Site icon ETHIO12.COM

አንድ ጣሳ ማሽላ በ250 ብር በሚሸጥበት አላማጣ ተከማችቶ የነበረ ከ3 ሺሕ ኩንታል በላይ የእርዳታ እህል ተገኘ

በአላማጣ ከተማ አሸባሪው ህወሓት ለታጣቂዎቹ አከማችቶት የነበረው ከ3 ሺሕ ኩንታል በላይ የእርዳታ እህል ተገኝቷል።

አሸባሪውና ወራሪው የወያኔ ቡድን ለራያ አላማጣ ህዝብ የሚመጣውን የእርዳታ እህል ለህዝቡ ሳያደርስ ለታጣቂዎቹ ቀለብ እንዲውል በየ መጋዝኖቹ እና ወፍጮ ቤቶች አከማችቶት መገኘቱን ነው መረጃው ያመለከተው።

ተከማችቶ የተገኘው የእርዳታ እህልም ከ2 ሺሕ 500 ኩንታል በላይ የዩ ኤስ አይዲ የተፈጨ የስንዴ ዱቄት፣ ከ400 ኩንታል በላይ ከረጢት የታሸገ ስንዴ፣ ከ100 ኩንታል በላይ ብስኩቶች እና ኃይል ሰጪ ምግቦች መሆኑም ተገልጿል።

የሽብር ቡድኑ ካለፈው 1 ዓመት ከ4 ወር በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ለሰብዓዊ እርዳታ እንዲውል የሚገባ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ከህዝቡ እየነጠቀ ለታጣቂዎቹ ሲያከማችና ሲቀልብ እንደነበር የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ወይዘሮ ሰዓዳ አደም የአላማጣ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ከሐምሌ/2013 ዓ.ም ጀምሮ ምንም ዓይነት እርዳታ ደርሷቸው እንደማያውቅ ገልፀው ልጆቻቸውን ለመመገብ በችግር እና በእንግልት ማሳለፋቸውን በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው ተናግረዋል።

አገዳ እየሸጡ እና በቆሎ እየጠበሱ በመሸጥ በሚያገኟት ገቢ ለልጆቻቸው እህል በውድ እንደሚሸምቱ የተናገሩት ው/ሮ ሰዓዳ አንድ ጣሳ ማሽላ በ250 ብር ይገዙ እንደነበርም ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ እንኳንስ የእርዳታ እህል ሊሰጠን ቀርቶ ለልጆቻችን ቀለብ በውድ የገዛኋትን ትንሽ ማሽላ አስፈጭቼ ሳላቦካ ዱቄት አምጪ ብለው አስፈራርተው ይወስዱብኛል ብለዋል።

በሌላ በኩል አሸባሪው ህወሓት በመጋዘን አከማችቶ ለተዋጊው ቀለብ ሲጠቀምበት የነበረው ስንዴ ለህዝብ መከፋፈሉ ተገለጸ፡፡

አሸባሪው ህወሓት በሰብአዊ ድጋፍ ስም ወደ ትግራይ ክልል ሲገባ የነበረውን ስንዴ በመጋዘን አከማችቶ ለተዋጊ ሰራዊቱ ቀለብ ሲጠቀምበት የነበረውን 120 ኩንታል ስንዴ የመከላከያ ሰራዊት በመቆጣጠር ለ2 ሺህ 767 አባወራዎችና እማወራዎች አከፋፍሏል፡፡

የዕዙ ስነ-ልቦና ግንባታ ኃላፊ የመከላከያ ሠራዊት የበይ ተመልካች ለነበረው የኮረም ከተማ ነዋሪዎች የዕርዳታ እህል በማደል ለህዝብ ደራሽ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ብለዋል፡፡

ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ የወጡ ነዋሪዎች ሠራዊቱ የህዝቡን ደህንነት በመጠበቅ እና አሸባሪ ቡድኑ ለጦርነት አላማ ሊያውለው የነበረውን የእርዳታ እህል በመከፋፋላቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀዋል።

ነዋሪዎችም ሰራዊቱ ላደረገላቸው በጎ ተግባር ያላቸውን ምስጋና ገልፀው ባሳለፉት ጊዜያት በሽብር ቡድኑ ምክንያት ለረሃብና እንግልት ተጋልጠን ቆይተናል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። (ዋልታ)

Exit mobile version