታጣቂዎች እንዴት መቆጣጠር ይቻል ይሆን?” የሚል ስጋት በርካቶች ያነሱት ጉዳይ ነበር። 

በወቅቱ ክልሉ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ ከነትጥቃቸው የሚታዩ ወጣቶች የስጋቱ ምንጭ እንደነበሩ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በበርካታ የትግራይ ከተሞች በተለይ ደግሞ በመቀለ የሚታዩ የሌብነትና የዘረፋ ወንጀሎች በርካታዎችን ያስጨነቀ ጉዳይ ሆኗል። በከተማዋ ውስጥ ዘረፋና ለዘረፋ ሲባል አስከ ግድያ የሚደርሱ ወንጀሎች እየተፈፀሙ እንደሆነ ይሰማል።

“ከሁሉም በፊት የከዳን እሱ [ፖሊስ] ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ ታገሉ ብለናቸው ነበር። ግን ከብልጽግና ጋር የተሰለፈው እሱ ነው። በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን እንደ ድርጅት ከድቶናል። [ፖሊስ] የትግራይን ሕዝብ ክዶታል” የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

መቀለ ከተማ ውስጥ በንግድ ሥራ የምትተዳደረውና ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገች ነዋሪ፣ “ሁኔታዎች በጣም ከባድ ሆነዋል። ወጥቶ መግባት አስፈሪ ሆኗል። የመንገድ ላይ ንጥቂያ፣ በሥራ ቦታ ስርቆት እንዲሁም ዘረፋ ያጋጥማል። እኔ ባለሁበት ቦታ ብዙ ሱቆች ይሰረቃሉ። ይህንን በመስጋት እኔም ጥበቃዎች ሱቄን እንዲጠብቁ እያደረግሁ ነው” ትላለች።

ይህች የከተማዋ ነዋሪ እንደምትለው በድፍረት የሚመጡ ዘራፊዎችና ሌቦች የሚፈልጉትን ነገር ያለምንም ፍርሃት ፈጽመው ነው የሚሄዱት።

“ሱቅ ውስጥ ገብተው የሚፈልጉትን ነገር አንስተው ይሄዳሉ፤ አንዳንድ ጊዜም ሙሉ ሸቀጦችን አንስተው የሚሄዱበት አጋጣሚዎችም አሉ። ብዙ የሚያሳዝን ነገር ነው የሚሰማው።”

ዳንኤል የሚባል የከተማዋ ነዋሪ በበኩሉ የደኅንነትና የፀጥታ ስጋቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሆነ ይናገራል።

ሰዎች በስጋትና በፍርሃት የተወጠሩበት ሁኔታ እንደተፈጠረ በመጠቆም “ብዙ ሰቀቀን ተከስቷል፤ ሰዎች ማምሸት አይችሉም። የሚያመሽ ሰው ሌቦች ሊያገኙት እንደሚችሉ ስለሚያስብ እንቅስቃሴ ተገድቧል” ሲል ያለውን ሁኔታ ይገልጻል።

ይህንንም በመፍራት ዳንኤልም ሆነ በቅርብ የሚያውቃቸው ጓደኞቹና የሥራ ባልደረቦቹ ዘወትር በጊዜ ወደ የቤታቸው ከመግባት በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ይናገራል። 

ባለው የወንጀል ድርጊት ምክንያት በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ ሰዎች ከደጃፋቸው ላይ ጭምር በሌቦችና በዘራፊዎች የሚገደሉበት አሳዛኝ ሁኔታ እንዳለ ነዋሪዎች

“ብዙ ነገር ይሰማል። ከሁሉ የከፋው ግን በየሰፈሩ የተቧደኑ ወጣቶች ‘አለው’ ብለው የጠረጠሩት ግን ምንም የሌለውን ሰው ሳይቀር አደጋ እያደረሱበት ነው” ይላል ዳንኤል።

ጨምሮም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ነገሮችን ከሰዎች እጅ ላይ ለመዝረፍ ሲባል ሕይወት የሚያጠፋበት ሁኔታ በከተማዋ ውስጥ እየታየ፣ እየተሰማ ነው። 

ሻይና ቡና በመሸጥ የምትተዳደረው ሰምሃል (ለደኅንቷ ሲባል ስሟ የተቀየረ) በበኩሏ “ደብረዳሞ” በመባል በሚታወቀው አካባቢ በተደጋጋሚ ሰዎች ተገድለዋል የሚል ወሬ እንደምትሰማ ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ወንጀል የሰሩ ሰዎች ተይዘው ወደ ፀጥታ አካላት ከተወሰዱ በኋላ ሳይቆዩ ይለቀቃሉ። አንዳችም የሚመጣ ለውጥ የለም። ዛሬ ይታሰሩና ነገ ይለቀቃሉ። ምስክሮች ቀርበው እንኳን ቅጣት የለም። እዚህ ከተማ ውስጥ ከጦርነቱ በላይ የከበደን ዘረፋ ሆኗል”

“ሁኔታው በጣም ከፍቷል። የማትገምታቸው ሰዎች ሳይቀር ሌብነትና ዘረፋ ላይ ተሰማርተው ታያለህ። ለዚህ ድርጊትም ሁኔታዎችን አጥንተው የሚመጡ ይመስለኛል” በማለት እሷም የዘረፋ ሰለባ የሆነችበት አጋጣሚ እንዳለ ትገልፃለች።

ስርቆትና ዘረፋው ቀንም ሆነ ማታ ሰው እያየ እንደሚፈጸም ጠቁማ “በእጅ ላይ ያለን ነገር መስጠት ያልፈቀደ ሰውን በስለት ይወጋሉ። ቢኖርህም ባይኖርህም ሕይወትህን እስከማጥፋት ይደርሳሉ። እኛ አካባቢ የሞቱና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ብዙ ሰዎች አሉ” ትላለች።

በዚህ በአሳሳቢ ሁኔታ እየተፈጸመ ባለው የወንጀል ድርጊት ምክንያት በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ ሰዎች ከደጃፋቸው ላይ ጭምር በሌቦችና በዘራፊዎች የሚገደሉበት አሳዛኝ ሁኔታ እንዳለ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ዛሬ ይታሰርና ነገ ይለቀቃል”

ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ ወደ አማራና አፋር ክልል በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ሺዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሚልዮኖች ተፈናቅለው ከባድ የሰብአዊ ቀውስ አጋጥሟቸዋል።

በአሁኑ ወቅት ትግራይ በቂ እርዳታ እየገባ አለመሆኑ እና መሠረታዊ ሸቀጦች ስለማይቀርቡ ሕዝቡ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሕይወት እየመራ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል።

በጦርነት እጅግ የተጎዳቸው ትግራይ የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች ያለ ደሞዝ ወራት ተቆጥረዋል፣ ነጋዴዎች የሚሸጡት ሸቀጥ አጥተው ሱቆቻቸው ባዶ የሆነበትና የቀን ሠራተኞች ሥራ ፈትተው እርዳታ የሚጠብቁበት ሁኔታ መፈጠሩን ቢቢሲ በተለያየ ወቅት ያነጋገራቸው ሰዎች ይመሰክራሉ።

በትግራይ ከተሞች የተንሰራፋው ሥራ አጥነት እና መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ባልቻሉ ወጣቶች ምክንያት የወንጀል ድርጊት እየተስፋፋ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ይገልፃሉ።

የመቀለ ነዋሪዋ ሰምሃል የተፈጠረው የደኅንነትና የፀጥታ ስጋት ላይ ኃላፊነት መውሰድ ያለበት ክልሉን እያስተዳደረ ያለው አካል ነው ትላለች።

“ወንጀል የሰሩ ሰዎች ተይዘው ወደ ፀጥታ አካላት ከተወሰዱ በኋላ ሳይቆዩ ይለቀቃሉ። አንዳችም የሚመጣ ለውጥ የለም። ዛሬ ይታሰሩና ነገ ይለቀቃሉ። ምስክሮች ቀርበው እንኳን ቅጣት የለም። እዚህ ከተማ ውስጥ ከጦርነቱ በላይ የከበደን ዘረፋ ሆኗል” ስትል የሁኔታውን ክብደት ለቢቢሲ ታስረዳለች።

ዘረፋው “በቤትህ ደጃፍና በሥራ ቦታህ ላይ የሚጠብቅህ በመሆኑ ሁኔታው አሳሳቢ ነው” ስትልም ታክላለች።

እየተስፋፋ ባለው ሌብነትና ዝርፊያ ምክንያት ነዋሪዎች በፈቃዳቸው ተሰባስበው አካባቢያቸውን ለመጠበቅ እንደሚሞክሩ የምትናገረው ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገችው ሴት እንደምትለው፣ መሳርያ ስለሌላቸው ስጋቱን በመቅረፍ በኩል ብዙ ለውጥ አላማጣም ትላለች። 

ዳንኤልም አልፎ አልፎ ከምሽቱ 04 ሰዓት እስከ ንጋት 10 ሰዓት ድረስ ከኅብረተሰቡ የተውጣጡ ሰዎች አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ እየተደረገ ቢሆንም ውጤታማ እንዳልሆነ ይናገራል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እነዚህ ነዋሪዎች የትግራይ ሕዝብ በጦርነት ስጋት ውስጥ በቂ እርዳታ ሳያገኝ መኖሩ ሳያንሰው “በየአካባቢው በሚገኙ ወጣቶች በሚፈጸሙ ዝርፊያዎች ምክንያት ተጨማሪ ስጋት ሲፈጥር ማየት እጅግ የሚያሳዝን” እንደሆነ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የትግራይ የፍትሕ አካላት ምን ይላሉ?

ጦርነቱ መቀስቀሱን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ክልሉ ሲቆጣጠር ከሥራ ውጪ የነበረውን የክልሉን ፖሊስ መልሶ ለማዋቀር በጊዜያዊ መስተዳደሩ በኩል ጥረቶች የነበሩ ሲሆን፣ የህወሓት ኃይሎች መቀለን ሲቆጣጠሩ ሂደቱ መቋረጡ ይታወሳል። 

ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ወዲህ አብዛኛውን የትግራይ ክልል የተቆጣጠረው ህወሓት የፖሊስ ኃይሉን መልሶ ባለማደራጀቱና በክልሉ ውስጥ ባለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት የወንጀል ድርጊቶች ተስፋፍተው ለነዋሪዎች ስጋት ሆነዋል።   

የትግራይ ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው የትግራይ የፍትሕና የፀጥታ አካላትም በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች የደኅንነት ስጋቱ እየጨመረ መምጣቱን ያረጋግጣሉ። 

ፖሊስንና ሚሊሻን ያካተተ የፀጥታ አደረጃጀት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን እንደፈረሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠርና ወንጀልን ለመከላከል የክልሉ መንግሥት በቅርቡ አዲስ የወንጀል መቅጫ ሕግ አርቅቆ ማጽደቁን የትግራይ ቴሌቪዥን የትግራይ የፍትሕና የፀጥታ አካላትን ጠቅሶ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።

… የትግራይ ሕዝብ በጦርነት ስጋት ውስጥ በቂ እርዳታ ሳያገኝ መኖሩ ሳያንሰው “በየአካባቢው በሚገኙ ወጣቶች በሚፈጸሙ ዝርፊያዎች ምክንያት ተጨማሪ ስጋት ሲፈጥር ማየት እጅግ የሚያሳዝን”

አዲሱ ሕግ “ዘረፋና ከባድ ሌብነት በመፈፀም የተጠርጠረ ወይ የተያዘ የዋስትና መብት አይሰጠውም” ይላል። 

“እንደቢላ፣ ገጀራ፣ መጥረቢያ የመሳሰሉ አደገኛ መሳርያዎችን ይዞ ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰ የሞት ፍርድ ወይም የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቀዋል” ሲል አዲሱ ሕግ ያብራራል።

ቢቢሲ በትግራይ ያሉ የፍትሕና የፀጥታ አካላትን አግኝቶ ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

ይህ ሕግ ተሻሽሎ በአዲስ መልክ ቢወጣም ግን ተግባራዊነቱ ላይ ክፍተት እንዳለ ነዋሪዎች እንዲሁም የትግራይ ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው ባለሥልጣናት ያስረዳሉ። 

ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያቱ ፈፃሚዎቹ የፍትሕና የፀጥታ አካላት በሚገባ አለመደራጀታቸው መሆኑ ተገልጿል።

የህወሓት ሊቀመንበር ስለ ፀጥታ ችግሩ ምን አሉ?

የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚገኙበት የትግራይ አመራሮች ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከነዋሪዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተው ነበር።

በእነዚህ ውይይቶች ወቅት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የፀጥታና የደኅንነት ስጋትን የሚመለከት ሆኖ፣ በርካቶች የሰጡት ሃሳብም “ለደኅንነታችን የምንሰጋበት ደረጃ ላይ ደርሰናል” የሚል ነበር።

ስርቆት፣ ዘረፋና ንጥቂያ ከተጠቀሱት ወንጀሎች መካከል ናቸው።

ግንቦት 2014 ዓ.ም በተደረገ አንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በክልሉ ከደኅንነትና ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ያለው ስጋት ትክክል እንደሆነ ተናግረዋል።

ሆኖም ሕዝቡ በምሬት እያቀረበ ያለውን ጥያቄ ለመመለስ ሲባል ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የነበረውን ፖሊስ መመለስ እንደማይቻል ገልፀዋል።

“ከሁሉም በፊት የከዳን እሱ [ፖሊስ] ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ ታገሉ ብለናቸው ነበር። ግን ከብልጽግና ጋር የተሰለፈው እሱ ነው። በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን እንደ ድርጅት ከድቶናል። [ፖሊስ] የትግራይን ሕዝብ ክዶታል” ብለዋል።

በዚህ ምክንያት በመላው ትግራይ ያለው የፖሊስ አደረጃጀት የማፍረስ እርምጃ እንደተወሰደ በመጠቆም “ነባሩን መልሰን አናስገባውም። ከታች እስከ ላይ ያለው በአዲስ ፖሊስ እንተካዋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም “ፀጥታውን ሁኔታ በተደራጀ ሁኔታ ለመመለስ ሥራ ጀምረናል። . . . በአሁኑ ወቅት ከግንባር ነው እያመጣን ያለነው። ስለዚህ ሥራው እየተጀመረ ነው። ዝግጅት ጨርሰናል” በማለት ጣቢያ ድረስ በመውረድ ፖሊስ እንደሚደራጅ ጠቁመዋል።

Exit mobile version