ETHIO12.COM

መዐዛ አሸናፊና ” በቃኝ”?

ፍርድ ቤቶች በከፍተኛ ወንጀልና ህዝብ በሚያውቀው ደረጃ ጥፋት የፈጸሙ አካላትን በሚገርም ድፍረት ከእስር ሲልቅ በተደጋጋሚ ተወቅሷል። የመርማሪ ፖሊስ ድክመትና ክሱን የሚያደራጁት አካላት ጉዳይ እንዳለ ሆኑ፣ ፍርድ ቤቶች ዋስትና ለማይገባቸው ዋስታና ሲፈቅዱ፣ በአገር ክህደትና ወነጀል ሳይቀር በገሃድ ለሚወነጀሉ እፎያታ ሲያደርጉ ሰፊ ትዝብት እየተሰነዘረ ነው። ከዚህም በላይ ዳኝነቱ እንኳን ሪፎርም አድርጎ ነበስ ሊዘራ ሌብነት ቤቱን እንደሰራበት ማስረጃ ሲቀርበብት እንጂ በሌላ በጎ ጉዳይ አይነሳም። በበርካታ ጉዳዮች የሚታማውን ይህን ድርጅት የሚመሩት ወ/ሮ መዐዛና ምክትላቸው ድንገት “በቃን” ማለታቸው ግርታን የፈጠረው ለዚህ ይመስላል። “በቃችሁ?” ተብለው እንደሆነ አፋቸውን ሞልተው የተናገሩም ተሰምተዋል።

ይህ ተገልጾለት የተወካዮች ምክር ቤት በቀረበለት ምክረ ሃሳብ መሰረት ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ምህረትን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ ወ/ሮ አበባ እምቢአለን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ በምትካቸው መሾሙን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባካሄደው ስብሰባ ነው ውሳኔው የተላለፈው።

ተሰናባቿ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊና ምክትል ፕሬዚዳንቱ በእራሳቸው ፈቃድ ሥራቸውን እንደለቀቁ ለምክር ቤቱ ተነግሮታል። እሳቸውም ሆኑ ምክትላቸው በአካል ይህን ሲሉ ግን አልተሰማም። በዳኝነት ረገድ ሌብነትና ከባድ ወነጀል የፈጸሙ በዋስና በቀላል ፍርድ እንዲለቀቁ መደረጉ፣ እንዲሁም እሳቸውም ሆኑ ምክትላቸው በሚፈለገው ደረጃ ሪፎርም መተግበር እንዳልቻሉ ተዘርዝሮ መወቀሳቸው ግን ቀድሞ ተሰምቶ ነበር። በተለይም ይህንኑ ድክመታቸውን አስመልክቶ ከዋልታው ስሜነህ ባይፈርስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በዛ ደረጃ ሲዝረበረቡ ላየ ” በቃችሁ” እንደሚባሉ ግልጽ ነበር።

ይህም ሆኖ ወ/ሮ መዐዛ የበቃኝ ድብዳቤ ማስገባታቸው ቢገለጽም ከፓርላማ ዝርዝር መረጃ እንዲሰጣቸው ተጠይቋል። አዲሱን ምትካቸውን ሶስት ድምጽ የነፈጉት ወገኖች ከጎጃም መወለዳቸው ለተገለጸው አዲሷ ምክትል ፕሬዚዳንት ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ወ/ሮ አበባ፤ በፌደራል ስነምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአቃቤ ህግነትም ሰርተዋል። በ1999 ዓ.ም የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ተቀላቅለውም ለዘጠኝ ዓመታት የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው አገልግለዋል። ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት መስራታቸው ሲገለጽ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነት በዕጩነት የቀረቡትን የአቶ ቴዎድሮስን ሹመት ነው።  በህግ ትምህርት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያገኙት አቶ ቴዎድሮስ፤ በተማሩበት ዩኒቨርስቲ ለሁለት ዓመት ገደማ የህግ አገልግሎት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። በኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ በነገረ ፈጅነት እና በአቢሲኒያ ባንክ በከፍተኛ ነገረ ፈጅነት የሰሩት አቶ ቴዎድሮስ፤ የብርሃን ኢንሹራንስ የቦርድ ሰብሳቢ ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በምትኩ ሹመት ለመስጠት በዕጩነት ያቀረቧቸውን ባለሙያዎች ምክር ቤቱ እንዲያጸድቅ ሲጠየቅ የዃላ ታሪካቸውና የታጩበት ምክንያት ቀርቦ ነበር።

በዚህ መሠረት ምክር ቤቱ በዕጩነት የቀረቡለትን ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ምህረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን ተቀብሎ በሦስት ድምፀ ተአቅቦ አጽድቋል። ተአቅቦ ያደረጉት ክፍሎች ለታእቅቦ ያነሳሳቸውን ምክንያት እንደተለመደው አላስታወቁም።

ለዋና ፕሬዚዳንት ተአቅቦ የአደረጉትን ጨምሮ ወ/ሮ አበባ እምቢአለ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን ምክርቤቱ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ቀደም ሲል ተአቅቦ ያደረጉት ለምክትል ፕሬዚዳንትነት የቀረቡትን ዕጩ የደገፉት ከአማራ ክልል በመወከላቸው መሆኑ ግን ተሰምቷል። ይህን የተከታተሉ ” ሁለቱንም ያቀረበው ብልጽግና ነው። ብሄር እየለዩ ያለ በቂ ምክንያት ድጋፍና ተቃውሞ ማሰማት አሳዛኝና የማይጠበቅ ነው” ሲሉ እንዲህ ያለው አካሄድ ወደፊት ቡድንተኛነትን ሊያነግስ እንደሚችል አመልክተዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ምህረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያገለገሉ መሆናቸውንና በግል ጥብቅናና የሕግ ማማከር አገልግሎት ለሀገር ውስጥና ለውጭ አገራት ተቋማት አገልግሎት የሰጡ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪ ለተለያዩ ባንኮች በነገረ ፈጅነት የሠሩና የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያዎች ማህበርን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ መሆናቸው ተመላክተቷል።

ወይዘሮ አበባ እምቢአለ በበኩላቸው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት መሥራታቸው ተገልጿል።

ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ምህረትና ወይዘሮ አበባ እምቢአለ በምክር ቤቱ ቀርበው ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።

ለዜናው ማሟያ የተወሰኑ አሳቦች ከጌትነት ተስፋማርያም ሪፖርት ላይ ተውሰናል።

Exit mobile version