Site icon ETHIO12.COM

ታዳጊ ሀገራት ከሩሲያ ማዳበሪያ እንዳይሸምቱ የአውሮፓ ህብረት ፕሮፖዛል

አውሮፓ ህብረት ታዳጊ ሀገራት ከሩሲያ የሚያደርጉትን ግዢ በማገድ ግንኙነታቸውን ወደ ሌሎች ሀገራት ያደርጉ ዘንድ በህብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝደንና በአጋሮቹ ያዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ይፋ የሆነው ባሳለፍነው ሳምንት ነው። በፈረንጆቹ ሰኔ 15 የተዘጋጀው ረቂቁ ታዳጊ ሀገራት የራሳቸውን የመሬት ማዳበሪያ የሚያመርቱበትን የመፍትሄ አማራጭ ማመቻቸት የሚል ግብ የተቀመጠለት ነው በጊዜ ሂደት ከህብረቱ የተሰጠው ጥቆማ እንደሚያሳየው።
ከሳምንት በፊት በተካሄደው የአውሮፓ ህብረት ጉባኤ ወቅት ረቂቅ ህጉ ለውውይት መቅረብ ቢችልም የህብረቱ አባላት ከመግባባት ለመድረስ አልቻሉም ነበር። ይህን ተከትሎ ነበር የህብረቱ ኮሚሽን ረቂቅ ህጉን በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ ያወጣው። በመግለጫው “ታዳጊ ሀገራት የራሳቸው የመሬት ማዳበሪያ ማምረት እንዲችሉ የተረቀቀው ሀሳብ ከአረንጓዴ ልማት ጅምሮች ጋር የማይጣጣም ነው።” የሚል ነበር።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ሰኔ 23 እና 24 በተደረገው የአውሮፓ ህብረት ስብሰባ ወቅት የህብረቱ ስራ አስፈፃሚዎች “ታዳጊ ሀገራት የራሳቸውን የመሬት ማዳበሪያ እንዲያመርቱ እንዲሁም አማራጮችን ማግኘት እንዲችሉ(ከሩሲያ የሚፈፅሙትን ግዢ እንዲያቆሙ) የሚያስችል አፈፃፀም እንዲያዘጋጅ” ነበር ጥሪ የቀረበው።
ይሁን እንጂ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የቀረበው የረቂቅ ህግ ድርሳን ተከልሶ ይቀርብ ዘንድ ምላሽ ሰጥቶበታል ብሏል ሮይተርስ። ኮሚሽኑ አክሎም “ታዳጊ ሀገራት የማዳበሪያ አማራጭ የሚያገኙበትን እንዲሁም ውጤታማ የማዳበሪያ አጠቃቀም ዘዴዎች ላይ በሚደረግ ድጋፍ ላይ ያተኮረ የዶጋፍ ማእቀፍ ማዘጋጀት ይኖርብናል። ሀገራቱ የራሳቸው ማዳበሪያ ፋብሪካ ይኑራቸው የሚለው እሳቤ ከህብረቱ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ጋር የሚጣረስ ነው።” ማለቱ ተዘግቧል።

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ከፕሬዝደንት ቪላዲሚር ፑቲን ጋር ስለ ጦርነቱ እና ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሶቺ ከተማ ከወር በፊት ባደረጉት ምክክር “አፍሪካ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖራትም በጦርነቱ ምክንያት ሰለባ ሆናለች” ሲሉ ገልፀው ነበር።
ሩሲያን ጨምሮ የአፍሪካ አጋር የሆኑ ሁሉም ሃገራት የጣሏቸውንና በስንዴ እና በማዳበሪያ ላይ ያነጣጠሩ ማዕቀቦቻቸውን እንዲያነሱም ማኪ ሳል ጨምረው ጠይቀዋል፡፡
በምላሹም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ወደ አፍሪካ ለሚገቡ የስንዴ ምርቶች ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ ቃል መግባታቸውም ነበር የተዘገበው። ፑቲን የስንዴ ምርቶች ወደ አፍሪካ መላካቸውን ለማረጋገጥ ሃገራቸው እንደምትሰራም ነው የገለፁት፡
በተያያዘ ጉዳይ “ሩስያ ላይ የተጣሉ ማእቀቦች የምግብ እና የግብርና ማዳበሪያን አይመለከቱም።” በማለት አውሮፓ ህብረት ያስታወቀው ከማኪ ሳል እና ፑቲን ውይይት ሰሞን ሲሆን የህብረቱ ከፍተኛ ዲፕሎማት ጆሴፍ ቦሬል “በአለም አቀፍ ደረጃ ለተከሰተው የምግብ ቀውስ እና የዋጋ መናር የአውሮፓ ህብረት እና ማእቀቡን ተጠያቂ ማድረግ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረው ነበር።

የማዳበሪያ ግብአት የሆነውን አሞኒያ ለማምረት በርካታ የተፈጥሮ ጋዝ የሚፈልግ ሲሆን፤ ያራ ኢንተርናሽናል አውሮፓ ውስጥ ይህንን ለማምረት በሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ ላይ ጥገኛ መሆኑን ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ሩሲያ 20 በመቶውን የአለም መሬት ማዳበሪያ አቅርቦት ትሸፍናለች። ሩሲያ እና ቻይና በጥምረት የአለምን 45 በመቶ ፎስፌት ያቀርባሉ።
ኢትዮጵያ ለማዳበሪያ ግዢ 27.2 ቢሊዬን ብር(660 ሚሊዮን በላይ ዶላር) ያወጣችው ባለፈው አመት ነበር። ጎረቤት ኬኒያ በተጠቀሰው አመት ለማዳበሪያ ኬሚካልና ዘር ግዢ 578 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች።

Esleman Abay #የዓባይልጅ

Exit mobile version