ETHIO12.COM

ከአሸባሪው ትህነግ ተልዕኮ ተቀብለው አዲስ አበባ የመሸጉ የሽብር ቡድን አባላት ተያዙ ሁለቱ ወዲያው ተገደሉ

ከአሸባሪው ትህነግ ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ እና አካባቢው የህዝብን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ 19 የሽብር ቡድን አባላት በተደረገው ከፍተኛ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ

ከአሸባሪው ትህነግ ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ እና አካባቢው የህዝብን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ 19 የሽብር ቡድን አባላት በተደረገው ከፍተኛ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

ጠላቶቻችን አዲስ አበባን የሽብር ማዕከል እናደርጋለን ብለው በአደባባይ ከፎከሩበት ጊዜ ጀምሮ እኩይ ተግባራቸውን ለመፈፀም ያላደረጉት ሙከራ እንዳልነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

በውጭና በውስጥ ተላላኪ የሚዲያ አውታሮቻቸው ከሚያናፍሱት የሐሰት ፕሮፓጋንዳና የተዛባ መረጃ ባሻገር በልዩ ልዩ የተሽከርካሪ የውስጥ አካላት ጭምር ድብቅ ቦታዎችን እያዘጋጁ ከነብስ ወከፍ እስከ ቡድን የጦር መሳሪያዎችን ወደ ከተማው ለማስገባት ያደረጉት ሙከራ በህብረተሰቡ ተባባሪነትና በፀጥታ ኃይሉ ብርቱ ጥረት እንደከሸፈ የሚታወስ ነው፡፡

ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ደግሞ ጠላቶቻችን ስልታቸውን በመቀየር በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ህዝቡ የደህንነት ዋስትና እንዳይሰማው እና ሰላም እንዲያጣ በማቀድ በንፁሃን ላይ ከባድ የዘረፋ እና የውንብድና ወንጀሎችን ጨምሮ አሰቃቂ ግድያን ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመሆን ባደረገው የተቀናጀ ኦፕሬሽን እነዚህ የወንጀል ቡድኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በጉዞ ርቀት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ በተለምዶ ራይድ ተብለው የሚጠሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ተሳፋሪ መስለው ከገቡ በኋላ ወደ ሰዋራ ስፍራ ወስደው በአሽከርካሪዎቹ ላይ የግድያ እና የውንብድና ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የቆዩ፡-

1ኛ. ሸዊት ሐዲስ፣
2ኛ. ዳዊት አለሙ፣
3ኛ. በሪሁ ናይዝጊ፣
4ኛ. ሃይለአብ ወርቁ የተባሉት ፖሊስ ባደረገው የሌት ተቀን ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ገዳይ ቡድኑን በማሰማራት፣ ድጋፍ በማድረግ፣ የተዘረፉ ንብረቶችን በመሸጥና በሽያጩ የተገኘውን ገንዘብ መልሶ ለወንጀል ተግባር እንዲውሉ በማድረግ በአጠቃላይ ለገዳይ ቡድኑ የቁሳቁስና የፋይናንስ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ፤

1ኛ. በረከት መዝገበ፣
2ኛ. ሰናይ ሐይላይ፣
3ኛ. ማዕረጉ በርሔ፣
4ኛ. ይኩኖአምላክ አማረ፣
5ኛ. ፀሀዬ ተስፋዬ እና
6ኛ. ዳንኤል ገ/ማርያም የተባሉት ተጠርጣሪዎችን ጥምር የፀጥታ ሃይሉ ባደረገው ብርቱ ክትትል በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል በጦር መሳሪያ የተደገፈ ዘረፋ፣ የመግደል ሙከራ እና የውንብድና ወንጀሎችን በየካ፣ በለሚኩራ፣ በቦሌ እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ሲፈፅሙ የቆዩ፡-

1ኛ. ፊሊሞን ህንፃ፣
2ኛ. አቡሽ ገ/እግዚአብሄር፣
3ኛ. መሰለ አባዲ ፣
4ኛ. ቸርነት ውዱ ፣
5ኛ. አቡሽ ግደይ፣
6ኛ. ህሉፍ ፈፀጉ፣
7ኛ. ወልደ ገብርኤል ህይወት፣
8ኛ. ሄኖክ ብርሃኔ እና
9ኛ. ክብሮም ንጉሱ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ በብርቱ ክትትል በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ሲሆን ግለሰቦቹ ስለፈፀሙት ወንጀል በተጨባጭ ማስረጃ የተረጋገጠባቸው ከመሆኑም ባሻገር ወንጀል መፈፀማቸውን አምነው ቦታውንና አፈፃፀሙን ለፖሊስ መርተው አሳይተዋል፡፡

በተወሳሰበ መንገድ በየጊዜው የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶች አሳሳቢነታቸውን በመገንዘብ እና ፖሊስ ከህብረተሰቡ ያገኛቸውን መረጃ መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል ምርመራና የክትትል አባላት ባደረጉት ብርቱ ክትትል እና ጥምር የፀጥታ ሃይሉ ባካሄደው ሰፊ ኦፕሬሽን በአጠቃላይ 19 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን የወንጀሉ ፍሬ የሆኑ 12 ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች፣ ለዕኩይ አላማ ማስፈፀሚያ ይጠቀሙባቸው የነበሩ የተለያዩ ሐሰተኛ ሰነዶች እና ልዩ ልዩ የፀጥታ አካላት የደንብ ልብስም ተይዘዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በፖሊስ ላይ ጥቃት ለመፈፀም በሞከሩ ሁለት የዘረፋ ቡድኑ አባላት ላይ ዕርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን በግንባር የከፈተብንን ጥቃት እንደማያዋጣው ሲያውቅ የከተማ ላይ ሽብር ለመፍጠር የሽብር ቡድኑን አባላት መልምሎ በድብቅ ወደ አዲስ አበባ ላስገባቸው ተላላኪዎቹ ልዩ ልዩ የጥፋት ተልዕኮ ሰጥቶ ቢያሰማራቸውም በጥምር ፀጥታ ኃይሉ የሚያኮራ ብርቱ ተግባር በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል፡፡

ፖሊስ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ለመከላከል በፀጥታ ኃይሉ የሚደረገው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እየገለፀ ሁሌም ለሰላማችን መረጋገጥ ከጎናችን ያልተለየው ህዝባችን ቀና ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version