Site icon ETHIO12.COM

የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ “ጦርነት በቃኝ” ነፍጥ አወረደ

ራሱን የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረም የሰላም እና የልማት ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ተስማምቶ ወደ ሱዳንን ለቆ ወደ ቀዬው ተመለሰ። ይህ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጣና ፎረም ከዶክተር አብይ ጋር ከመከሩና ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን ወደ ካርቱም አቅንተው ከተመለሱ በሁዋላ ነው።

የሱዳን መንግስት የደህንነት ሚኒስትር ከኢትዮጵያ አቻቸው ተመስገን ጥሩነህ ጋር ባደረጉት ይፋዊ ስምምነት መሰረት ውል ሲያስሩ ” ሱዳን ካሁን በሁዋላ የነሱን መሬት ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ሊያጠቃ የሚችል ሃይልን አታስተናግድም” በሚል መናገራቸው ይታወሳል።

በዚሁ ስምምነት መሰረት ይሁን በሌላ አግባብ ይህ ታጣቂ ቡድን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ጋር በሱዳን ካርቱም በደረሱት የሰላም ስምምነት መሠረት ቡድኑ የሰላም አማራጮችን በመከተል ወደ ክልሉ መመለሱን የመንግስትና ሚዲያዎች አስታውቀዋል።

ትህነግ ትጥቁን ለመፍታትና ጥያቄ ካለው መንግስትን አክብሮና ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ወደ ሰላም መንገድ መምጣቱን ተከትሎ የተሰማው ዜና የቤኒሻንጉል ታጣቂ ሃይል በስምምነቱ መሰረት የቡድኑ አባላት ትጥቃቸውን ፈትተው ተሃድሶ በመውሰድ በክልሉ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ላይ ለመሰማራት ወስነው ነፍጥ ማውረዳቸው ታውቋል።

የቡድኑ አባላት ከሱዳን ድንበር ሸርቆሌ ወረዳ ገንገን ቀበሌ ጀምሮ ወደ ክልሉ ሲገቡ በአሶሳ ዞን የሸርቆሌ፣ የመንጌ የሆሞሻ፣ የዑራ፣ የአሶሳ እና የባምባሲ ወረዳ ነዋሪዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ቡድኑ ” ጦርነት በቃኝ” ማለቱ ከሱዳን ጋር የተጀመረው አዲስ ወዳጅነት ውጤታማ መሆኑም ተመልክቷል።

የሰላም አማራጭን ተቀብሎ ወደ ክልሉ ለገባው የቤሕነን አመራሮች እና አባላት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ ማምሻውን አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀሩን ዑመር ጠቁመዋል፡፡

Exit mobile version