Site icon ETHIO12.COM

“የመጨረሻው የድል ዋዜማ ላይ ሆነን ሰማዕታትን እየዘከርን ነው”

ነገ የሚዘከረውን የሰሜን ዕዝ ሰማዕታት ቀን ምክንያት በማድረግ የተሰጠ መግለጫ

የሰሜን ዕዝ ሰማዕታትን በመዘከር ታሪካዊ አደራችንን እንወጣለን!!

ኢትዮጵያ በዘመኗ በርካታ ህልውናዋን የሚጋፉ እብሪት የወጠራቸው ሀገራት ወረራ ፈፅመው ጥቅምና ፍላጎታቸውን ለመጫን ተፈታትነዋታል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ጀግና መውለድ ታውቅበታለችና ጀግኖች ልጆቿ ጠላቶቿን በጦርና በጋሻ ተፋልመው እንደአመጣጣቸው በመመለስ ሉአላዊት ሀገር አስረክበውናል።

አሸባሪው ህወሓት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ለ27 አመታት እንደፈለገ በህዝብ ሰብዓዊ መብቶች ላይ ሲረማመድ ቆይቶ ሀገሪቱን ለውድቀት የዳረገ ዘረፋ በማካሔዱና በዚህ ጦስ የነበረውን የፌዴራል መንግስት ሥልጣን በማጣቱ ገና በለውጡ ጅማሬ የህወሓት አመራሮች ሀገራዊ ለውጡን ማጥላላትን ሥራዬ ብለው ተያያዙት።

የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ መቀመጫውን በትግራይ ክልል አድርጎ ከትግራይ ህዝብ ጋር እድሜ ልኩን የኖረ ሠራዊት ነው። ዕዙ በሰውና በመሣሪያ የመከላከያን ከፍተኛ ድርሻ የያዘ የተቋሙ ግዙፍ ኃይል ነበር። ወቅቱ መኸር በመሆኑ ሠራዊቱ የአርሶ አደሩን ሰብል መሰብሰብ እና በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ በማባረር ውሎ አዳሩን ከትግራይ ገበሬ ጋር አድርጓል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ህወሓት ከሰው ልጅ በማይጠበቅ ጭካኔና በአለም መድረክ ባልታዬ ክህደት  ለዘመናት በቀበሮ ጉድጓድ እየኖረ ሲጠብቀው የኖረውን የሰሜን ዕዝ ሠራዊት በተኛበት ጥቃት ከፈተበት። ሀገር እንጠብቅ ህዝብ እናገልግል ያሉ፤ ቀን ገበሬ ሌሊት ጥበቃ ሆነው ለበርካታ አመታት  ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ፣ ቀን ሀሩሩ ሌሊት ብርዱ ሳይበግራቸው፣ ክረምት ከበጋ የሚለፉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በህወሓት የክህደት በትር ሀገር አማን ብለው  በተኙበት ተወጉ።

በዚያ ጥቃት ብዙዎቹ የሰሜን ዕዝ አባላት በግፈኛው የህወሓት ጥቃት ተገደሉ። በቅጡ እንኳ ሳይቀበሩ ጅብና አሞራ በላቸው። በሬሳቸው ላይ ከበሮ እየደለቁ ጨፈሩበት፡፡ ብዙዎቹ እየቆሰሉ አካላቸውን አጡ። እንዲሁም ታፍነው በርሐብና ውኃ ጥም እየተቀጡ ተንገላቱ። እነኝህ ታፋኝ የሰሜን ዕዝ አባላት በግፈኞች ዱላ ተደበደቡ። ተገደሉ። ሴት የሠራዊቱ አባላት በጉልበተኞች ተደፈሩ።

ህወሓት ምንም እንኳ የሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ በብሔር እየመረጠ በርካታ ጓዶችን ይግደል እንጂ በወቅቱ “የራሴ” ለሚላቸው የትግራይ ተወላጆች እንኳ ከመጨከን ወደ ኃላ አላለም። የሰሜን ዕዝን በሚያጠቃበት ወቅት ለሴራው ያልተባበሩትን በርካታ የትግራይ ተወላጅ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት አመራሮችንና አባላትን  ገድሎ የጭካኔውን ጥግ አሳይቶናል።

የሰሜን ዕዝ አባላት ትምህርት ቤት ሠርተው ህፃናት ይማሩ ባሉ፣ ጤና ጣቢያ ሠርተው የእናቶችንና የህፃናትን ሞት እንቀንስ ባሉ፤ የውኃ ጉድጓድ ቆፍረው እናቶችን ከሸክም በገላገሉ የተከፈላቸው ወሮታ የግፈኛው ህወሓት ጥይት ሆነ።

ህወሓት ከሃያ አመታት በላይ ትግራይ ክልል እየኖረ  ከአነስተኛ ደመወዙ ቀንሶ ገንዘብ አዋጥቶ፣ እጁና ትክሻው እስኪላጥ ድንጋይ ፈልጦና ተሸክሞ ትምህርት ቤት፣ ጤና ኬላ፣ የወጣቶች መዝናኛ የገነባ፤  የክረምቱን ጭቃ ሳይጠየፍ የአርሶ አደሩን ሰብል ሲኮተኩት እና ሲያርም ከርሞ፤ ጠዋት ብርዱን ቀን ፀሐዩን ሳይፈራ የደረሰውን ሰብል ሲያጭድ እና ሲወቃ፤ ምሽግ ውስጥ እየኖረ የጠበቀውን፣ የሞተለትንና የቆሰለለትን የሰሜን ዕዝ ሠራዊትን ክዶ የወጋ የጭካኔና የክህደት ጥግ መታወቂያው የሆነ የማፍያዎች ጥርቅም ነው።

አሸባሪው ህወሓት የጥቅምት 24ቱ የሰሜን ዕዝ የክህደት ጥቃት አልበቃው ብሎ ለሌላ ጦርነት ከመሰለፍ ወደ ኃላ አላለም። በ2013 ዓ.ም ሰኔ ወር መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ሠራዊቱን ከትግራይ ባስወጣበት ወቅት በየበርሃው ተበታትኖ የነበረውን ታጣቂውን አሰባስቦ የአፋርና አማራ ክልሎችን በስፋት ወረረ። በዚህ ወረራ ወቅትም አመራሮቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ መሔድ ካለባቸው እንደሚሔዱ እየማሉ ተናገሩ። 

በአማራና አፋር ክልሎች ምንም የማያውቁ ንፁሀን ላይ ከባድ መሣሪያ በመተኮስ እና በጅምላ በመረሸን የጥፋት መሐላቸውን በተግባር አሳዩን። ጭና፣ ጋሊኮማ፣ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ያለርህራሔ ንፁሀን ዜጎችን በጅምላ ገደሉ። ከትልልቅ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እስከ የገበሬው ቤት ድረስ ዘረፉ፤ አወደሙ፤ አቃጠሉ። የአርሶ አደሩን ሰብል አጭደውና ወቅተው ከመውሰድ እስከ በእሳት ማቃጠል የደረሰ ጉዳት አደረሱ። ህሊናቸውን የሸጡ ህወሓታዊያን ከመነኩሴ እስከ ህፃናት ያሉ ሴቶችን አስገድደው ደፈሩ።

የጀመሩት ወረራ በጀግናው ሠራዊታችን ጠንካራ ምት ተፈረካክሶ ከአፋርና አማራ ክልል ተጠራርገው ሲወጡ መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጎ ባለበት ሰአት ነሐሴ 18 ቀን ሦስተኛ ወረራ ከፈቱ።

ደብተር ይዘው ትምህርት ቤት መሔድ ከነበረባቸው ህፃናት እስከ መነኩሴ ድረስ በግድ ወደ ግንባር በማምጣት የትግራይን ህዝብ ለጥይት ማብረጃነት ተጠቀሙበት፡፡  ህወሓት ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች እስከ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመተባበር ወረራ ቢከፍትም የብርቱውን ሠራዊታችንን ክንድ መቋቋም አልቻለም። ትንሽ ድል ሲያገኝ የሚፎክረው፤ ሲሸነፍ ደግሞ የሚያለቅሰው ህወሓት ከኢትዮጵያ ህዝብ በዘረፈው ከፍተኛ ሀብት የውጭ ሀገር ሰዎችን (ሎቢስት) ቀጥሮ ፕሮፓጋንዳ ቢያስነዛም ውጤቱ ኪሳራ ሆኖበታል።

ይህን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮውን ለማሳካትም አንዴ በጦርነት ሌላ ጊዜ ደግሞ በድርድር ጊዜ ሸምቶ ለማገገም ያለመታከት እየሠራ ይገኛል። ግን እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን። በየትኛውም ግንባር እንፈተናለን እንጂ ፈፅሞ አንሸነፍም።

ምንም እንኳ አሸባሪው ህወሓት ቀደም ብሎ በሰሜን ዕዝ ላይ ቀጥሎም በመላው ኢትዮጵያ ላይ የፈፀመው ጥቃትና ወረራ መዘዙ እስከዛሬ ድረስ ዘልቆ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲሁም አለም አቀፍ ጫና ያስከተለ ቢሆንም ሁሉንም በአሸናፊነትና ድል እየተወጣን እንገኛለን።

ከመላው ህዝባችን ጋር ሆነን ባደረግነው ታላቅ ተጋድሎ ህወሓት ራሱ በለኮሰው ጦርነት ሊጠፋ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡ የሰማዕታቱን ፍሬ የምናይበትና ድሉን የምንዘክርበት ወቅት ላይ ነን።

እኛ አደራ የምንዘነጋ ሳንሆን የወንድሞቻችንን፣ የኢትዮጵያን ክብርና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ተጋድሎ ከዳር ለማድረስ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት በጀግንነት ለመክፈል የተዘጋጀን ነን።

አሸባሪው ህወሓት የፈፀመብን በደልና ሰቆቃ ተቆጥሮ የማያልቅ በታሪክና ትውልድ ፊት ይቅርታ የማይቸረው ነው፡፡ በወንድሞቻችን ላይ የደረሰውን ግፍና መከራም መቼም አንረሳውም፡፡ ነገር ግን እኛ እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኃይል ህዝብና ሀገርን አፅንተን የምናስቀጥል ህዝባዊ ሠራዊት ነን፡፡

ስለሆነም በደልን ስንቆጥር የምንኖር ሳንሆን  የኢትዮጵያን ህዝብ በተለይም የትግራይን ህዝብ ከህወሓት የዘመናት ባርነትና ጭቆና ነፃ ለማውጣት የከፈልነውንና እየከፈልን ያለነውን መስዋዕትነት አጠናክረን በመቀጠል የመጨረሻው የድል ዋዜማ ላይ ሆነን ሰማዕታትን እየዘከርን ኢትዮጵያችንን አስከብረን በአሸባሪው ህወሓት መቃብር ላይ ድላችንን እናበስራለን።

“ጥቅምት 24 መቼም አንረሳውም!!”
ክብርና ሞገስ ለተሰው ሰማዕታት!!

Exit mobile version