Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ አንደ አገር ገናና በነበረችበት ዘመን አሜሪካ አትታወቅም ነበር

Made with LogoLicious Add Your Logo App

“ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተሻግራ እንደ ሀገር ንጉሥ ሰለሞንን ስትጎበኝ አሜሪካ እንደ አህጉርም እንደ ሀገርም አትታወቅም ነበር” አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ

10ኛው የጣና ፎረም ውይይት በሦስተኛ ቀኑ ሲቀጥል “አህጉራዊውን የሰላም እና ደኅንነት ምህዳር፤ ለችግሮች ምላሽ የመስጠት አቅምን መገምገም” በሚል የመወያያ ሃሳብ ላይ ትኩረት አድርጓል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጣና ፎረም ቦርድ አባል አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የጸጥታው ምክርቤት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሃናህ ቴታህ፣ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሃመር እና አምባሳደር ባንኮሌ አድዮ ለተወያዮቹ መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።

አፍሪካ በሰው ሃብት የከበረች እና በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች አህጉር ብትሆንም ከውስጥም ከውጭም በነበረባት የዘመናት ተከታታይ ተጽዕኖ ምክንያት በምግብ ራሷን ያልቻለች፣ ተደጋጋሚ ጦርነት እና ግጭት መለያዋ የሆኑ አህጉር ሆናለች ብለዋል።

አህጉሪቷ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ድክመት፣ ፍትሐዊ የውኃ እና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጉድለት ሲፈትኗት ዘልቀዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እና መንፈስ የሚቀነቀነው “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የአህጉሪቷን ውጫዊ ተፅዕኖዎች በመቀነስ እና በመቋቋም በኩል ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

አሜሪካ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” መሳካት ድጋፍ ታደርጋለች ያሉት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሃመር ለዚህ ማሳያ የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር በሚደረግ ንግግር እንዲፈታ ሙሉ ድጋፏን ማሳየቷ ነው ብለዋል።

ለአፍሪካ ሀገራት ፈተና እና ችግሮች ከአሜሪካ የተሻለ ድጋፍ ያደረገ ሀገርም አህጉርም ያለ አይመስለኝም ያሉት ልዩ መልዕክተኛው ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ አፍሪካ ሀገራት የምግብ እጥረት በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር አውጥታ ድጋፍ አደርጋለች ብለዋል፤ ምንም እንኳን የአምባሳደሩ ንግግር በፎረሙ ተሳታፊዎች ዘንድ ተቃውሞ ቢገጥመውም።

ልዩ መልዕክተኛው አያይዘውም የአሜሪካ መንግሥት ለአፍሪካ ችግሮች የተመረጡ የመፍትሔ ሃሳቦችን እያነሳ ተግብሩ አይልም፤ ነገር ግን የምታመነጩትን የመፍትሔ ሃሳቦች ለመተግበር ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። አፍሪካ ለችግሮቿ ኃላፊነት መውሰድ ያለባትም ራሷ አፍሪካ ናት ብለዋል።

ከፎረሙ ተሳታፊዎች ጠንካራ ውይይት እና ክርክር በኋላ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ያለፈው ታሪካችን ሊያስተምረን ይገባል፤ ስለችግሮቻችን ማንንም አንወቅስም መውቀስ ካለብን ራሳችንን ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአክሱም ዘመን የነበረንን ስልጣኔ ተመልከቱ፤ በግብጽ የነበረንን የቀደመ ስልጣኔ አስቡ፤ ችግራችን የነበረንን ጥንታዊ ስልጣኔ እና ታሪክ በተገቢው መንገድ ለልጆቻችን አለማስተማራችን ነበር ያሉት አቶ ኃይለማርያም አሁን ላይ ግን ለልጆቻችን ከማስተማራችን በፊት ስለራሳችን የተሳሳተውን እይታችን ማረም ይገባናል ብለዋል።

“ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ሳባ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተሻግራ እንደ ሀገር ንጉስ ሰለሞንን ስትጎበኝ አሜሪካ እንደ አህጉርም እንደ ሀገርም አትታወቅም ነበር” ያሉት አቶ ኃይለማሪያም ከኋላ እየመጡ ለሚቀድሙን ሁሉ እርግጥ ነው ኅላፊነቱን መውሰድ ያለብን ራሳችን ነን ብለዋል። የጣና ፎረም መንፈስም ችግርን እንዲህ በግልፅ ተናግሮ በጋራ እና በትብብር መፍትሔ መፈለግ ነው ብለዋል።

አዎ! ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት አሜሪካ ለሀገሬ ኢትዮጵያ በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላር አውጥታ ምግብ እረድታ ይሆናል፤ ነገር ግን አሜሪካ የረዳችን ከችግራችን በምንወጣበት መንገድ አልነበረም ብለዋል። ግብርናችን እንዲሻሻል፣ ቴክኖሎጂ እንድንጠቀም እና የተሻሻለ አሰራርን እንድንተገብር ተደጋጋሚ ድጋፍ የጠየቅናት አሜሪካ በፖሊሲ ሰበብ ፈቃደኛ አልነበረችም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው አሚኮ

Exit mobile version