Site icon ETHIO12.COM

መንግስት በዜጎች ጥበቃና ሰብአዊ እርዳታ እንደማይደራደር ይፋ አደረገ

በየቀኑ አንዳን አንጓ እያነሳ ምላሽ እየሰጠና የንግግሩን አቅጣጫ እያመላከተ ያለው መንግስት ዛሬ እርዳታ ሰጭዎች እንደሚቆጣጠርና እንደ ቀደመው ጊዜ መረን እንደማይለቃቸው አስታውቋል። ቀደም ባሉት ቀናት መንግስት የትግራይን ሕዝብ ከእገታ ማስለቀቅ ዋናው ግቡ እንደሆነና የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ማስጠበቅ የዘመቻው ተግባር እንደሆነ ማስታወቁ አይዘነጋም።

የዜጎች ሰብአዊ እርዳታም ሆነ ጥበቃ ለድርድር እንደማይቀርብ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ያስታወቁት ዛሬ ነው። የመንግስት ሚዲያዎች እንደዘገቡት ሚኒስትሩ ይህ የሚደረገው መንግስት ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱን የመወጣት ግዴታ ስላለበት ብቻ ነው።

ፕሮፌሰር ክንድያ ያልተግደበ እርዳታና መከላከያ ከትግራይ ይውጣ የሚሉትን ነጥቦች እንደሚያነሱ አስታውቀው ነበር። መንግስት ለማንም ምላሽ እንደሰጠ ሳያስታውቅ በሁለቱ ጉዳይ ድርድር ብሎ እነገር እንደሌለ ይፋ አድርጓል። ቀደም ሲልም የአገር መከላከያ በገሪቱ ያሻው ስፍራ መስፈር፣ የአገሪቱን ዳር ድንበር መጠበቀ፣ የፌደራል ንብረቶችን መንከባከብና ደህንነታቸውን መጠበቅ ተፈጥሯዊና ህገመንግስታዊ ስልጣናቸው እንደሆነ ማመልከቱ ይታወሳል።

እንኳን ትግራይን ለቆ ሊወጣ በትግራይ ታግተውብኛል ያላቸውን ዜጎች ሰላማቸውን እንደሚያስጠብቅ የገለጸው መንግስት፣ ትህነግ አቀርበዋለሁ ያለውን የመሰረታዊ አገልግሎቶች ዳግም መጀመር ጉዳይም ” ድርድር አያስፈልገውም እንደ መንግስት ለዜጎቼ ማድረግ የሚገባኝ ተግባሬና ግዴታዬ ነው” በሚል በዚህም ጉዳይ ንትርክ እንደሌለ ይፋ አድርጓል።

ነጻ በወጡ አካባቢዎችና ከተሞች ሕዝብን በማወያየት አስተዳደር እየተከለ መሆኑን ያመልከተው መንግስት ዛሬ ብኮሙኒከሽን ጽህፈት ቤት በኩልን ” የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲሁም የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦትን ለማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን ለመወጣት ቁርጠኛ ነው” ብሏል።

ሚኒስትሩ አክለውም የዜጎች ሰብአዊ እርዳታም ሆነ ጥበቃ ለድርድር እንደማይቀርብ ጠቅሰው፥ በተመሳሳይ የትግራይም ህዝብ ሰብአዊ እርዳታም ሆነ ጥበቃ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም ሲሉ ተድምጠዋል። በሁሉም አካባቢዎች በአስቻጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሁሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማፋጠን መንግስት በትጋት እየሠራ መሆኑንም ግልጽ አድርገዋል።

“በተረጅዎች ስም የሚመጣ የእርዳታ እህልና መድኃኒት በየትኛውም የሽብር ቡድን እንዲዘረፍ መንግስት አይፈቅድም”” ያሉት ሚኒስትሩ “መንግሥት የዕርዳታ ሥርጭቱን ይቆጣጠራል” ሲሉ ቃል በቃል ተናገረዋል። ይህን ማድረግም ህገ-መንግስታዊ ግዴታው እንደሆነ ገልጸዋል። ህገመንግስታዊ የሆነው አሰራር በአገሪቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ያለ ልዩነት እንደሚሰራ በማስጠንቀቂያ መልኩ ገልጸዋል።

እያደር በደቡብ አፍሪካው ንግግር ላይ ትህነግ አቀርበዋለሁ ላለው ጥያቄ መንግስት አቋሙንና አሰራሩን ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ከትሀንግ በኩል በቀጥታ የተባለ ነገር የለም። አወያይ ሆነው የተመደቡትና ስብሰባውን ” የሰላም ንግግር” የሚሉት ክፍሎችም ስብሰባው መጀመሩን ከመናገራቸው ውጪ ዝርዝር ነገር አልተነፈሱም። ንግግሩ እሁድ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Exit mobile version