Site icon ETHIO12.COM

በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የዜጎችን መፃኢ ዕድል ለመወሰን

በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የዜጎችን መፃኢ ዕድል ለመወሰን መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና እና የምጣኔ-ሀብት ዕድል በር ለከፈቱ ግለሰቦች እና ተቋማት የሚሰጠው “የአፍሪካ የምግብ ሽልማት” አዲስ ሊቀ-መንበር ሾሟል።

የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ሚሪሾ ኪኪዌቴ “የአፍሪካ የምግብ ሽልማት” ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የሽልማቱ ኮሚቴ የቀድሞ ሊቀ-መንበር ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ለአዲሱ “የአፍሪካ የምግብ ሽልማት” ሊቀመንበር የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ሚሪሾ ኪኪዌቴ ኃላፊነቱን አስረክበዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርና ሽግግር ቀጣይነት ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአፍሪካ አንገብጋቢ የሆነውን የምግብ ዋስትናን እና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን በመግለጽ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች አገራት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተለይ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የዜጎችን መፃኢ ዕድል ለመወሰን መሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የሽልማቱ ኮሚቴ የቀድሞ ሊቀ-መንበር ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በበኩላቸው፣ ሽልማቱ የአፍሪካን ግብርና ለማዘመን እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።

ሽልማቱ በአህጉሪቱ በግብርና እና ምግብ ዋስትና አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሰቦች እና ተቋማት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ እና ልምድ ልውውጥ ለአህጉሪቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው እንስተዋል።

አዲሱ “የአፍሪካ የምግብ ሽልማት” ሊቀመንበር የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጃካያ ሚሪሾ፣ በተሰጣቸው ኃላፊነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ የአፍሪካን ግብርና እና የምግብ ዋስትና ለማሻሻል እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የአፍሪካ የምግብ ሽልማትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠሩም ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአፍሪካ የምግብ ሽልማት ውስጥ ካሉት ኮሚቴዎች መካከል የቀድሞ የኢሴክስ መሥራች ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን ይገኙበታል።

“የአፍሪካ የምግብ ሽልማት” የአፍሪካን ግብርና ለሚያሸጋግሩ ግለሰቦች እና ተቋማት 100 ሺህ ዶላር የሚሸልም ነው

ENA

Exit mobile version