Site icon ETHIO12.COM

ኬላዎች አካባቢ የሚታዩ ሕገ ወጥ ተግባራት ለእህል ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሆነዋል -ነጋዴዎች

– ክልሎች ከኮሚሽኑ ዕውቅና ውጪ ያሉ ኬላዎችን እንዲያነሱ አሳስበናል- የጉምሩክ ኮሚሽን

በኬላዎች አካባቢ የሚታዩ አላስፈላጊ እና ሕገ ወጥ ሥራዎች ለእህል ዋጋ ጭማሪ ምክንያት በመሆናቸው መንግሥት የክልል ኬላዎችን በከፍተኛ ሁኔታ መቆጣጠር እንዳለበት የእህል በረንዳ ነጋዴዎች አሳሰቡ።

የጉምሩክ ኮሚሽን በበኩሉ፤ ችግሩ የሚፈጠርባቸው የክልል ኬላዎችን በመለየት ኬላዎቹ እንዲነሱ ለየክልሎች የጽሁፍ ደብዳቤ መላኩን ተናግሯል።

በአዲስ አበባ እህል በረንዳ አካባቢ ነጋዴ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ጌታቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ባሳለፍነው ሳምንት በግብርና ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። ምክንያቱ ደግሞ በኬላዎች አካባቢ የሚታዩት አላስፈላጊ እና ሕገ ወጥ ሥራዎች ናቸው። ስለዚህ መንግሥት በግብርና ምርቶች ላይ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል መንግሥት የክልል ኬላዎችን በከፍተኛ ሁኔታ መቆጣጠር አለበት።

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለፃ፤ ለመንግሥት ተገቢውን ግብር እና ታክስ የሚከፍል ተሽከርካሪ እና ነጋዴ በኬላዎች ላይ በሚያጋጥመው እንግልትና የጊዜ መባከን በአዲስ አበባ የግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር አስተዋጽኦ አለው። ይህም በከተማዋ የዋጋ ንረት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

ሌላው የእህል በረንዳ ነጋዴ አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው፤ መንግሥት በየክልል ኬላዎች ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር የላላ ነው። በዚህም ምክንያት በአካባቢው ሙስና እና ህገወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲበራከት ሆኗል። ስለዚህ መንግስት ያቋቋመው የጸረ ሙስና ኮሚቴ በክልል ኬላዎች ላይም ተግባራዊ ሊሆን ይገባል።

እንደ አቶ ግርማ ገለፃ፤ በክልል ኬላዎች ላይ የሚደረግ እንግልት የግብርና ምርቶች በወቅታቸው ገበያ ላይ እንዳይውሉ ያደርጋል። ይህም የምርት እጥረት ስለሚሚፈጥር በገበያው የሚገኙ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር ይደረጋል።

የገበያ የዋጋ ጭማሪ በሽማቹ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል ያሉት አቶ ግርማ፤ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች መልካም አስተዳደር ለመፍጠር እንደሚሞከረው ሁሉ በኬላዎች ላይም ይህንኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከትናንትና ጀምሮ በግብርና ምርቶች ላይ የነበረው የዋጋ ጭማሪ ቅናሽ ቢያሳይም በገበያው ያሉ ሕገወጥ ደላሎች ለዋጋ ጭማሪው መንስዔ ሆነዋል ያሉት ደግሞ አቶ ድሪባ ሃይሌ ናቸው።

እንደ አቶ ድሪባ ገለፃ፤ ከትናንት ጀምሮ በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ ቢኖርም በገበያው ላይ የዋጋጭ ጭማሪ እንዲኖር የሚያደርጉት በየክልሉ ያሉ ኬላዎች እና ሕገ ወጥ ደላሎች ናቸው። መንግሥት የግብርና ምርቶች ዋጋ የተረጋጋ እንዲሆን በኬላዎችና ሕገወጥ ደላሎች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር ማጠናከር አለበት።

በሀገሪቷ በቂ ምርት እየተመረተ ባለበት ወቅት የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች መቆም አለባቸው። ሕጋዊ ነጋዴዎችን መደገፍና በመልካም አስተዳደር በኩል ያሉ ችግሮችን መንግሥት ቢቀርፍ ችግሩ በአፋጣኝ ሊፈታ እንደሚችል አምናለሁ ብለዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን በበኩሉ፤ ችግሩ የሚፈጠርባቸው የክልል ኬላዎችን በመለየት ኬላዎቹ እንዲነሱ ለየክልሎች የጽሁፍ ደብዳቤ መላኩን ተናግሯል።

የጉሙሩክ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ዳይሬክተር አቶ ተገኔ ደረሰ እንደተናገሩት፤ በአዋጅ ኬላ ማቋቋም የሚችለው ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ ነው። ነገር ግን ከኮሚሽኑ ውጪ በክልሎች በርካታ ሕገወጥ ኬላዎች አሉ። በነዚህ ኬላዎች አማካኝነት ነጋዴዎች እንግልት እየገጠማቸው ይገኛል።

ሕገወጥ ኬላዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ በመሆኑ እና የሀገር ውስጥ ንግድ እንዲጎዳ እያደረጉ በመሆኑ ክልሎች ኬላዎቻቸውን እንዲያነሱ የጽሁፍ ደብዳቤ ተልኳል ያሉት አቶ ተገኔ፤ ኮሚሽኑ ነጋዴዎችን ከእንግልት ለማዳን ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት እየዘረጋ እና ሕገወጥ ሥራን ለመዋጋት ሰፊ ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን አዲስ ዘመን

Exit mobile version