ETHIO12.COM

አሜሪካ “ሕዝቡ አገርኑ ይወዳል ከዚህ በላይ ጫና ማድረግ አንችልም”፤ ትህነግ ተስማምቶ ተነጋጋሪ ሰየመ

ፎቶ - የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በግጭት ላይ ያሉ ሁሉም አካላት በአፋጣኝ ወደ ድርድር እንዲመጡ በጠየቁበት ወቅት ይህንኑ ለኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ማማከራቸው ተጠቅሶ በተዘገበበት ወቅት የተሰራጭ ምስል ነው

ይህ ጦርነት ሃዘኑ አሁን ሳይሆን ወደፊት ነው። የዚህ ጦርነት ጠንሳሾችና ተዋንያኖች ዛሬ ሳይሆን አድሮ ገበናቸው ሲወጣ ለቅሶው እጥፍ፣ ሃዘኑ ገዚፍ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይህ ጦርነት እያንዳንዱ ቤት ውስጥ የቀበረው የሃዘን ጉድ ከብዛቱ አንጻር እረፍት ሲሆን ጩኸቱን አንሰማም ቢሉም አይቻልም። ባለቀ ሰዓት አሜሪካ ” ሕዝቡ አገሩን ይወዳል” ስትል ሞክራ ሞክራ፣ ሁሉንም ድንጋይ ፈንቅላ እንዳልሆነ ገሃድ አስታውቃለች መባሉ ተሰምቷል። ሁሉም ተዳምሮ ምስኪኖች ጫንቃ ላይ የወደቀውን ሃዘን ማን ይጠበው?

ቀደም ሲል “እነማን ይወከሉ” በሚለው አጀንዳ መግባባት ያቃታቸው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ወታደራዊና የፖለቲካ አመራሮች የፊታችን ሰኞ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሰላም ንግግር ላይ የሚሳተፉ አካላትን ለመሰየም የነበራቸውን ልዩነት አጥብበው መስማማታቸው ተሰማ። በእለቱ ንግግሩ ከሚገኝበት አገር እንደሚደርሱ ይጠበቃል።

ይህ የተሰማው የትህነግን ውስጣዊ ሁኔታ የሚከታተሉና ንግግሩ እንዲካሄድ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ከሚያደርጉ ዲፕሎማቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው የአሜሪካ ነዋሪ የመረጃው ባለቤቶች ናቸው።

ከስራቸው ባህሪ አንጻር ማንነታቸው ከዜናው ፍንጭ ሊሰጥ በማይችል መልኩ እንዲርቅላቸው የጠየቁ መሆናቸው አስታውቀው መረጃውን ያቀበሉን እንዳሉት ቀደም ሲል በወታደራዊ አመራሩና በፖለቲካው አመራሩ መካከል “ማን ወደ ደቡብ አፍሪካ ይሂድ፣ ማን ይቅር?” የሚለው ጉዳይ አላስማማም ነበር።

” ከአገር ውጭ የሚኖሩት ይወከሉ፤ እኛ እዚሁ ሆነን አብረን የመጣውን እንቀበል” በሚል ወታደራዊ አመራሮች ግትር አቋም ቢይዙም ከወዳጆቻቸው በኩል በተደረገ የማግባባት ስራ፣ ከውጭም አመራሮቻቸው ጣልቃ በመግባት ሙግቱ ቀንሶ ከስምምነት መደረሱን ነው መረጃውን ያደረሱን ያስታወቅት።

በአሜሪካና አውሮፓ መለሳለስ፣ በተለይም አሜሪካ ሶስተኛ የተባለውን ጦርነት ትህነግ መጀመሩን፣ ተንኮሳ እንዲያቆም በማሳሰብ ያወጣቸው መግለጫ ያላስደሰታቸው የትህነግ ሰዎች ” ህዝብ አገሩን ይወዳል። ከዚህ በላይ ኢትዮጵያን መጫን አንችልም። የምችለውን ሁሉ አደረግን አልሆነላችሁም። አሁን ከመስማማት ውጭ አማራጭ የላችሁም” የሚል ይዘት ያለው ጥቅል አሳብ ከተነገራቸው በሁዋላ ተስፋ ወደ መቁረጡ በሄዳቸውንም እነዚሁ ክፍሎች አመልክተዋል። የዶክተር ቴውድሮስም ለቅሶ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑ ተሰምቷል።

በተለይም አሜሪካ የመከላከያ ሰራዊትን ሁሉ አቀፍ ዝግጅትና የሕዝቡን የድጋፍ ስነልቦና ከገመገመች በሁዋላ ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማያዋጣ ደጋግማ አስታውቃ ስለነበር ትህነግ ውጊያውን በመጀመሩ ደስተኛ አልነበሩም። አሌክስ ዲዋል እንዳለው የትህነግ ሃይል ሙሉ በሙሉ ወደ መፍርከስ መሻገሩን ተከትሎ አሜሪካ “ትንኮሳ አቁሙ” ስትል ባለተለመደ መልኩ ተግሳጽ ያቀረበችው ከዚህ ስሜት የተነሳ እንደሆነ ከመረጃ ሰዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

አሁን ላይ መንግስት በሁሉም አቅጣጫ የበላይነቱን በመያዙ ድርድር የሚባል ነገር እንደሌለ፣ የሚደረገው የሰላም አማርጭ ንግግር እንደሆነ፣ ንግግሩ ፍትህን የሚያካትትና በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ “ቅጽበታዊ” የተባለውን ጥቃት ያቀዱ፣ ያስተባበሩና ያከናወኑ አመራሮች በየትናውም መስፈርት በክህደት ወንጀል ከመተየቅ እንደማያልፉ፣ መንግስት በዚህ ረገድ አቋሙ የጸና እንደሆነ ለአሜሪካ በግልጽ እንደተነገረ ከወዲሁ ለማወቅ ተችሏል።

አሜሪካ አስቀድማ ለምስራቅ አፍሪቃ የሾመቻቸው ጄፊር ፌልትስማንን ተደጋጋሚ ንግግር ካደረጉ በሁዋላ ለትህነግ አመራሮች በህዝብ እንደማይወደዱ ጠቅሰው ሌላ አማራጭ እንዲያዩ ሲመክሯቸው አልቀበልም ማለታቸው ተከትሎ ” 1983 ላይ የተቸከሉ” ሲሉ በአደባባይ ዘልፈዋቸው፣ በዛው ከሃላፊነቱ በበቃኝ መልቀቃቸው ይታወሳል።

ወደ ቆቦ በወረራ የገባው የትህነግ ሃይል ለጦርነቱ ሲወስን ዶክተር ደብረጽዮን ” አይሆንም፣ ይቅርብን፣ ህዝብ ከማስጨረሰ ውጭ የማናመጣው ነገር የለም” በሚል በከፍተኛ ደረጃ መቃወማቸውን ዲፕሎማቶች እንደመሰከሩ ያመለከቱት የመረጃው ባለቤቶች ዶክተሩ መከላከያ በለሊት በክህደት እንዲመታ ሲወሰንም ተመሳሳይ አቋም እንደነበራቸው ከነዚህ አካላት መስማታቸውን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ከሌሎች አካላት ይህን መረጃ ማረጋገጥ ወይም በተባራሪም ቢሆን መስማት አንዳልቻሉ ገልጸዋል።

በለውጡ ማግስት ዶክተር ደብረጽዮን “አዲስ አበባ ተደምረው፣ ትግራይ ሲሄዱ ይቀነሳሉ፡ በሚል ሽሙጥ አቋማቸው ሲገለጽ እንደነበር ይታወሳል። ይህን አስመልክቶ ከሳቸው የተሰማ ማስተባበያም ሆነ ተቃውሞ የለም።

ሰኞ በሚደረገው ንግግር ከትህነግ ጋር ቀደም ሲል አብረው የሰሩና የትህነግትን አካሄድ ጠንቀቀው የሚያውቁ የመንግስት ወኪሎች ልክ በ1983 ዓ.ም ኼርማን ኮሆን ሎንዶን ላይ መንግስትንና ተቃዋሚዎችን ሲያደራድሩ እንደተደረገው አዲስ ዜና ሊያበስሯቸው እንደሚችሉ የሚገምቱ አሉ።

ከውቅቱ ተደራዳሪዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር አሻግሬ ይገልጡ ኢሳት ላይ ቀርበው ሲመሰክሩ “ከድርድር ስንወጣ አገር አልባ ሆነን ነበር” ማለታቸውን ያስታወሱ ” የትህነግ ሰዎች ደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ ስሜት ሊያታጥሙ ይችልሉ” የሚል የሰፋ ግምት አላቸው።

ሎንዶን ድርድር እየተደረገ “ትጥቅህን አውርድ” በሚል የኢትዮጵያ ሰራዊት በግፍ ተበትኖ በጎዳና ላይ እንዲለምን፣ አገር በጠበቀ የባዕድ ሃይል ተደርጎ እንዲንከራተት ተደርጎ ነበር” ሲሉ የውቅቱን ድራማ የሚያስታውሱ ” አሁን ላይ ልክ እንደቀድሞ ባይሆንም ተኩስ አቁም ታውጇል። መሳሪያህን አውርድ” ወደ አንድ ካምፕ ተጠቃለል” የሚል መመሪያ ሊተላለፍ እንደሚችል ከግምት በላይ ይናገራሉ።

መንግስት በየትናውም ስፍራና ሰዓት ለሰላም ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑንን ሲያስታውቅ ፣ አንዳችም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ እንደማይቀበል ደጋግሞ ያስታወቀው ምን አልባትም የ1983ቱን ድራማ ሊደግመው ከማሰብ ይሁን ከሌላ የታወቀ ነገር የለም። በጥምር ጦር ስም ተቀናጅቶ በመከላከያ እየተመራ የትግራይን አሉ የሚባሉ ከተሞች እየተቆጣጠረ ያለው መንግስት ” የፌደራል የአየር ማረፊያዎችንና ንብረቶችን ሙሉ በሙሉ እቆጣጠራለሁ” ማለቱና የአገር መከላከያ ሰራዊት በአገሪቱ የፈለገው አካባቢና ክልል መስፈር እንደሚችል ማስታወቁ ጨዋታው መጠናቀቁን አመላካች እንደሆነ አድርገው የሚወስዱ አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ” ታላቅ የጦር ሃይል ስትገነባ ትከበራለህ” እንዳሉት አሜሪካ አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ግዝፈትና ዘመናዊ አደረጃጀት፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የበለጸገ በመሆኑ በቀላሉ ሊናድ እንደማይችል ያመነችበት ደረጃ በመድረሱ ይህን ሃይል ገፍቶ ከትህነግ ሚሊሻ ጋር “ፍቅር እስከመቃብር” ብዙም እንደማያስኬድ ማመኗን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውንም የሚገልጹ አሉ። አብይ አህመድም ለመስቀል በዓል ባደረሱት የንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ” እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ በዚህ ዓመት ሰላም እንደሚሰፍን ነው” ሲሉ ካለምንም መነሻ ይህን እንደማይሉ አሳባቸውን ያተናክራሉ። በትናትናው ዕለት በቡራዩ የልዩ ተሰጥዖ ባለቤት የሆኑ ተማሪዎች የሚማሩበትን ተምህርት ቤት ሲመርቁ ” በሰሜን ያለ ውጊያ ይቆማል ሰላም ይወርዳል። ከብልጽግና ጉዞ የሚያቆመን አንዳች ሃይል የለም” ሲሉ ንግግራቸውን ማጽናታቸውን በርካቶች ያደመጡት በዋዛ አይደለም።

ይህ በንዲህ እንዳለ የጸጥታው ምክር ቤት በዝግ በኢትዮጵያ ጉዳይ መክሮ ሳይስማማ ተበትኗል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር “እኔ ተጋሩ ነኝ” ሲሉ ባሰሙት ንግግር ” የዲፕሎማሲ ቃላት አልቀውብኛል” ሲሉ ዓለም ጄኖሳይድ እንዲጠብቅ አስተንቀቀው ነበር። እሳቸውን ተከትሎ አዲስ አበባ ተቀምጦ ሴራ የሚጠምቀው ቢቢሲ አማርኛ በትግራይ ጅቦች አስከሬን እየበሉ መሆናቸው የተሳሳተ ምስልና መረጃ አሰራጭቶ ነበር።

ኢፕድ_አጋልጥ‼️
በሃሰት ዘገባ የኢትዮጵያን ስም የሚያብጠለጥሉ ምዕራባዊያን ሚዲያዎች ሰሞኑንም በዚሁ ተግባራቸው ቀጥለውበታል። ተደጋጋሚ የሀሰት ዘገባ ከሚሰሩ ሚዲያዎች መካከል አንዱ ቢቢሲ ነው።
ቢቢሲ እአአ ኦክቶበር 19 ቀን 2022 ሀሰተኛ ምስል በመጠቀም ጭምር የተለመደውን የውሸት ዘገባ አስነብቧል።
“በኢትዮጵያ ባለው የርስ በርስ ጦርነት ጅቦች የሠው አስከሬን እየበሉ ነው” ሲል ለሰራው የፈጠራ ዘገባ የተጠቀመው ምስልም ሀረር ቱሪስቶች ጅብ ሲመግቡ የተነሳን ምስል ነው። በፎቶግራፉ ላይ በግልጽ እንደሚታየው ቢቢሲ የሀረሩን ፎቶ ሲወስድ የፎቶግራፉ ባለቤት የሆነውን የታዋቂውን ጌቲኢሜጅስ ሎጎ ቆርጦ ትግራይ ውስጥ የተነሳ በማስመሰል ተጠቅሟል።
ቢቢሲ ይህ ቅጥፈቱ ሲጋለጥበት ፎቶውን ቀይሯል፤ ነገር ግን ሀሰተኛው ፎቶግራፍ እንደ ማርቲን ፕላውት ባሉ የአሸባሪው ትህነግ አፈቀላጤዎች ገጽ ላይ በግልጽ ይታያል።
ቢቢሲ ባለፈው አመት ትህነግ በአማራ ክልል ሰፊ አካባቢ ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት በጅቡቲ አንድ ጀነራልን አናግሮ የሰራውን እና የሀገርን ሉአላዊነት የሚዳፈረውን “ዜና” ባልተለመደ ሁኔታ ከድረ ገጹ ላይ ከሶስት ጊዜ በላይ ኤዲት ማድረጉ አይዘነጋም። ኢዜአ

ቢቢሲን ጉያው ውስጥ ይዞ ማስታገስ ያላቻለው መንግስት በበኩሉ “ሲያምራችሁ ይቅር” ሲል በተቆጣጠራቸው ከተሞች አገልግሎት ለማስጀመር፣ ዝግጅቱን ማተናቀቁንና የተደበቀ ዕህል እያወጣ ማደሉንና መንገድ፣ ባቡር፣ የአየር በረራ ስራ በሙላት ለማስጀመር ርብርብ ላይ መሆኑንን እያስታወቀ ነው።

ከትግራይ ለንግግሩ በሚል ሰማንያ የሚሆኑ ሰዎች በመጀመሪያው ጉዞ ከመቀለ እንዲወጡ ታስቦ እንደነበር መረጃ እንዳላቸው የጠቀሱ ሲናገሩ ነበር። ይሁን እንጂ መረጃው በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም። አሁን ላይ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚጓዙት ቁጥራቸው በይፋ ባይታወቅም ዋና ዋና ወታደራዊ አመራሮችና ሙሉ የትህነግ ስራ አስፈጻሚዎች መካተታቸው ታውቋል።

ደብረብርሃንን አሽትቶ ወደ ትግራይ የተመለሰው ትህነግ ” ጦርነቱ አልቋል፣ ከማን ጋር ነው ንግግር የሚደረገው” በሚል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ፣ አለያም አፍንጫ በመያዝ የጎደለበትን በጉልበት ማሳካት እንደሚችል በተደጋጋሚ በመናገር ይታወቃል። የአፍሪካ ህብረትን “ወግድ” ሲል የነበረው ትህነግ “አማራ ወዳጄ፣ ኢትዮጵያ አገሬና ፍቅሬ፣ መግንተልን አስቤው አላውቅም” የሚሉ አዳዲስ ቅኝቶች ማሰማት ጀምሮ አፍሪካ ህብረትን ” አመስግናለሁ” ያለው።

ምንም ይሁን ምን ሰላም እገሌ ከዕገሌ ሳይባል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ የወቅቱ ጥያቄ ነውና በአሸናፊና ተሸናፊ ስሜት ሳይሆን በወንድማማችነት ስሜት ንግግሩ በሚጠበቀው መልኩ እንዲከናወን በርካቶች በጸሎት ጭምር እየማለዱ ነው።

ጦርነቱ ወደፊት ይፋ የሚሆኑ ሰፊና አስደንጋጭ አሃዞችን እስኪያሰማ ድረስ ጉዳቱን የሚያውቁ የደረሰባቸው ናቸውና ሁሉም ወገን የሰላም አማራጭ ንግግሩን በቀናነት በማበረታታት የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የሚወተውቱ ” ለተራ ሳንቲም ለቀማና ለተራ ተቀጣሪነት ብሄር ውስጥ ተውሽቀው ሴራ የሚያመርቱም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ህብን ከህዝብ የሚያቀራርብ ስራ እንዲሰሩ ይገባል” የሚሉ ድምጾችም እየበረከቱ ነው።

Exit mobile version