Site icon ETHIO12.COM

ከ23 በላይ የመሬት ደላላዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

በህገ ወጥ መንገድ ከፍተኛ መሬት ለግለሰቦች እንዲሰጥ አድርገዋል የተባሉ ከ23 በላይ የመሬት ደላላዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

(የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ህዳር/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ) በአዲስ አበባ እና በክልሎች ከተለያዩ አመራሮች፣ ባለሙያዎች ጋር በመመሳጠር እንዲሁም ለባለስልጣን ሽፋን በመሆን ከፍተኛ መሬት በህገ ወጥ መንገድ ለግለሰቦች እንዲሰጥ አድረገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከ23 በላይ ህገ ወጥ የመሬት ደላላዎች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎቹ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት ነው በዛሬው ዕለት  የቀረቡት።

ተጠርጣሪዎቹ በክልሎችና አዲስ አበባ ከሚገኙ በተለያየ ደረጃ ያሉ የስራ ሃላፊዎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ካርታ በህገ ወጥ መንገድ  በማስወጣት ለግለሰቦች እንዲተላለፍ  ማድረጋቸውን መርማሪ  ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ በተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቂያው አቅርቧል።

በተለይም ከአርሶ አደር ኮሚቴዎች ጋር በመገናኝትና ሀሰተኛ ማስረጃ እንዲያቀርቡ በማድረግ ብዙ ሺህ ካሬ ሜትር ከመሬት ባንክ ውስጥ ወጥቶ ለግለሰቦች እንዲደርስ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የይገባኛል ጥያቄ ተነሰቶባቸው በክርክር ላይ የሚገኙ ቦታዎችን በማጠር ባላቸው ግንኙነት ሐሰተኛ ሰነድ በማቅረብ ጭምር መጠርጠራቸውም ተገልጿል።

የተገኘውንም መሬት ለራሳቸው የወሰዱ በመሆኑ እና ለስራ ሃላፊዎች ሽፋን በመስጠት እንዲወስዱ በማድረግ በህገ ወጥ ድርጊታቸው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ከፍተኛ ሃብት ያካበቱ በመሆኑ በህገ ወጥ የድለላ ስራ ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው በምርመራ ከህዳር 23 እስከ 25 ቀን 2015ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው የተባለው፡፡

Exit mobile version