Site icon ETHIO12.COM

መንግስ የተኩስ ማቆም ስምምነትን ቅድሚያ ያደረገ የሰላም ሃሳብ ለአፍሪካ ህብረት አቀረበ

የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሰላም እንዲሰፍን ሩቅ መንገድ መጓዙን አስታውቋል። በዝርዝር የተጓዘበትን መንገድ ያወሳው ኮሚቴው በትግራይ፣ አማርና አፋር አዋሳኝ አካባቢ ያሉ ዜጎች ድጋፍና መሰረታዊ አገልግሎት ማግነት እንዲችሉ ቅድሚያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረገ ለአፍሪካ ሕብረት ሰነድ ልኳል። ዓለምም ይህንኑ እንዲረዳ ማድረጉን አመልክቷል።

የትግራይ ክልልን እየመራ ያለው ትህነግ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን በአስቸኳይ ወልቃይት ለትግራይ ካልተመለሰና አገልግሎት ካልተጀመረ ጦርነት እንደሚከፍቱ፣ የቀድሞ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ደግሞ በቂ የጦርነት ዝግጅት መደረጉና፣ ሰራዊታቸው በሃይል የሚፈልገውን ለማድረግ ብቃት እንዳለው ካስታወቁ በሁዋላ የተቋረጠ መሰረተ ልማት ለማስጀመር ከፌደራል ወደ ትግራይ ለሚሄዱ ባለሙያዎች ሙሉ ዋስትና መስጠታቸው ገልጸው በዲፕሎማቶች ፊት ደብዳቤ መላካቸው አይዘነጋም።

በቅርቡ መግለጫውን ያወጣው የአገሪቱ የደህንነት ምክር ቤት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ካለው የጸጥታ ሃይል አቅም በላይ ሊሆን የሚችል ሃይል እንደሌለ፣ እንደውም የሚመጣጠን ባለመሆኑ ስጋት እንደሌለ አስታውቆ ነበር።

“የትግራይን ክልል በመወከል ትህነግ ብቻውን የመደራደር ችሎታውም ሆነ ብቃቱ የለውም” በሚል በትግራይ የሚገኙ ተገዳዳሪ ነን የሚሉ ድርጅቶች ያወጡት መግለጫና ማስጠንቀቂያ ምን እንደደረሰ በይፋ ባይገለጽም መንግስት ተኩስ እንዲቆምና ጠይቋል። የተኩስ ማቆሙ ስምምነት ለቀጣይ ንግግር መነሻና መደላድል እንደሆነም አመልክቷል። አያይዞም ይህ ሲሆን የትም ቦታ ለሰላም ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑንን አስታውቋል። የአውሮፓ ህብረት መንግስት የተናጠል ተኩስ ማቆሙ፣ ያለገደብ እርዳታ እንዲገባ መፈቀዱ፣ የዓለም የምግብ ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ከ4 ሺህ በላይ ከባድ መኪኖች ትግራይ መድረሳቸው፣ በጎ ቢሆንም እንደማይበቃ ጠቅሶ የተቋረጡ አገልግሎቶች እንዲከፈቱ ደጋግሞ ወትውቷል።

መንግስት በበኩሉ የተንሸዋረረ የሚለውን የውጭ አገር ጫናና ግፊት ተቋቁሞ ከፍተኛ ሁሉን ያካተተ የምድርና የአየር ላይ የመከላከያ አቅም በመገንባቱ ብተለያዩ አጋጣሚዎች እየገለጸ፣ ማናቸውንም ጥቃት የሚፈጽሙ አካላት ከውጭም ሆነ ከውስጥ የማያዳግም፣ ጊዜ የማይወስድ ምላሽ እንደሚሰጥ፣ በቅርቡም የትህነግ ሃይል ዳግም ጥቃት እከፍታለሁ ብሎ ከሞከረ ሃላፊነቱን ራሳቸው እንደሚወስዱ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ዲፕሎማቶች ካስታወቅ በሁዋላ ይህን የተኩስ አቁም ስምምነት መቅደም እንዳለበት የሚያስገነዝብ የሰላም ሰነድ ለአፍሪቃ ህብረት ማቅረቡ ትህነግን በደጋፊዎቹን ሰላም በሚፈገው የትግራይ ተውላጅ መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የሚከተው እንደሆነ የሚገልጹ መኖራቸው ተሰምቷል።

ሙሉ መግለጫው እነሆ።

መንግስት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት የጀመረውን ጥረት ከዳር ለማድረስ የተቋቋመው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ፣ እስካሁን የነበረውን እንቅስቃሴ፣ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት አድርጓል።

እንደሚታወሰው ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት ለሰላም እድል ለመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ለአብነትም የተናጠል የሰብዓዊነት ተኩስ አቁም ማወጅን ጨምሮ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳት፣ እስረኞችን መፍታት፣ የሰብዓዊ ድጋፍን በከፍተኛ ሁኔታ የማሳለጥ እና መሰል እርምጃዎችን ወስዷል።

ከእነዚህ እርምጃዎች በተጨማሪ፣ መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እና ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ይታወቃል ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የሰላም ንግግር ያለቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ለመጀመር ያለውን ዝግጁነት መግለፁ ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት የሰላም አማራጭን በዘላቂነት እውን ለማድረግ እና በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል፣ በተለይም የግጭት ሰለባ እና ተጋላጭ በሆኑ የትግራይ፣ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ዜጎች በእለት ተእለት ኑሮዋችው እየገጠማቸው ያለውን ችግር መቀረፍ እንደሚገባ፤ በተለይም የሰብዓዊ ድጋፍ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማድረስ ይቻል ዘንድ፣ እንዲሁም የመሰረተ ልማት እና የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም ስራ ለማስጀመር አስቻይ የሆነ ሁኔታ በፍጥነት ለመፍጠር፤ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በአጭር ጊዜ ላይ መድረስ እንደሚገባ ኮሚቴው አጽኖት ሰጥቶ ተወያይቷል።

ይህን ሂደት ለማፋጠን ይረዳ ዘንድ፣ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሰረት የሚጥል የሰላም ምክረ ሃሳብ ላይ ውይይት በማድረግ የምክረ ሃሳብ ሰነዱን በማዳበር አጽድቆዋል።

እንዲሁም ኮሚቴው ይህ ምክረ ሃሳብ በተቻለ ፍጥነት ለአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ወኪል እንዲቀርብ ወስኗል።

እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትን የሰላም ጥረት በሚደግፉ አካላት ትብብር በመታገዝ በአጭር ጊዜ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ይቻል ዘንድ፣ የሰላም ምክረ ሃሳቡን በተመለከተ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማብራሪያ እንዲሰጥ በወሰነው መሰረት ይህ ተግባር በዛሬው እለት ተከናውኗል።

በተጨማሪም ኮሚቴው፣

ወደተኩስ አቁም ስምምነት ሲገባ በሚፈጠረው አስቻይ ሁኔታ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በተቻለ ፍጥነት መልሶ ማቅረብ ይቻል ዘንድ፣ አስፈላጊ ቅደም ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን፤

የአፍሪካ ህብረትም የሰላም ንግግሩ በአስቸኳይ ተጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል ዘንድ፣ የሰላም ንግግሩ የሚካሄድበትን ቦታ እና ጊዜ በፍጥነት ወሰኖ ንግግሩ እንዲጀመር፣ ይህን ማድረግ ይቻል ዘንድ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ ገምግሟል።

እንዲሁም የሰላም አብይ ኮሚቴው፣ ከላይ የተመላከቱትን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ፣ የሚመለከታቸው ንዑስ ኮሚቴዎች እና ተቋማት አስፈላጊውን እንቅስቃሴ ከወዲሁ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

በተጨማሪም ለሰላም አማራጩ እውን መሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳየውን ድጋፍ በማድነቅ፣ ይህ ድጋፍ ተጥናክሮ እንዲቀጥል፤ የአለም አቀፉ ማህበረሰብም ከአፍሪካ ህብረት ጎን በመቆም የሰላም ጥረቱ የተሳካ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ኮሚቴው ጥሪ አስተላልፏል።

Exit mobile version