Site icon ETHIO12.COM

ሃያ አንድ አምባሳደሮች ተሾሙ፤ ” ከፈተና በሁዋላ … ተነቃቅተናል”

ተሿሚ አምባሳደሮች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ የማስቀጠል ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አስገነዘቡ።

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በቅርቡ ለተሾሙ 14 ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደሮች እና 7 አምባሳደሮች በብሔራዊ ቤተ መንግስት በተካሄደ ስነ-ስርዓት የሹመት ደብዳቤ ሰጥተዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

“ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ሀገራት ለማገልገል በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፤ አገርን በከፍተኛ ቦታ በቅንነት ለማገልገል መታጨት ከፍተኛ እድል ነው ብለዋል” ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ።

ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ካሳለፈችው ፈተና በመውጣት በተስፋ ጎዳና ትገኛለች ያሉት ፕሬዝዳንቷ እየተካሄዱ የሚገኙ የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ስራዎችን በመደገፍ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ ማስቀጠል ከተሿሚ አምባሳደሮች እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ፈተና ውስጥ በገባችበት ወቅት ብሔራዊ ጥቅሟን አስጠብቀው ማስቀጠል የቻሉ ጀግና ልጆች እንዳሏት ለዓለም አሳይታለች፤ ተሿሚ አምባሳደሮቿም ይህንኑ ውጤታማ ተግባር ማስቀጠል እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በፈተና እና ተስፋ ውስጥ መቆየቷን አስታውሰዋል።

ተሿሚ አምባሳደሮች በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ የመጣውን የዲፕሎማሲ ስራ ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ ቀጣይነት ያለው ሆኖ እንዲዘልቅ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ ተሿሚ አምባሳደሮች በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ አማካኝነት ቃለ-መሐላ ፈጽመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version