Site icon ETHIO12.COM

በአዲስ አበባ ቤተመንግስት ሳይሆን የ”ሳተላይት ሲቲ” እንደሚገነባ አብይ አስታወቁ፤ 2ቢልዮን ዶላር ያስገባል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ የሳተላይት ሲቲ እንደሚገነባ በይፋ አስታወቁ። ከ400 እስከ 500 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረገበት ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት “ጫካ ሃውስ” የሚል ስያሜ አለው። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝም አመልክተዋል።

ዛሬ ለተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ማብራሪያ ሲሰጡ ነው አብይ አህመድ የ“ጫካ ሃውስ” ፕሮጀክትን አስመልክቶ የተዛቡ መረጃዎችን ለማጥራት በሚል ያወሱት። እሳቸው ስም ባይጠቅሱም ሪፖርተር ጋዜጣ ነበር “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ49 ቢሊዮን ብር ቤተ መንግስት እየገነቡ ነው” በሚል ምንጮች እንደነገሩት አመልክቶ ዜናውን የበተነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ወሬ” ሲሉ መዛባቱን የጠቆሙትን ፕሮጀክት 49 ቢሊዮን ሳይሆን ከ400 እስከ 500 ቢሊዮን የሚፈጅ ሲሉ ነው የገለጹት።

“ልንገነባ ያሰብንው ‘የጫካ ሃውስ’ ይባላል። ልንገነባ ያሰብንው ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ኩራት የሚሆን ‘ሳተላይት ሲቲ’ ነው። ልንገነባ ያሰብንው የኢትዮጵያን ቤት ነው” በማለት ለምክር ቤቱን ለህዝብ ያስታወቁት አብይ አህመድ “ጊዜ ስጡን ታዩታላችሁ” ሲሉ ቤቱ በጭብጨባ አድናቆቱን ሰጥቷቸዋል።

ፕሮጀክቱ ተራራ ላይ የሚሰራ በመሆኑ እዛ አካባቢ ያሉ ኤምባሲዎች ከላይ እንዳይተዩ ሰግተው አንዳን ምሁራንን እራት ጋብዘው የተቃውሞ ጽሁፍ እንዳጻፏቸው ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ” ጀምረን አናቆምም፤ ልንገራችሁ ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል” ብለዋል። ለኤምባሲዎቹ ስጋት መፍትሄ እንደሚበጅም አመልክተዋል።

እራት በልተው የተቃወሙም “ምሁራን” ሲሉ የጠሯቸውም ሆነ ይህን ፕሮጀክት አንጋዶ የሚመለከት ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ያመልከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፕሮጀክቱ እጅግ ውብና ዘመናዊ ትውልድ የሚኮራበት እንደሆነ አበክረው አስታውቀዋል። የሚሰራው ቤት የኢትዮጵያ በመሆኑ ሲጠናቀቅ የአገር ኩራት እንደሚሆንም ገልጸዋል። አነሰ ቢባል ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገባም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ዘማናዊ ሆቴሎች፣ ሰው ሰራሽ ሃይቆች፣ ዘመናዊ የአይቲና የሳተላይት መንደሮች የሚካተቱበት በመሆኑ ሲጠናቀቅ ከፍተኛ የቱሪስት ሃብት እንደሚሆን መረጃውን አዛብተው ለሚናገሩና ለሚረጩ አስታወቀዋል።

Exit mobile version