ETHIO12.COM

“መንግሥት ውስጥ የተሸሸገ ሸኔ አለ” ታዬ ደንደአ

የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ የግድያ ማስፈራሪያዎች እንደሚደርሷቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በተለያዩ መድረኮች በሚያነሷቸው ሃሳቦች አነጋገሪ የሆኑት ሚኒስትር ዲኤታው፤ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ አለ ስለሚሉት ‘የማፊያ ቡድን’ እና በግል ስለሚደርሱባቸው ጫናዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ድምጼ ታፍኗል”

አቶ ታዬ በቅርብ በተካሄደው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አስተያየት “እንዳልሰጥ ድምጼ ታፍኗል” ብለው የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ካሰፈሩ በኋላ ጉዳዩ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

አቶ ታዬ በጨፌው [በኦሮሚያ ምክር ቤት] የሆነው ሲያስረዱ፤ አፈ ጉባኤዋ የዕለቱን አጀንዳ ካቀረቡ በኋላ ምክር ቤቱ በሁለት ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ እንዲነጋገር አጀንዳ ለማስያዝ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ይናገራሉ።

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አቶ ታዬ፤ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ከመቼውም ጊዜ በላይ “እየተበላሸ መጥቷል” ስላሉት የክልሉ የደኅንነት ሁኔታ አጀንዳ አድርጎ እንዲወያይበት ማቅረብ ፈልገው እንደነበረ ይገልጻሉ።

ሁለተኛው ማንሳት የፈለጉት ጉዳይ ደግሞ “ከሌብነት ጋር በተያያዘ በክልላችን አስተዳደሩ ተዳክሟል” የሚል መሆኑን ጠቅሰዋል።

“እጄን ሳወጣ ይዩኝ አይዩኝ [አፈ ጉባኤዋ] አላውቅም ዝም ብለው አጀንዳ ወደማጸደቅ ሄዱ። ከዚያ ‘ክብርት አፈ ጉባኤ የማነሳው ሃሳብ አለኝ’ አልኩ” ይላሉ አቶ ታዬ።

“ከዚያ ዕድል እንደመስጠት አሉና እንዳልናገር ደግሞ ማይክሮፎኑን ዘጉብኝ። ትንሽ ቆይተው ‘ዕድሉን መጠቀም አልቻሉም’ አሉ። ‘ዝጉበት፣ ዝጉበት’ የሚል ድምጽ ይሰማ ነበር” በማለት አቶ ታዬ በጨፌው አጋጥሟል ያሉትን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ታዬ አስተያየቴን እንዳልሰጥ የተከለልኩት፤ ምክር ቤቱ በአጀንዳነት የያዛቸው ሪፖርቶች ችግር እንዳሉባቸው ስለሚታወቅ ነው ይላሉ።

ከአንድ ዓመት በፊት የኦሮሚያ የፀጥታ ስጋት በአጭር ወራት ውስጥ ይወገዳል ተብሎ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ስንገናኝ የክልሉ የፀጥታ ችግር ተባብሷል የሚሉት አቶ ታዬ፤ ለዚህ የፀጥታ መደፍረስ ምክንያቱ ምንድን ነው? ተጠያቂውስ ማን ነው? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ምክር ቤቱ እንዲወያይ ቢፈልጉም ዕድሉ እንደተነፈጉ ያስረዳሉ።

“በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የተደራጀ ማፊያ አለ”

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ታዬ፤ በፓርቲው ውስጥ “ሌብነት ላይ የተሰማራ የተደራጀ ማፊያ አለ” ሲሉ ይከስሳሉ። አክለውም “ለዜጎች ክብር የለውም” ያሉት ቡድን በአካል እንጂ በሃሳብ ብልጽግና አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

“ወረቀት ይዞ ብልጽግና ነኝ ሊል ይችላል እንጂ፣ ይህ ሰው አስፈራርቶ አፍኖ የሚወስድ ቡድን ብልጽግና አይደለም። . . . የታገልንለት ወደ ኋላ እንዲመለስ፤ ማፊያ እጅ እንዲገባ እኛ እንፈልግም” ብለዋል።

አቶ ታዬ በንግግራቸው በኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ውስጥ አለ ያሉት የማፊያ ቡድን፣ አባላቱ እነማን እንደሆኑ እንዲሁም “ማፊያ” ያሉት ቡድን ፈጽሟል ስላሉት አሉታዊ ተግባር ያቀረቡት ማስረጃ የለም።

“እዚህ ቡድን ውስጥ ያሉት እነ እከሌ ናቸው ብሎ ለመዘርዘር ጊዜው አሁን አይደለም። ጊዜው ሲደርስ ስማቸውን እንዘረዝራለን” ሲሉ በደፈናው ማለፍን መርጠዋል።

“የደኅንነት ስጋት አለብኝ”

አቶ ታዬ በቅርቡ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው ገልጸው ነበር። “ ‘እንረሽንሃለን…ግንባርህን እንልሃለን’ እያሉ በግልጽ የሚያስፈራሩ አሉ።…ሁሉንም አስፈራርቶ አይሆንም። ሰው መጉዳት፣ ሰው መግደል ይቻላል። ይህ ብዙ ቦታ ሆኗል። ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይም ተፈጽሟል” በማለት ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።

የግል ጠባቂዎቻቸው እንዲነሱ መደረጋቸውን የሚናገሩት ሚኒስትር ዲኤታው፣ ምንም እንኳ የግድያ ዛቻን ጨምሮ ማስፈራሪያ ቢደርስባቸውም፤ “በትግላቸው” እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ።

ቢቢሲ የሚኒስትር ዲኤታ ጠባቂዎች ስለመነሳታቸው ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ማረጋገጥ አልቻለም።  

“… እኛ ከቤት የወጣነው ለነጻነት ነው። ለሕዝብ ነጻነት ታግዬ ብታፈን በተቃራኒ ጎራ ስለታገልኩ ነው። ዋስትናችን ትግላችን ነው” ሲሉም አክለዋል።

አቶ ታዬ ደንደአ

“ለውይይት በሩ ዝግ ነው”

አቶ ታዬ በኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ውስጥ አሉ የሚሏቸው ብልሹ አሰራሮችን በንግግር ለመፍታት መንገዶች ዝግ መሆናቸውን ይናገራሉ።

“በውይይት ውስጣችንን ማየት አለብን። በኦሮሚያ ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ግን ይህ እንዲደረግ አይፈልግም። ለውይይት በሩ ዝግ ነው። እኔ በጣም ብዙ ጊዜ ሞክሪያለሁ። ለዚህ ማስረጃ ማቅረብ እችላለሁ። የሚሰማኝ ግን አጣሁ” ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ደኅንነት ሁኔታ

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታው አሁን በኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ “…ወንድ ልጅ የሚደፈርበት፣ አባ ገዳዎች የሚገደሉበት፣ ሰው ወጥቶ መግባት የማይችልበት፣ እጅግ በጣም አስቀያሚ ነገሮች ያሉበት” ሲሉ ይገልጹታል።

አቶ ታዬ የዜጎች ደኅንነትን ማረጋገጥ ሳይቻል ሰው ወጥቶ መግባት ስጋት ሆኖበት ሳለ፤ “በክልሉ አጠቃላይ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል ሲባል፤ ቀድሞ ምን ታቅዶ ነበር” ያስብላል ይላሉ።

“በክልሉ ከተገነቡት ትምህርት ቤቶች ይልቅ የተቃጠሉት ይበልጣሉ። ሕዝባችን መኖሪያ ቤቱ ተቃጥሎ መሄጃ አጥቷል። በሬው ታርዶበት የሚያርስበት የለውም። ያለው ችግር ተቆጥሮ አያልቅም።”

አቶ ታዬ ለጠቀሷቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች እርሳቸው አባል የሆኑበትን አስተዳደርን ተጠያቂው ያደርጋሉ።

“ከሁሉም በላይ የሕዝብ ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው። …ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ለተከሰተው ችግር ትልቁን ኃላፊነት መውሰድ ያለበት መንግሥት ነው” ብለዋል።

አቶ ታዬ “ክልሉ ገብቶበታል” ላሉት ችግር ከመንግሥት በተጨማሪ ሌሎች ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው አካላት እንዳሉ ይናገራሉ።

“በሰላማዊ መንገድ ከተማ ተገብቶ ከዚያ በኋላ ወደ ጫካ መሄድ አግባብ አይደለም” በማለት በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድንም “የሰላም ፀር” መሆኑን አንስተዋል።

“ሁለት ሸኔ ነው ያለው”

አቶ ታዬ ከዚህ ቀደም በአሮሚያ ክልል ሁለት ሸኔ ነው ያለው ሲሉ ተደምጠው ነበር።

ሚኒስትር ዲኤታው መንግሥት አሸባሪ ሲል የፈረጀው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ “ሌላኛው ሸኔ መንግሥት ውስጥ የተሸሸገው ነው” ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ይሰጣሉ።

“ጫካ ያለው አለ። ሌላኛው ደግሞ መንግሥት ውስጥ የተሸሸገው አለ። ወንጀል ደግሞ በዚህም በዚያም ይፈጽማሉ። ስለዚህ እኛ ውስጥ ያለ አለ፤ ከውጪም አለ” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ካሉ የፀጥታ ችግሮች አንጻር የመስተዳደሩ መዋቅር ላይ ትችቶች ሲሰነዘሩበት የቆየ ሲሆን፣ ባለሥልጣናትም መዋቅራቸውን ለማስተካከል እርምጃ እንደሚወስዱ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ቆይተዋል።  

“የሥልጣን ጥም የለኝም”

አቶ ታዬ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው እና በተለያዩ መድረኮች አባል የሆኑበትን አስተዳደር አጥብቀው የሚተቹት ‘ሥልጣን ስለሚፈልጉ ነው’ የሚሉ ትችቶች ሲነሱባቸው ይታያል።

አቶ ታዬ ግን ይህ “ቀልድ ነው” ይላሉ።

“ሥልጣን ብንፈልግ ኖሮ በወያኔ ዘመንም አገኘው ነበር። ወያኔ አይደለም ለእኛ አይነት ሰው በአግባቡ መጻፍ ለማይችሉት ሁሉ ሥልጣን ሲሰጥ ነበር። ሥልጣን ፍለጋ እድሜያችንን አልገበርንም።”

አቶ ታዬ አሁን ያሉበት የሚኒስትር ዲኤታ ሥልጣን ከዚህ ቀደም ከነበሩበት ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረው፤ “ሰው በየዕለቱ እየተገደለ፣ ኢኮኖሚ እየደቀቀ፣ ወጥቶ መግባት እና በሕይወት መኖር አሳሳቢ በሆነበት ጊዜ ምን አይነት ሥልጣን ያምራል? የማይመስል ነገር ከማስመስል ቢቀር ይሻላል” ብለዋል።

Exit mobile version