Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ ከብልጽግና ጋር አብራችኋል የተባሉ ጋዜጠኞች ታሰሩ

በትግራይ ክልል፣ መቀለ ከተማ ውስጥ አምስት የትግራይ ቲቪ ጋዜጠኞች ለሳምንታት በእስር ላይ መሆናቸውን ባልደረቦቻቸው ለቢቢሲ ተናገሩ። በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለፁት ጋዜጠኞች ክስ ያልተመሰረተባቸው ሲሆን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውም ተገልጿል።

ከታሰሩት ጋዜጠኞች አራቱ በእስር ላይ ለሁለት ሳምንታት ያህል ቢቆዩም እስካሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን፣ አንደኛው ጋዜጠኛ ደግሞ ለ6ኛ ቀን በእስር ላይ ይገኛል።

አምስቱ የትግራይ ቲቪ ባልደረቦች በመቀለ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከብልጽግና ጋር አብራችኋል በሚል መሆኑን ባልደረቦቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል። እነዚሁ የቢቢሲ ምንጮች አንድ የሂሳብ ባለሙያ እና አምስት የትግራይ ቲቪ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን አረጋግጠዋል።

የታሰሩት ጋዜጠኞች ምስግና ሥዩም፣ ሐበን ሐለፎም፣ ኃይለ ሚካኤል ገሠሠ፣ ተሾመ ጠማለው እና ዳዊት መኮንን መሆናቸውንም ምንጮቹ ተናግረዋል። ሌላው በቁጥጥር ስር የዋለው የፋይናንስ ባለሙያ ክፍሎም አፅብሃ እንደሚባልም ገልጸዋል።

የመቀለ ከተማ ዐቃቢ ሕግ አዲስ ገብረ ሥላሴ፣”ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው ነው። ጉዳያቸውም በምርመራ ላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ጋዜጠኞቹ የኢትዮጵያ ጦር ትግራይን በተቆጣጠረበት ወቅት ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ተባብራችኋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባልደረቦቻቸው ገልጸዋል።

ቢቢሲ የትግራይ ክልል ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑትን ወይዘሮ ሊያ ካሳን በማግኘት ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል ምስግና ሥዩም እና ተሾመ ጠማለው ከቴሌቭዥን ጣቢያው ጋር ሲሰሩ የቆዩ ሲሆኑ፣ አቶ ሀበን ሀለፎም፣ ኃይለሚካኤል ገሠሠ እና ዳዊት መኮንን ቀደም ሲል ‘በግምገማ’ እገዳ ተጥሎባቸው ነበር።

ከታሰሩትጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ሀበን ሀለፎ በትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር ሲቋቋም ከአንድ ሳምንት በላይ ታስሯል። ከኅዳር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የቴሌቭዥን ጣቢያው ዳግም ሠራተኞቹ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲገኙ ጥሪ አቅርቦ ሥራውን ቀጥሏል።

Exit mobile version