Site icon ETHIO12.COM

ማይክ ሐመር በአዲስ አበባ እየመከሩ ነው፤ መንግስት ትህነግ በሰላም ጥረቱ ወላዋይ መሆኑን አስታውቋል

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር አርብ አዲስ አበባ በመግባት ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ተወያዩ።

በቅርቡ የተሾሙት ልዩ መልዕክተኛው ካለፈው ሳምንት ማብቂያ በጀመሩት ጉዟቸው በቀዳሚነት ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና ግብፅ ከተጓዙ በኋላ ነው አዲስ አበባ ያቀኑት።

ልዩ መልዕክተኛው አዲስ አበባ እንደገቡ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ከኦነግ እና ከኦፌኮ ሊቃነ መናብት ጋር ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት ኃላፊነት ከተቀበሉ በኋላ የመጀመሪያ በሆነው ጉዟቸው አርብ ዕለት አዲስ አበባ መግባታቸውን ያመለከተው የአሜሪካ ኤምባሲ፣ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ይገናኛሉ ብሏል።

ልዩ መልዕክተኛው በቀዳሚነት የተነጋገሩት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ስለሚደረገው ጥረት፣ የእርዳታ አቅርቦት እና በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አመልክቷል።  

ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ለተጀመረው የሰላም ጥረት ቁርጠኛ መሆኑን እና ለዚህም ተደራዳሪ ቡድን አቋቁሞ ሥራ መጀመሩን፣ ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መቀጠሉን እና የመብት ጥሰት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል።

አቶ ደመቀ ጨምረውም መንግሥት ለሰላም ንግግር ያለውን ዝግጁነት በሚያሳይበት ጊዜ “በህወሓት በኩል የሚታየው ወላዋይ አቋም በአፍሪካ ኅብረት የሚካሄደውን የሰላም ጥረት ስጋት ላይ የሚጥል ነው” በማለት የተገኙ ውጤቶች ወደኋላ እንዳይመለሱ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቡድኑ ላይ አስፈላጊውን ጫና እንዲያሳርፍ መጠየቃቸውን ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ገልጿል።

ከልዩ መልዕክተኛው ጋር በተደረገው ውይይት ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ከሚያስማማ መፍትሄ ላይ ለመድረስ በመርኅ ላይ የተመሠረተ አቋም እንዳለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ውይይቱን በተመለከተ ከልዩ መልዕክተኛው በኩል የተባለ ነገር ባይኖርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ማይክ ሐመር መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እና በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እያስገኘ ያለውን ውጤት ማድነቃቸውን አመልክቷል።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አርብ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ እንዳመለከተው ሊቀ መንበሩ አቶ ዳውድ፣ ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) መሪ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ጋር በመሆን ከአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር መወያየተቻውን ገልጿል።

አዲስ አበባ በሚገኘው በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል ውስጥ የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ከሌሎች ዲፕሎማቶች ጋር ሆነው ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቹ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ በአጠቃላዩ የአገሪቱ ሰላም፣ በኢኮኖሚ እና በፓርቲዎቹ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ኦነግ በፌስቡክ ገጹ ማስታወቁን ቢቢሲ አመልክቷል።

Exit mobile version