Site icon ETHIO12.COM

“በቶሌ ቀበሌ በንጹሓን ላይ ጭፍጨፋ የፈጸሙት የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው ”አምነስቲ ኢንተርናሽናል

የሸኔ ታጣቂዎች በቶሌ ቀበሌ በንጹሓን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ነግረውኛል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ታጣቂዎች በንጹሓን ላይ የፈጸሙትን ጭፍጨፋ አስመልክቶ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮዝ ሙቼና ፤ የጥቃቱ ፈጻሚዎች የሸኔ ታጣቂዎች መሆናቸውን ከጥቃት የተረፉ ሰዎች ነግረውኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ 

በቶሌ የተፈፀመው ዘግናኝ ግድያ ሴቶችና ሕጻናት ሕይወታቸውን ያጡበትና የተሰቃዩበት ግድያ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ገዳዮቹ ለሰው ልጅ ሕይወት ምንም ደንታ እንደሌላቸው ያሳዩበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገደሉ ከዓይን ምስክሮችና በሕይወት ከተረፉ ሰዎች መስማታቸውንም ገልጸዋል፡፡

እንደ አምነስቲ ገለጻ፤ በቶሌ ቀበሌ የተፈፀመው ዘግናኝ ግድያ በኦሮሞ ነፃ አውጪ ጦር እጅ የተፈጸመ መሆኑን የአይን እማኞች አረጋግጠውልኛል፡፡ ጥቃቱ እንደተጀመረ የአካባቢው አስተዳደር መረጃው ቢደርሰውም፣ መንገዱ ተዘግቷል በማለት ጸጥታ ኃይል ሳይልክ እንደቀረ አምነስቲ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ ሴቶች እና ሕጻናት ሕይወታቸውን ያጡበት ይህ አሰቃቂ ግድያ ራሱን የቻለ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ መመርመር አለበት ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮዝ ሙቼና ተናግረዋል።

በጭፍጨፋው በብዛት የተገደሉት ሕጻናትና ሴቶች እንደሆኑና አዲስ የተወለዱ ሕጻናት ጭምር እደተገደሉ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በቃለ መጠይቁ የተሳተፉ ሰዎች እንደገለጹት ያለማቋረጥ ግድያ፣ ቤት ማቃጠል እና ዘረፋ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ የሳተላይት ምስል ትንተና ሰኔ 18 ቀን በቶሌ ቀበሌ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ የእሳት ቃጠሎ ተነስቷል የሚለውን አባባል ያረጋግጣል ብሏል አምነስቲ በመግለጫው፡፡

በጥቃቱ ወቅት ጎልማሶች ሥራ ለመሥራት ከቤት ከወጡ በኋላ ነው ያለው የአምነስቲ ገለጻ፤ ከጥቃቱ በፊት የሸኔ አባላት በአካባቢው እንዳሉ የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ከጥቃቱ በፊት በአካባቢው የሚገኙ መንደሮችን ከበው ነበር ብለዋል፡፡ በወቅቱ በመንደሮቹ ውስጥ በብዛት የነበሩት ከአጥቂዎች መሸሽ ያልቻሉ እናቶችና ሕጻናት ናቸው ብሏል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ሰኔ ወር ላይ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በንጹሓን ላይ ጭፍጨፋ ያካሄዱ የሽብር ቡድኖች በተቀናጀ የጸጥታ አካላት በተወሰደ እርምጃ አብዛኞቹን የሽብር ቡድን ተሳታፊዎች መደምሰስ ተችሏል፡፡ ወደ ጫካ የተበታተኑ የሽብር ቡድኑ አባላትም በጸጥታ ኃይሎችና በኅብረተሰቡ ትብብር እየታደኑ ይገኛሉ። በአካባቢው ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች የማረጋጋትና ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መንደራቸው እንዲመለሱ፣ የቆሰሉ እንዲታከሙ፣ ንብረታቸው የወደመባቸው የዕለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ እርዳታ እንዲያገኙ መደረጉንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህንን ጭፍጨፋ የሚያጣራ ቡድን ማዋቀሩ የሚታወስ ነው፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version