ETHIO12.COM

“የመስዋዕትነት ሰልፍ” የተባለ አድማ ተጠራ “እሁድ ቤተመንግስት ይወረር”

"ቤተ መንግስት አንበሶች ስላሉ በተቃውሞ ሲገባ እንዳይደነብሩና ነብስ እንዳያጠፉ ጥንቃቄ ይደረግ" ሲል በማህበራዊ ገጽ ያሰፈረን ሰው አሳብ ለማካተት ብቻ የተለጠፈ ነው። ምስል አንድነት ፓርክ፤

ይህ ለውጥ እውን ከሆነ በሁዋላ ሕዝብን ስሜታዊ የሚያደረጉ ተግባራት ናቸው በቅስቀሳ መልኩ የሚሰራጩት። ሰው ይገደልና ይሰቀላል። ተሰቅሎ ሲወገር ፊልም ይቀረጻል። ወዲያው ለህዝብ ላይቭ ይለቀቃል።

“እኔ ከገሌ ብሄር አልተወለድኩም በል” እየተባለ ሰው በማንነቱ ሲገደል የሚያሳይ ፊልም በቅጽበት አየር ላይ እንዲውልና በብርሃን ፍጥነት እንዲሰራጭ ይደረጋል።

ንጹሃን እንዲታገቱ ይደረግና እገታው በሚፈለገው መንገድ ተቀነባብሮ በማህበራዊ ሚዲያ እንዲጎን ይደረጋል።

ነበሰጡር ስትሞት፣ ህጻን እያየ አባት ሲገደል፣ ንብረት ሲቃጠልና ሌሎች ባሟችና በሚወድመው ንብረት ሲዛበቱ የሚያሳይ ምስል በተቀናበረ ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያዎች ይጦዛል። ይህ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በማራ፣ አፋር … ሆኗል። አሁን ደግሞ መልኩን ቀይሮ እየሆነ ነው። ሲሆን ንጽሃን ላይ የደረሰን ጉዳት ለፖለቲካ ገበያ ለማዋል ታስቦ ሲሆን፣ አንድም ሆነ ተብሎ ጉዳቱ እንዲደርስ ሴራ ይጠነሰሳል፤ ሴራውን ፈጻሚና አስፈሳሚ የቀተራሉ። በጀት መዳቢዎቹ ሚዲያዎችንም ያካትታሉ። በግብስብስ በተከፈቱ የቁጭ በሉ ስሞች ድራማው ይረጫል። ህዝብ በሚያየው ተቃጥሎ ስሜት ውስጥ ይገባል። ስሜት ውስጥ የሚገቡ ማሰብ ያቆማሉ። ማሰብ ባቆሙት አማካይነት የሚፈለገው የወቅቱ አጀንዳ ይፈጸማል።

ዛሬ ቃለት ሳይመረጥ ” ቤተመንግስት ክበብ፣ ቤተመንግስት ውረር፣ ቤተመንግስት ገብተህ ንቀል” የሚባለው እምነት ላይ የተንጠለጠለ ” የቅዱስ ሲኖዶስ የሰማእትነት ጥሪ” አዝማቾቹ አባቶቹ ላይ “እንዳትወያዩ፣ እንዳትነጋገሩ” በሚል ጫና እያደረጉ እየቆሰቆሱት ነው።

በስመ ነጻ ሚዲያ የሚደረገው ይህ የአመጽ ጥሪ ሁሉንም ዓይነት አማራጭ ተከትሎ በኪሳራ ሲቋጭ አስቀድሞ የሞከረው ሙስሊሞችን ነበር። የሙስሊሞች በር ሲዘጋ፣ መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ህዝብና በርካታ ዕምነት ባለበት አገር “አንድ እምነት፣ አንድ ቤተክርስቲያን፣ አንድ ጳጳስ፣…” በሚለው ለስምምነት የማይበጅ፣ ለዘመኑ የማይመጥን፣ ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ዘመቻ በታሪካዊቷ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስም ተከፍተ። ይህ ዘመቻ የመጨረሻው ካርድ ባለው ከፍተኛ በጀት እየታገዘ ያገኝውን ሁሉ አዝማች፣ አጋፋሪ፣ አውራጅና ጫኝ፣ ተቆርቋሪና አልቃሽ … አድርጎ “ለጠቅላይ” እንጫወት እያለ ነው።

በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ ካሉት አባቶች አንዳንዶቹ ለቅሰቀሳ በሚጋበዙባቸው ሚዲያዎች ” አንወያይም አላልንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያወያዩን እንፈልጋለን፤ ጥላቻ ሃጤያት ነው። መሰዋት ፍቅር ከሌለበት ዋጋ የለውም” ሲሉ የሰሙ፣ ሲኖዶሱ በተወሰኑ ክፍሎች ጫና ስር ስለመውደቁ ማሳያ እንደሆነና አድሮ ሌላ ጣጣ እንደሚያመጣ ይገልጻሉ። ሌሎች ደግሞ “እጅግ ያከረሩና የመንፈሳዊነት ጠረን የሌላቸው” መኖራቸውን ጠቅሰው ልዩነት መኖሩን ያመልክታሉ። እነዚህ ክፍሎች “አፈንጋጭ” ከሚባሉት ወገን ሆነው ያልተገባ ድርጊት እንዲፈጠር የሚሰሩ መኖራቸውን ያክላሉ። በፖለቲካው አመራር ውስጥም አብረዋቸው ያሉ መስለው ባለተገባ መንገድ ልዩነቱን የሚያከሩ ካድሬዎች ስለመኖራቸው አይጠራጠሩም።

የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ከፍተና ግፍ ይፈጸምበት እንደነበረ ” ሰው ይሸጥበታል” በሚል ሰሞኑንን የገለጹ፣ ጸቡ የሃብት ቅርምትና የሌብነትም እንደሆነ ሰሞኑን ቃለ ምልልስ ሰጥተው የተናገሩ አሁንም በስራ ላይ ያሉ ምስክሮች ተሰምተዋል።

አዲስ አበባ አገር ስብከት ገቢው ከፍተኛ በመሆኑ፣ ውዝግብ፣ ሽኩቻ የሚበዛበት ሆኖ መቆየቱን የመሰከሩት እንደሚሉት ከሆነ በሲኖዶስ ውስጥ ከበድ ያለ ገቢ ባለበት አቅጣጫ ለመሰለፍ እጅ መንሻው ለጉድ ነው።

በዚህ ሁሉ የቅድስና ትብትብ ውስጥ ያለችውና የአምልኮ አጸዷ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቸርችሮ ጸዳሏን በሚገፏት የተከበበችው ቤተክርስቲያን ለዚህ ሁሉ የተዳረገችው በሯን ለመዝጋት የሚያስችል ጽዳት ያላቸው መሪዎች ስለሌሏት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል።

ከውስን ደጋግ አባቶች በስተቀር ጥቅም ላይ የተንጠለጠሉት ወገኖች ራሳቸውን ሳይሆን ቤተክርስቲያንንም ባልተገባ ስፍራ እንድትሆን አድርገዋታል። ነብሳቸውን ይማረውና አለቃ አያሌው ” እንኳንም አይኔ አሳወርከኝ። አመስግንሃለሁ” ሲሉ በህይወት ዘመናቸው ዮሃንስ ወልደነጎድጓድ ቤተክርስቲያን ንግስ ላይ ሲያስተምሩ እያለቀሱ ” እኔ በምሰማው ልፈነዳ ደርሻለሁ። እናንተ ከመስማትም አልፎ እያያችሁ እንዴት ቻላችሁት” ሲሉ ስለ መቆሸሽ አስተምረው እንደነበር የሚያስታውሱ፣ ሲኖዶስ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ “ቤተመንግስት ውረሩ፣ የሰማዕት ሞት ሙቱ” በሚል የስልጣን ጥማት ያሰከራቸው ክፍሎች ለሚያራግቡት እልቂት ጋባዥ ፉከራ ተላቀው ራሳቸው እንዲመለከቱ ይመክራሉ።

መንግስትም ዕልህ መጋባቱን ትቶ በሆደ ሰፊነት ልቅ የሆኑትን በማረቅ ቤተክርስቲያኒቱ ባላት ደንብና መተዳደሪያ መሰረት ችግሯን እንድትፈታ ሚናውን እንዲጫወት በርካቶች እየጠየቁ ነው። የዓመጽ ጥሪውን ንቆ፣ ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ባስቸኳይ በመፈለግ ዕልባት እንዲገኝ ሊፈጥን እንደሚገባው የሚያሳስቡ ወገኖች መንግስት ውስጥ ያለው መዥጎርጎር ሊታረም እንደሚገባው አመልክተዋል።

ይህንን ልዩነትና ወይም አለመግባባት ተንተርሶ “አርቲስት ነን፣ ኮባ ለፍላፊ ነን፣ ማስታወቂያ ሰራተኛ ነን፣ የባንክ ካሸር ነን፣ የዩቲዩብ ተከፋይ ነን… ” እያሉ ከየስርቻው እየተጠራሩ “ግፋ በለው” የሚሉ በማያተርፉበት ጨዋታ ዝም ብለው ነገር ማንቀርቀባቸው ጊዜው የመረጃ ዘመን ነውና የከፋ ነገር ቢከሰት አብረው ሲጠቀሱ ከመኖር የዘለለ ጥቅም አያስገኝላቸውምና ቢተውት የሚሉ አሉ።

” ተጸእኖ ፈጣሪ ነን” ብለው ራሳቸውን የቆለሉ ጥቁር ለብሰው ” ሃዋሪያዊ የፖለቲካ መመሪያ” ሲሰጡ ” አብዛኛ” የሚባሉ አድፋጮች ለፈገግታ እንደሚጠቀሙባቸው፣ በተለይ ውጭ ያሉትን ” ሻሸመኔ ናና ተሰዋ” ሲልም በማህበራዊ ሚዲያ የተሳለቁባቸው ጥቂት አይደሉም። አንዳችም የማህበረሰብ ስራና ጥቅም ላይ ፈጠራቸውን ያላኖሩ፣ የማኖር ብቃትም የሌላቸው፣ አገር በተወረችበት ወቅት ቤት ዘግተው ሃድራ ሲያሞቁ የነበሩ፣ ዛሬ ወጥተው ምስኪን መእመናን ወደ እሳት ለመንዳት ሲነደፋደፉ ማየት እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ የሚገልጹ ” ኢትዮጵያ የተሰራችበትን ውቅሯን ለሚረዳና የክልሎችን ህገመንግስታዊ አቅም የሚያውቁ በዚህ መልኩ መንግስትን ለመናድ ማሰባቸው መጨረሻው ሃዘን እንደሚሆን ይወቁት” እያሉ ነው።

ምስል – አንበሶች “ቤተ መንግስት አንበሶች ስላሉ በተቃውሞ ሲገባ እንዳይደነብሩና ነብስ እንዳያጠፉ ጥንቃቄ ይደረግ” ሲል በማህበራዊ ገጽ ያሰፈረን ሰው አሳብ ለማካተት ብቻ የተለጠፈ ነው። ፎቶው ከአንድነት ፓርክ የተወሰደ ነው።

Exit mobile version