Site icon ETHIO12.COM

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት እና ጉህዴን የሠላምን ስምምነት ተፈራረሙ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት እና በክልሉ ታጥቆ ሲንቀሳቀስ የነበረው የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የሠላምን ስምምነት ዛሬ ተፈራረሙ።

የሠላም ስምምነት ሠነዱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ሊቀ መንበር አቶ ግራኝ ጉደታ በአሶሳ ከተማ ተፈራርመዋል።
በሠላም ስምምነቱ ላይ በመከላከያ ሠራዊት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጀነራል አምዴ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ የክልሉ ምክርቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ አለምነሽ ይባስ፣ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድርን ጨምሮ የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ ሰምምነቱ ህገ-መንግስቱን ባከበረ መንገድ በውይይት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተናግረዋል።
ከስምምነቱ ቀደም ብሎ የንቅናቄው አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ሠፊ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ መደረሡንም ርዕሰ-መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

እስካሁን የተከፈለው ዋጋ ይበቃል ያሉት አቶ አሻድሊ፣ አሁን በክልሉ ለተፈጠረው አንጻራዊ ሠላም እና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በተደረገው ጥረት ውስጥ የሀገር ሽማግሌዎች የተወጡት ሚና እውቅና የሚሠጠው ነው ብለዋል።

የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ሊቀ መንበር አቶ ግራኝ ጉደታ፣ ለሠላም ሲባል ዛሬ ከክልሉ መንግስት ጋር በተደረገው ስምምነት እጅግ መደሠታቸውን ገልጸዋል።

በውይይት ላይ የተመሠረተ ልማት እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የሠላም ስምምነቱ በትክክል እስከታች ወርዶ ለክልሉ ሠላም ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም እንዲተባበር አቶ ግራኝ ጥሪ አቅርበዋል።
በስምምነቱ ወቅት የተገኙ የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው፣ ለህዝብ የምናስብ ከሆነ የእስካሁኑ ይበቃናል፣ አንድ ለይ ሆነን ሠላምና ልማታችንን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ይህ ስምምነት ለጠላቶቻችን እንቅልፍ የሚነሳ ነው ያሉት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጠላቶቻችንን አንገት ለማስደፋት በጋራ ቆመን የክልሉን ሠላም ማሠጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ለዚህ ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

ስምምነቱ ችግሮችን ወደጫካ ገብቶ በመሣሪያ በመታገል ሣይሆን በሠላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍትሔ መስጠት እና በመተከልና ካማሺ ዞኖች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አስተማማኝ ሠላም በማስፈን የክልሉን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ማዕከል ያደረገ ነው ሲል የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዘግቧል።

Exit mobile version