Site icon ETHIO12.COM

“አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ህዝብ ላይ ያለው ጥላቻ ከፖለቲካ አደረጃጀቱ ይመነጫል”

አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ላይ ያለው ጥላቻ ከህዝባዊ ግንኙነት ሳይሆን ከሽብር ቡድኑ የፖለቲካ አደረጃጀት የመነጨ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሕወሓትን ያቋቋመው ቡድን ከመጀመሪያውም ጠላት ብሎ የተነሳው የአማራን ሕዝብ ነው፡፡

ቡድኑ ከአርባ ዓመት በፊት ጀምሮ በአማራ ህዝብ ላይ ያለውን ቂምና ጥላቻ በመያዝ ለም የሆኑ የወልቃይትና የሁመራ አካባቢዎችን በቁጥጥሩ ስር በማዋል እና ህብረተሰቡ ከአካባቢው እንዲሰደድ በማድረግ ግፍ ሲፈጽም እንደነበር በርካታ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህንን የተመለከተ መጽሐፍን ሰሞኑን ለምረቃ በቅቷል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው እንዳሉት፤ ቡድኑ ወደስልጣን ለመምጣት የትግራይና የአማራ ህዝብ በታሪክ ጠንካራ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አላቸው፡፡ ነገር ግን ሾልኮ በወጣው ሰነድ በአማራና በትግራይ ሕዝብ መካከል የተንጸባረቀው ጥላቻ መጀመሪያ ላይ ሕወሓት እንደፖለቲካ ድርጅት ሲደራጅ ያመጣው መሆኑን መጋለጡን ነው የጠቆሙት፡፡

በኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በተግባር በሕዝባዊ ስብሰባዎቹ፣ በየመድረኮቹ፣ በሚዲያው አማራ እንዲጠላ በቡድኑ ታቅዶና ታስቦበት መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡

ይህ ሰነድም የቀድሞው የሽብር ቡድኑን አስተሳሰብ መቀጠሉን፣ ከወሰን ጋር ተያይዞም የአማራን ሕዝብ ጠላት የማድረግ አባዜውን የሚያሳይ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ አቋም በመያዝና ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀኑንም ስለማይወደው ይህንን ህዝብ የማዳከም ስልቶች እንደሚንጸባረቁበት ሾልኮ በወጣው ሰነዱ ላይ መቀመጡንም ነው ያነሱት፡፡

አሸባሪ ቡድኑ መጀመሪያ ላይ የአማራ ገዢ መደብ ብሎ ሲያቀነቅን እንደነበር፣ ትግል እያፋፋመና ብሄርን እያጠናከረ ሲሄድ ደግሞ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ጠንቀኛ ሆኖ መታየት ያለበት ነው ብሎ በማመን የሃሰት ተረኩን መቀጠሉንም አንስተዋል፡፡

ጌታቸው ረዳም ሆነ በሽብር ቡድኑ አቀነባባሪዎች የሚሰጡ መግለጫዎችና ፕሮፖጋንዳዎች የሕወሓት እኩይ ተግባርን ሕዝብን ለመከፋፈል፣ አንዱን በአንዱ ላይ ለማስነሳትና ውዥንብር ለመፍጠር ያለውን ጽኑ ፍላጎት ማንጸባረቁንም አንስተዋል፡፡

የሚስጢር ሰነዱ ላይ ቡድኑ ወጥ የሆነ ፕሮፖጋንዳ ማራመድ እንዳልቻለ የተጋለጠበት መሆኑን ጠቁመው፤ በአንድ በኩል አማራ ጠላታችን ነው ብሎ ያስባል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከአማራ ሕዝብ ጋር የነበረንን ወዳጅነት እንቀጥላለን፣ አንጎዳውም ይላል፤ እንደሰሞኑ በጨነቀ ሰዓትና ነገሮች አልሆን ሲሉ አማራን ለጊዜውም ቢሆን በፖሮፖጋንዳ በቃል የመሸንገል ሥራ ይሰራል፤ በአጠቃላይ የተምታታበት አካሄድ ነው፡፡

መሬቱን መያዙንና ሲጨፈጭፈውና እንዲጨፈጨፍ ያደረገ ሕዝብ መሆኑን ዘንግቶ ዝብርቅርቅ ንግግሩ የቡድኑን እኩይ ባህሪውን ያሳየበት መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

የሽብር ቡድኑ መሪዎች ንግግር አንድም ከድርጅቱ እኩይ ባህሪነት እንደገናም ከግለሰብ ተፈጥሯዊ ባህሪ የመነጨ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የሰሞኑ ንግግርም ሕወሓት አማራ ላይ ያለውን አቋም አለመቀየሩን፣ እንደ ሕዝብ ጠላቴ ነው ብሎ የሚፈርጀውን እንደቀጠለበት ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ጌታቸው ረዳ ፖለቲከኛ ከመሆኑም በፊት በትምህርት ቤት ሕግ ሲማር ሲያውቁት ቅጥፈትና ሃሰት የተሞላበት እንደነበር፣ ይህ የግል ባህሪው ወደሕወሓት እንዲወሰድ እንዳደረገውም ረዳት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

ሕዝብና መንግሥት አንድ ሆነው አቅም እንዳይፈጥሩ ክፍፍል የመፍጠር አካሄድ ለመከተል በሰነዱ ማስቀመጡን ያነሱት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ሕዝብና መንግሥት መካከል መቃቃርን መፍጠር፣ በሕዝብ መካከልም መቃቃርና መጠራጠር ስሜቶች እንዲፈጠር ለመስራት መነሳቱን በሰነዱ ላይ እንደተቀመጠ ተናግረዋል፡፡

የተሳሳተ የፖለቲካ ትንተናቸውን ያነሱት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ አማራ ክልል ላይ ፋኖ በመታሰሩ በክልሉ መንግሥትና በፋኖ መካከል ክፍተት በመኖሩ ሕዝብን ለማንቀሳቀስ እንደማይመችና ጠንካራ ማጥቃት ቢደረግ የመከላከል አቅም የለም የሚል አስተሳሰብ አለው፡፡

ፋኖን የመኮነንና በሌላ በኩል ደግሞ የክፍተት ምንጭ ማድረግ በፖሮፖጋንዳ የማዳከም ሥራ ቁልጭ ብሎ መቀመጡንም አንስተዋል፡፡ የፖለቲካ ነበልባል የሚያስነሱ ጉዳዮችን ወደራሱ ጥቅም የመቀየርም በታክቲክነት ለመጠቀም የጠነሰሰው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ የአካባቢ አስተዳደሮችን እምነት በማሳጣት የማዳከም፣ መንግሥትና ሕዝብ ሆድና ጀርባ ለማድረግ የወጠናቸው አንዳንዶቹ ቡድኑ ቀድሞም ሲሰራበት የነበረ፣ ገሚሶቹ ወቅታዊ ንፋስ አመጣሽ ነጥቦችን በማቀጣጠል መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት የማዳከም ስልት ነው ብለዋል፡፡

ሰሞኑን ከሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሾልኮ የወጣው ሰነድ እንዳመለከተው ቡድኑ በተለይ የአማራ አርሶ አደር እርሻውን እንዳያርስና ያረሰውንም እንዳይሰብስብ በማድረግ ልማን ማደናቀፍ አንዱ ስልቱ አድርጎ የያዘ ሲሆን ከዚህም አልፎ ሰርጎገቦችን በማስገባት ክልሉን ብሎም ሃገርን ማተራመስ የሚል ስልት የያዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ዘላለም ግዛው አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2014

Exit mobile version