Site icon ETHIO12.COM

“የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው” ይልቃል ከፋለ

የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው፤
የሕግ ማስከበር ዘመቻው የአማራን ህዝብ አንድነት ለማጠናከር ያለመ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ.ር) ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየመከሩ ነው።

የጎንደር ከተማን ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ መሰራት ስላለባቸው ጉዳዮች የጋራ አቋም ለመያዝ ያለመ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ያለው።

ጎንደር የስልጣኔያችን ምልክት፤ የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሐብቶች መናገሻ የኾነች የዓለም መዳረሻ ከተማ መኾኗን ያነሱት ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ገጽታዋን ለማጠልሸት በሐይማኖትና በብሔር ሽፋን ግጭት እንዲቀሰቀስ የሚሰሩ ሐይሎች መበራከታቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡ በጎንደር ከተማ የተከሰተው ግጭትም የሕዝቡን ማኅበራዊ እሴት የማይመጥን አሳዛኝ ድርጊት ነው፤ ማንም ይሁን ማን ጥፋተኞች መወገዝ አለባቸው፤ አጥፊዎች ለህግ ቀርበው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በተደረገው ጥረት ሕዝቡ ያሳየው ትብብርም የሚመሰገን ነው ብለዋል።

በአካባቢው በአማራና በቅማንት ሕዝብ መካከል ግጭት ተከስቶ ሕዝቡ እንዲደሳቆል የሚያደርጉትንና ለዘመናት በአብሮነት የኖረውን የክርስትናና እስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ለመለያዬት በተለየዩ ጊዜያት ግጭት ቀስቅሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ።

የሰው ታላቅነት የሚመዘነው ከውድቀት መነሳት በመቻል በመኾኑ ከዚህ በፊት የተፈጠሩትን ግጭቶች ምክንያታቸውን በመለየት ለመፍትሔዎቻቸውና ለቀጣይ አብሮነታችን የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይኖርብናል ነው ያሉት።

“አንዳችን ለአንዳችን አስፈላጊ መሆናችንን በመገንዘብ ሐይማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭት የሚቀሰቅሱ አካላትን አጋልጠን ለህግ ማቅረብ አለብን፤ ከዚህ በኋላ የጎንደርን ሰላም ለማናጋት የሚሰሩትን አምርረን ልንታገላቸው ይገባል ” በማለት ነው ያሳሰቡት ዶክተር ይልቃል።

በቅርቡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ የነበሩ ስጋቶችን በመቀነስ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ርእሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የህግ ማስከበር ዘመቻው የአማራ ሕዝብን አንድነት ለማጠናከር ያለመ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው ብለዋል።

አንድ ስንኾንና ስንጠናከር ሌሎች ያደምጡናል፤ ከተፈረካከስን ግን ተደማጭነታችን ይቀንሳል ሲሉም ለነዋሪዎች የአንድነት ጥሪ አቅርበዋል። (አሚኮ)

Exit mobile version