ETHIO12.COM

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አባል ነን ብለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ

ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት አባል ነን በማለት ኅብረተሰቡን እያጭበረበሩ በሚገኙ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ እንዳስታወቀው ፣ ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት የደኅንነትና የሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት አባል ነን የሚሉ ግለሰቦችን በተመለከተ በተለያዩ መንገዶች ክትትል ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በዚህ የማጭበርበሪያ ስልት የሚጠቀሙ አካላት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል ነው ያለው፡፡

ሰሞኑን በተደረጉ ጥብቅ ክትትሎችም ፈለቀ ዴብሳ ደማ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02፣ አስፋው አዳማ ሙታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01፣ ሳምሶን ገነነ መንገሻ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5፣ ተስፋ ሀተው ገምቴሳ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ሰበታ ክፍለ ከተማ፣ ዮሰን በቀለ ትክሳ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ክፍለ ከተማ ሐሰተኛ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን መታወቂያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

የሌሎች መንግሥታዊ ተቋማትንም ሐሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም ለሕገወጥ ድርጊት የሚያውሉ ግለሰቦች በጸጥታ አካላት የተቀናጀ ሥምሪት ተይዘዋል ብሏል፡፡

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱንና የሌሎችን ተቋማት መታወቂያ አስመስለው በማሠማራት የሚጠቀሙ ግለሰቦች መንግሥት የጀመረውን የጸረ ሙስና ትግል ተከትሎ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ጭምር ለማደናቀፍ ያለሙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ኅብረተሰቡ የመንግሥታዊ ተቋማት አባል ነን በማለት በሐሰተኛ መታወቂያ የማጭበርበር ድርጊት ለመፈጸም ከሚሞክሩ ግለሰቦች ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በ910 ነፃ የስልክ መስመር እና Info@niss.gov.et በሚለው የኢሜይል አድራሻ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም በ816 እና 987 ነፃ የስልክ መስመር ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ነው የተመላከተው፡፡ ዜናው ከአማራ ሚዲያ የተወሰደ ነው

Exit mobile version