Site icon ETHIO12.COM

«ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ ተጓዦች ላይ የተደረገው ቁጥጥር የህወሀት ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ነው»

ከሰሞኑ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ ተጓዦች ላይ የተደረገው ቁጥጥር የህወሀት ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ነው ሲል የፌደራል መንግስት ገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታርያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ኹኔታ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው በሰላም እና ጸጥታ፣ ለሰሜኑ ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ባሉ ጥረቶች፣ በሰብዓዊ ድጋፎች እና አረንጓዴ አሻራ ላይ አተኩረዋል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ በመስጠቱ ዙሪያ፤ በመጪዎቹ ሳምንታት የተኩስ አቁም እንዲደረስ፣ የሰላም ውይይት እንዲሁም ሌሎች በእንጥልጥል የቀሩ ጉዳዮች ደግሞ በብሔራዊ ምክክሩ እንዲዳሰሱ ለማድረግ የሚያስችል የሰላም ረቂቅ ሰነድ ይፋ መደረጉን አንስተዋል፡፡

በሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ የተዘጋጀው ሰነዱ መንግስት ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ በሚፈታበት ሁኔታ ላይ እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት አመላካች ነውም ብለዋል፡፡

የሰላም ውይይት ምንም አይነት ቅድመ ኹኔታ የሚያስፈልገው አይደለም ያሉት ቢልለኔ፤ የትግራይ ሕዝብ የህወሃት እስረኛ ሆኖ ሊቀጥል አይግባም ነው ያሉት፡፡

ህወሃት ፍላጎቱን ለማስፈፀም በትግራይ ክልል በተከታታይ የኀይል አማራጮችን እየተጠቀመ እንደሚገኝ ያነሱት ኃላፊዋ፤ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም ጭፍጨፋዎችን እንደሚፈፅም አመልክተዋል፡፡

በህገወጥ መንገድ የሰበሰበውን የውጭ ምንዛሬ፣ ለመጠባበቂያነት የተቀመጡ የነዳጅ፣ የምግብና የመሳሰሉ ግብአቶችን ለዚሁ እኩይ ተልዕኮው እንደሚጠቀም ጠቁመዋል።

ቡድኑ ይህን ሁሉ እኩይ ተግባራት እየፈፀመ ባለበት ኹኔታ፤ መንግስት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ነገሮችን በሆደ ሲፊነት ሲመለከት መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ከጦርነቱም በፊትም ሆነ በጦርነቱ ወቅት እንዲኹም ከጦርነቱም በኃላ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርግ እንደቆየና በህወሃት በኩል ለሰላም አማራጭ የተሰጠ ሥፍራ አለመኖሩን በማንሳት አኹንም በዚሁ ባህሪው መቀጠሉን ነው ያነሱት።

ህወሃት የሀሰት ክሶችን በማንሳትና የተሳሳቱ ትርክቶችን በመንዛት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በተሳሳተ አቅጣጫ ለመምራት ሙከራ እያደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

በመኾኑም በትግራይ ክልል ዙሪያ ብዥታ ሊኖር እንደማይገባና በክልሉ መላሶ ግንባታና መሰረታዊ ድጋፎች ላይ መንግስት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት ባለሙያ በመላክም ሆነ እዛው ያሉውን የሰው ኀይል በመጠቀም በክልሉ መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎት ለመመለስ ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም ደግሞ አንዳንድ በመሬት ላይ ያሉ ኹኔታዎች እንዲሻሻሉ እንደሚፈልግም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት መሪነት በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ የሰላም ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መኾኑንም አረጋግጠዋል።

ኃላፊዋ ከሰሞኑ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ ተጓዦች ላይ እየተደረገ ስለሚገኘው ቁጥጥር አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም ህወሃት በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ወረራ በፈፀመበት ወቅት የዘረፋቸውን የመንግስት ማህተሞች በመጠቀም ሀሰተኛ መታወቂያ በማሳተም ለእኩይ ተግባሩ እያዋለ በመኾኑ፤ ይህንን ድርጊቱን ለመግታት እና ተከታትሎ ለመያዝ በተወሰደ እርምጃ የተፈጠረ መኾኑን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ግን የትራንስፖርት አገልግሎቱ ወደ ቀድሞ ኹኔታው መመለሱን ነው የተናገሩት።(አሚኮ)

Exit mobile version