Site icon ETHIO12.COM

ሱዳን – በጫጉላ ሰረገላ – “ሳምሪዬ ሳምሩ” አዲሱ ዘፈን ለትህነግ

ቦሰና “አከሲ” ካለች ቆየት ብላ ቤቱን በጭብጨባ ታቀልጠዋለች። ቦሰና ገንፎ ከሰራች ቀውስ አለ። ቦሰና ዝም ብላ “አከሲ” አትልም። ያበደው እንደ ዚፕ ሲገጥማት፣ ቦሰና ትዘፍናለች። የዘፈኑ ስም ” አከሲ” ነው። እልልታም ይታከልበታል። ዋናው ጉዳይ ግን …. ፈገግ አለ …

ኢትዮጵያና ሱዳን ምን እያደረጉ ነው? በፍቅር ሰረገላ፣ የፍቅር ካርታ እየተጫወቱ ጫጉላ ላይ ያሉ ሙሽሮች መስለዋል። ትህነግ ሲተነፍስ ሱዳንም አመሏን አስተካክላለች። ትህነግ ለሰልፍ ማድመቂያ ሳይሆን በውል አቅም አንሶት ሲነደባለል ሱዳን ነቃች። ኢትዮጵያ ጉያ መግባቱ እንደሚያዋጣት አመነች። እናም “ሳምርዬ ሳምሩን …” እየዘፈነች ነው። የዘፈኑ ድምጽ በጣም ሃይለኛ ነው። ድምጹ የማይሰማቸው ለሚከፈላቸው “ተንታኞች” ብቻ ነው። ሳምሩ … ሳምርዬ … ሲያልቅ እንዲህ ነው። የበሻሻ አራዳ ብለው ያጣጣሉት በነጩ ቤት በድል አድራጊነት ሲንጎባለል፣ እነሱ ተንደባለሉ። አራዳ!! ያበደው አዘነ።

ያበደው ለሁሉም የነጮቹ አዲስ ዓመት በጎ እንዲሆን ይመኛል። ትህነግ ጡንቻው ሟምቶ ተራ የክልል ነዋሪ ለመሆን ሳይፈቅድ መንምኖና ሰሎ የተባለውን ሆኗል። አማራጭ የለም። ሶስት ዙር ሰው ገብሯል። ሶስት ዙር አቅራርቷል። አልሆነም። ጥምሩ ጦር አንክቶታል። ዙሪያውን ከቦ ጠብጥቦ “የሰላም ያለህ” አዘፍኖታል። ትቢቱን አራግፎ “ድረርሱልኝ” ሲል ጮዃል። አሁን ትህነግ ስጋት የሚሆንበት ዘመኑ አክትሟሏል። ይህን ለማየት ለጓጓችሁ አዲሱ ዓመት የሰላም ይሁንላችሁ። ይህን በማየታችሁ ያዘናችሁ ለዳግም ፍልሚያ ተደራጁና ሱዳን ግቡ። ሱዳን ውስጥ “ሳምርዬ ሳምሩ” ተከፍቶ ይጠብቃችኋል። ያበደው ወሬ ሲሰማ ይቀባጥራል። ሲናደድ አፉ ይደርቃል። ሲደሰት … ምሱን ፍለጋ ቦሰና ጋር ይሮጣል። ቦሰና ነብሱ ናት።

ሳምሶን ሚኪቻሎቪች ብልጥግና የሚባለው የ “በለጠጉ” ህምምም ያበደው ምጸት አሳየ… ብልጤ ከሚከፍላቸው፣ የደህንነት ሹሙ የማይወራረድ ሃብት ከሚረጩላቸው ሁሉ በላይ ነው። አገሩን ይመክታል። አገሩን የሚወድ ፓትርዮቷ ነው። አስፋውም አለ ተኳሽ። ቅርቃር አዋቂ!! ሌሎችም አሉ። … ግን ምን አገባን። ብልጥግና “የምረጨው ሞልቶኛል ምን አገባቹህ” ቢለንስ? ያበደው ለመለካከፍ እንጂ ሲፈለግ ብልጥግና ቢወደም ባይወድም ሙግቱን በአድራሻ ያደርገዋል። ሌባ ሁላ!!

አብይ አህመድ አቶ ጀማልን ” ሼኩ ጥሩ ልጅ አግኝተው” ሲሉና በዳቦ ቤት ምርቃት ላይ የ”ዳቦ ስም” ሲሰጡ። አብይ በግንባታው ተደስተው እንጂ ራቅ ብለው ገምግመው አይመስልም። ስለ ዳቦ ስሙ … እሳቸውን ለቀቅ አድርገን “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” በሚል ጀማልን “ለማስታወቂያው እንኳን ደስ አለህ? ለማለት እንወዳለን። ቶሎ ማስታወቂያውን ወደ ጅዳ የቁም … እስር ቤት ሳይሆን የቁም ኑሮ ሰፈር እንዲልኩ እንመክራለን። ጀማል ዘይትና ዱቄት አካባቢ አይጠፋምና ወደፊትም በዳቦና ዱቄት ጉዳዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሆኑ ብለን ለመተጠቆምም ። ምክንያቱም ሲኒማ ራስ ከባቢ ምስክራችን ነው።

የዛሬው “የተከበሩ” አቶ ጀማል አዲስ አበባ ስታዲየም ቆሎ እየቃመ ጊዮርጊስን ዳር ዳር ሲል፣ ለሚያውቁ የዳቦ ስሙ አዝናንቷቸዋል። ግን አብነት እንዴት ብለው ይሁን? የኦዳ ልጅ ለብልጽግና የምርጫ ዘመቻ የፊት ተሰላፊ ነበሩ። ሲያልቅ እንዲህ ነው… ያበደው ሳቀ። ለኦዳ ልጅ ጀማል ከባድ ሚዛን ነው። ዲጂታል ነው። በዛ ላይ ደግሞ ይቅር … ለመሆኑ ግን ያ የተነገደበት ጊዮርጊስ ስታዲየሙ አልቆ ይሆን? የአዲስ አበባ የስፖርት ተንተኞች ገና ሳይወጠወጥ ካርታ በስክሪን እያዩ ” በሩ በጸሃይ መግቢያ መሆን አለበት” እያሉ ሸራተን የኩኪስ ግብዣ ላይ ሲላላጡ … አይ ዘመን። ጊዜ በምኞት አጡዘው፣ በምኞት አሳፍረው፣ በምኞት አንሳፈው፣ በምኞት አኑረው፣ ከርሳቸውን በጠላ የሚሞሉ ጯሂዎች መልምለው … የሚያኖሩን የሰው ቀላሎች መጫወቻ አድርጎን ነበር። ገና ያደርገናል። ምን ተይዞ!! ወጠጤዎች የመሪዎቻችን አጫዋችና አማካሪ ሆነዋል። ብዙ አየን … ኤጭ !!

መንግስት ጅሎ ጅሎ፣ ሌብነትን ለመዋጋት የምርመራ ጋዜጠኛነት ስልጠና እየሰጠ ነው ለካ። ያበደው ተወራጨ። ያበደው ዘለለ። አሁን እስቲ መስራት ከተፍለገ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸመውና እየተፈጸመ ላለው ዝርፊያ ምን ምርመራ ያስፈልጋል? ሁሉ ገሃድ፣ ሁሉ ሜዳ ላይ ያለ፣ ነገር ግን … ያበደው ዝም አይነቅዝም አለ። የአዲስ አበባን መሬት የቸበቸበው የሪል እስቴት ሰፈር ግልሙትና በቂ ነው። በማስታወቂያ ስም ግብር እያስገቡ ማን ይነካቸዋል?

ያበደው ሰላምታውን ረስቶ ለፍለፈ።እንደምን ከርማችኋል። በድጋሚ ያበደው ነኝ። ሰላም በያላችሁበት ሳሚ” የሲሪላንካ ዲያስፖራ በሀገሩ ት/ቤትና ጤና ጣቢያ ይሰራል። የእኛ ዲያስፖራ የማያቋርጥ የጠብና ልዩነት አጀንዳ ወደ ሀገር ቤት ይልካል። Negative energy !!!” ሲል የፓኪስታን ዳያስፖራ በአገሩ ተዓመር የሚሰራ እንጂ ለሽብር ሃብቱን የማያፈስ መሆኑንን ያበደው ያየውን መመስከር ወደደ። እንደ አቅማቸው ዱቄት ወደ አገራቸው የሚልኩም አሉ … ቂጫ!!

“አሁን ሰው ለኤርሚያስ ለገሰ እንዴት ብር ይሰጣል?” የቦሰና ጥያቄ ነው። ቦሰና ኤርሚያስን ስታይ ያማታል። ” ገዲቲ” ትላለች። ቆሻሻ ማለቷ ነው። ሃብታሙን ” ከደቱ” ትለዋለች “ለማኝ” ማለቷ ነው። ያበደው እርግጠኛ መሆን ሲፈልግ ቦሰናን ይተነኩሳል። ምክንያታማ ናት። የማርያም ምሩቅ፣ የማሪያም ዲግሪ ያላት አስተዋይ ናት። ባደግ በሰልፍ ዲግሪ ካደላቸው ትልቃለች።

” በ97 ሰለሞንን የመሰል ልጅ አናቱን አፍርሰው ሲገሉት፣ ሰርቆ ነው የተገደለው። ሌቦች ናቸው” እያለ ለድምጻቸው መሰረቅ ለተሰው ኤርሚያስ የሰጠውን ስምና ድፍረት ስታስብ ያዞራታል። ሰለሞን ቤተሰቧ ነው። ሰለሞን ሌባ አልነበረም። ሰለሞን በሌብነት ታምቶ አያውቅም። በመለስ ትዕዛዝ ግንባሩን ተወግቶ አደገበት ሰፈር ወደቀ። የወሬ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኤርሚያስ “ሌባ” አሉት። ውሻው ደጎል እንኳ ኤርሚያን ሲያይ ቤቱን ጥሎ ይወጣል። ወይም ቶሎ እግሩን አንስቶ ይሸናል። በውሽኛ ትርጉሙን ባያብራራም ለቦሰና ግልጽ ነው። “ገዲቲ” የምትለውም ለዚሁ ነው።

ሃብታሙ “መቀመጫዬን ነደሉት” ብሎ ፎቶ እየለጠፈ ሲያለቅስ፣ ሲለምን፣ ሲያስለምን፣ በልመና ሲኖር፣ ለምኖ ቤተሰቡን ሲቀልብ፣ ሁሉም አልገባውም ነበር። ቦሰናም በየዋህነት “ምን አድርገውት ይሁን እኒህ ክፉዎች፣ ደፈሩት፣ በቡድን ይሆን ” እያለች ትነፈርቅለት ነበር። ዛሬ ግን “አታላይ” ትለዋለች። ቦሰና ሃብትሽን ብዙ አውርዳበታለች። ግን ሚስቱና ልጆቹ ሰዎች በመሆናቸው ያበደው ያልፈዋል።

ቦሰና “የከደቱ ልጅ፣ የገዲቲ ልጅ ” የሚባሉ ያሳዝኗታል። የገዳይ ልጅ። የአስገዳይ ልጅ። የተላላኪ ልጅ። የባንዳ ልጅ። የለማኝ ልጅ። የከሃጂ ልጅ … አበሻ ስድብ ይችላል። አንዷ ለቅሶ ቤት ቁጭ ብላ እያስተዛዘነች ሳለ ለካስ መዛበቻ ሆናለች። ውሻ እያስከተለች የምትንከወከወው እብድ ከሰው ሁሉ መካከል መርጣ “ውጪ” ብላ ወረደችባት። ባሏ የለም። ገዳይ ነበር። ለሱ ተረፋት። “ይህቺ ዕብድ አይደለችም” ሃሜቱ መልኩን ቀየረ። የ … ሚስት እያለች በባሏ ሃጢአት ነደፈቻት። በራ ድንኳኑንን ጥላ ወጣች። ቦሰና ይህን ታሪክ ሁሌ ታነሳለች። ቦሰና ሲነሳባት ነበልባል ናት። ሲነሳባት መሸሽ ነው።

ያበደው ነቃ። አሰበ። “ግን ግን” ሲል ጠየቀ። ለነሱ የለፋበትን የሚገብረው ተላላ፣ የቁም ሞት የሞተ … ያበደው አፉ ደረቀ። ለገዳዮች ቃል አቀባይ የሚለግሱ ” አገር ወዳዶች” ምጽ … ምራቁን ተፋባቸው። ያደላቸው አገራት በዜጎቻቸው ትክኖሎጂና ልማት ሲላክላቸው ኢትዮጵያ ጸብ የሚጠምቁ ዲያፖራዎችን አብዝታለች። እዚህ አውሮፓ ለስደት የሚመጡ እህቶችን ቤታቸው አክርመው “ይህን እናደርግልሻለን” በሚል የሚቀባበሉ እንዳሉ የሚያውቁና የደረሰባቸው ያውቁታል። ያበደው አቆረዘዘ። ከአንድ ምስኪን ጋር የተጫወተው ታወሰው። የፖለቲካ ፓርቲ ድጋፍ ደብዳቤ ለማግኘት ከወገብ በታች አምጪ ተብላለች። ብለዋታል። አማራጭ ስለሌለ አድርጋላቸዋለች። ስታያቸው ያማታል። የስደት ምድር መንግስታት!! ለስብሰባ እንጀራና ወጥ የሚመደብባቸው አሉ። ይህ ሁሉ መዋጮና ልዩ ክፍያን አያካትትም። እነዚ ናቸው አማራጭ ሆኖ አገር ለመምራት ሽብር ስፖንሰር የሚያደርጉት። ያበደው ብዙ ጉድ ሰምቷል። አይቷል። ሞራል የት ነው?

እንደው ነገርን ነገር አነሳውና ያበደው ዘላበደ እንጂ ነገሩ የተጀመረው ኢትዮጵያና ሱዳን የጀመሩት ዳንኪራ ወደ ጫጉላ ማደጉ ላይ ነው። ከዚህ ጫጉላ ምንም የማይሸታቸው ሙታን ናቸው። ሱዳን በክልሏ ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያ ላይ ጠብ መንጃ የሚያነሱትን ሁሉ ለማስረከብ ምላለች። ፈርማለች። መፈረም ብቻ ሳይሆን እያደረገች እያሳየች ነው። ደመቀ መኮንን በቅርቡ ካርቱም ደርሰው ከመጡ በሁዋላ የቤኒሻንጉል አማጺዎች ” በቃን” ብለው ከውርደት በፊት አገራቸው ገብተዋል። ጠመንጃ አጋድመው እርሻ ገብተዋል። ቁማናቸው ያማረውን መከላከያ በኢትዮጵያ ቆዳ ሊሰፋቸው ማሰልጠኛ አስገብቷቸዋል።

ሱዳን ሳምሪዎች አሉ። መከላከያና ጥምሩ ጦር ትህነግን አንኩሮ ሲጥለው ሰላም ብሎ ፈረመ። ሱዳን መሽጎ በምስሪዎች/ ግብጾች ቀለብና ትጥቅ ተከታታይ ሙከራ ሲያደርግ የነበረው የትህነግ ክንፍ ሳምሪ እየተወቃ በስደት ሁለተኛ ዓመቱን ሲያከብር ትህነግ “ወገቤን” አለ። ሱዳን ትህነግ እንደማያዋጣትና የገባላትን ቃል እንደማይተግብር ስትረዳ እጀግኖቹ እግር ስር ተደፋች። ሳምሪ ልክ እንደ ቤኒሻንጉል አማጺ ተላልፎ ሊሰጥ ስምምነት ተደረሰ። አብይ አህመድ ጣና ፎረም ላይ እጃቸውን ይዘው በፈገግታ የመዘለጓቸው ጀነራል ሳይውሉ ሳያድሩ ሁሉንም አደረጉ። ጸሃይ ሲጠልቅ እንዲህ ነው። አሁን የሚያዋጣው በልክ ማሰብ ነው። የፌደራሊዝም አስተዳደር ለአብላጮች መገዛት ነው። ሃላፊነትን በልክ መቀበልና የጨዋታውን ህግ አክብሮ መኖር ብቻ ይሆናል። ለሁሉም የሚሰራው ይህ ነው። አብላጫ ስለሆንክ በተረኝነት ስሜት የምታብድም ስከን። ቀስ በል።

ዘገምተኛው ባይደን ለበሻሻው ጀግና “ናልኝ” ብለው ደብዳቤ ጻፉ። ያ ሁሉ ድንፋታና ማስፈራሪያ በኢትዮጵያ መከላከያና በፍትህ አምላክ ውሳኔ ተገለበጠ። ላንቃዋን በረባ ባልረባ ስታላቅቅና መሬታችንን ወራ ስታላግጥ የነበረችው ሱዳን ለሰላም አውርዱ ዘመቻ እጇን ሰጠች። ያበደው የሰማው ዜና ሰሞኑንን ይፋ ይሆናል። ዜናው ባይነገርም በተግባር ሲፈጸም ይታያል። ጦርነት ባህል መሆኑ ቀርቶ ውግዝ እንዲሆን ምዕመናን ጸልዩ። ሰላም ባህላችን፣ ሴራ ጠላታችን …. ዳቦ ቤት !! መቀለ ትህነግ ሃያ ሰባት ዓመት ያልገነባው ዳቦ ቤት በቅርቡ ይቆማል። የቱሪስት ሰፈር ይሰራል። ተረባርበን ትግራይን እናንጻለን!! ያበደው ተስፋው ታደሰ። ልቡናው በራለት። ቦሰና ታወሰችው። የደጎል ፍቅር መጣበት። የአማራና የኦሮሞ ሸኔዎችን መመሳሰል እየመረመረ ደጁ ደረሰ። ቦሰና ገንፎ ሰርታለች። ነገር አለ። ቦሰና ገንፎ ከሰራች ተከታይ ገንፎ አለ።

አሁን ከቦሰና ጋር ነኝ። ቦሰና ችድ ናት። ጠረኗ ውብ ነው። ጥፍር ድረስ ትነዝራለች። ” አከሲ” ማለት ታበዛለች። የቦሰና ዓይነት ጥቂት ናቸው። ያበደው ታድሏል። ቦሰና ቦሰናዬ ” ሳምሩ ሳምርዬ” ሁለት ዜማ የተለያየ ትርጉም። እሰይይ የሚል ድምጽ… አከሲ!! ጭብጨባ፤ የማያቋርጥ እልልታ!! ሰላም ሰንብቱ። ጀማል ማስታወቂያውን አደራ!!

– በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/zagol_news

Exit mobile version