Site icon ETHIO12.COM

የሽብር ወንጀል ተግባር በኢትዮጵያ ህግ

መግቢያ

በአለም አቀፍ ደረጃ ስለሽብር ሽብር የሚለው ቃል የታወቀው በፈረንሳይ አብዮት ከ1993 እና 1994 አ.ም አካባቢ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ የቅርብ የነበረው ክስተት እንኳን ብናነሳ በ2001 ዓ.ም በአሜሪካ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ዓለም አቀፍ ተቋማትንም ሆነ አገራት በሽብርተኝነት ላይ ያላቸውን አቋም እንዲፈትሹ እና ጠንካራ የህግ ማስፈጸም ስራ እንዲያከናውኑ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ክስተት አገራት ድርጊቱን ወደ መከላከል ስትራቴጂ እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤትም የሽብር መከላከል ትኩረቱን ሁሉን አቀፍ የሽብር ወንጀል መካለከል ላይ እንዲያተኮር፣ ሽብር የዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ስጋት እንደሆነ በመቀበል ሁሉም አባል አገራት ድርጊቱን ወንጀል በማድረግ እንዲደነግጉ እና የህግ ማስፈጸም ስርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ አቅጣጫ በማስቀመጡ በተለይ አባል ሀገራት ሽብር ህግ እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል፡፡

የሽብር ወንጀል ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች (Transnational Organized Crime) ከሚባሉት ዉስጥ አንዱ እንደመሆኑ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያሉ የህግ ምእቀፎች ሽብርተኝነትን በበቂ ሁኔታ በሚከላለከልና መቆጣጠር በሚያስችል መልኩ ጠንካራ የህግ ምእቀፍ በማስፈለጉ የቀድሞው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 በወጣበት ወቅቱ የነበረውን ነባራዊ ክስቶችን ለመሸፈን ባለማስቻሉ አዲስ ህግ መውጣት አስፈልጓል፡፡ በዚህም ምክንያት አዲሱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ተሻሽሎ ሊወጣ ችሏል፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ የሽብር ወንጀል ምን ነት፣ የሽብር ተግባራት ምን ምን እንደሆኑ እና የወንጀል ተጠያቂነት በኢትዮጵያ ህግ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

የሽብር ወንጀል ምንነት

የሽብር ወንጀል ምን እንደሆነ ለማወቅ አዲሱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 መሰረት ሽብር ከሚለውን ቃል ይልቅ የሽብር ድርጊት (ወንጀል) ምንነትን በመዘርዘር የገለፀ ሲሆን ይኸውም ማንኛውም ሰው (ግለሰብ ወይም ቡድን) የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ በሚል በሰው ወይም በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ መሆኑ ተገልፆል፡፡ ይኸውም በዚህ አዋጅ አንቀፅ 3 ላይ እንደተገለጸው የሽብር ድርጊት የሚገለጠው በዓላማው ነዉ፡፡ ይህም ዓለማዉ ሁለት ሲሆን እነሱም 1ኛ. የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ እና 2ኛ. ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን የማስገደድ አላማ የያዘ ነው።

የሽብር ተግባራት እና የወንጀል ተጠያቂነት

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ 1176/2012 አንቀጽ 3 መሰረት የሽብር ወንጀል ተግባራት ማንኛውም ሰው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ፡-

በአዋጁ ከአንቀጽ 3 ውጭ ያሉ የሽብር ወንጀሎች፡-

 መዛት፡- በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 5 መሰረት ከላይ በአንቀፅ 3 ስር የተገለፀውን የሽብር ወንጀል ለመፈፀም መዛት ከአንድ ዓመት እስከ አምስት አመት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ተግባር እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ዛቻ የፈጸመው ሰው አደርገዋለሁ ያለውን ድርጊት ለማድረግ ለመፈጸም ያለው አቅም፣ ዕድል ወይም በሌላ ሰው የሚያስደርግ ከሆነ ይህንን ለማድረግ አቅም ያለው መሆኑ ወይም በመዛቱ ምክንያት ህብረተሰቡ ወይም የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል የተሸበረ ወይም ሽብር ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በመመዘን ነው፡፡

 ማቀድና መሰናዳት- የሽብር ድርጊትን ለመፈጸም ማቀድና ማሰናዳት በራሱ የሚያስቀጣ ተግባር ሲሆን በሁለቱ መካከል ግልጽ ወሰን ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ የአዋጅ ቁጥር 1176/2012 ዓ.ም አንቀጽ 6 በአዋጁ አንቀጽ 3 የተመለከተውን ድርጊት ለመፈጸም ማቀድና መሰናዳት የሚያስቀጣ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ድንጋጌው የማቀድ ተግባር ከሶስት እስከ ሰባት ዓመት እስር እንደሚያስቀጣ እንዲሁም መሰናዳት ተግባር ከአምስት እስከ አስራ ሁለት ዓመት የሚያስቀጣ ስለመሆኑ ያስቀምጣል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 6 ማቀድ ማለት በአዋጁ አንቀጽ 3 የተመለከተውን የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ከሀሳብ ባለፈ ወንጀሉን ለመፈጸም የሚፈጸምበትን ሁኔታ፣ ቦታ፣ ጊዜ ወይም መሰል ጉዳዮችን የመለየት ወይም የመወሰን ጉዳይ እንደሆነ ትርጉም ያስቀምጣል፡፡

 ማደም ማለት ሁለትና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም የተስማሙ እንደሆነ ስለመሆኑ በ1996 አ.ም ከወጣው የወንጀል ህግ አንቀጽ 38 ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡ በአዋጁ የሽብር ወንጀልን ለመፈጸም ማደም ከአምስት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት እስር ድረስ ሊያስቀጣ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ማደም ከማቀድ እና መሰናዳት ለየት የሚያደርገው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ሁለትና ከዛ በላይ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሰዎች ድርጊቱን ለመፈጸም የተስማሙ መሆኑን የሚጠይቅ ነው፡፡ ስምምነት መኖሩ በማስረጃ መረጋገጥ ያለበት ሲሆን በግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ በሰዎቹ መካከል ስምምነት ለመኖሩ የሚያስረዳ ሁኔታ ካለ አድማ ስለመኖሩ ለማረጋገጥ በቂ ይሆናል፡፡

 በሐሰት ማስፈራራት- በሽብር ድርጊት በሀሰት ማስፈራራት በቀላል እስራት ወይም ጉዳት ያስከተለ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 8 ላይ ተደንግጓል፡፡ በሀሰት ማስፈራራት በሽብር ህግ ውስጥ እንዲካተት የተደረገበት ዋና ምክንያት ሰዎች በዘፈቀደ የሽብር ጥቃት እንደሚያደርሱ በመግለጽም ሆነ በማስመሰል ዜጎችን ለስጋት እንዳያጋልጡ ማድረግ ነው፡፡

 ድጋፍ ማድረግ፡- ወንጀሉን የሚፈፅም ሰው መርዳት ከሰባት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ድርጊት ሆኖ በአዋጁ አንቀጽ 9 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የድጋፍ ዓይነቶችን ስንመለከት የሽብር ወንጀል አፈጻጸምን ለመርዳት በማሰብ ሰነድ ወይም መረጃ ማዘጋጀት፣ ማቅረብ፣ መስጠት፣ የምክር አገልግሎት፣ የሙያ ድጋፍ፣ ጉዳት ማድረስ የሚችሉ መሳሪያ፣ ኬሚካሎች ወይም ንጥረ-ነገሮች ያዘጋጀ፣ ያቀረበ የሰጠ ወይም የሸጠ ድጋፍ እንዳደረገ ይወሰዳል፡፡

 ማነሳሳት፡- አንድ ሰው ሌላው ሰው የሽብር ድርጊት እንዲፈጽም ለማድረግ በመጎትጎት፣ ተስፋ በመስጠት፣ በገንዘብ፣ በስጦታ፣ በማስፈራራት ወይም በማናቸውም ሌላ መሰል ዘዴ ያነሳሳ እንደሆነ ለድርጊቱ በአንቀጽ 3 ላይ በተቀመጠው ቅጣት እንደሚቀጣ በአንቀጽ 10(1) ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ድጋፍ ከማድረግ የሚለየው ድርጊቱን የሚፈጽመው ሰው በራሱ ፍላጎት የሚፈጽመው ሳይሆን ማነሳሳት በፈጸመው ሰው ምክንያት ሲሆን ድጋፍ ማድረግ ደግሞ ወንጀል አድራጊው ሀሳብ ያለው ሆኖ ድጋፍ የሚያደርገው ሰው የድርጊቱ ፈጻሚ ሀሳቡን እንዲያሳካ ማመቻቸት ወይም አስተዋጽዎ ማበርከትን የሚመለከት ነው፡፡ ከነዚህ ወንጀሎች እና ቅጣቶች በተጨማሪ ከሽብር ወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት መሆኑን እያወቀ ንብረቱን ይዞ የተገኘ ወይም የተገለገለበት ማንኛውም ሰዉ የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት ይቀጣል፡፡ እንዲሁም ይህ ድርጊት የተፈጸመው በቸልተኝነት እንደሆነ ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ የሽብር ወንጀል ከፍተኛ የአካል፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ቀውስን እና ሌሎች ጉዳቶችን የሚያስከትል አስከፊ ድርጊት ነው፡፡ የፍትህ አካላት፣ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ወንጀልን በመከላከልና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለህግ እንዲቀርቡ ከፍተኛ እገዛ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡

በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና የተዘጋጀ ministry of justice

Exit mobile version