Site icon ETHIO12.COM

ዕርቁ ያሳሰባቸው ከሸኔ ጀርባ ያሉ “ሸኔዎች”

ሸኔ፣ “አንድም ሶስትም ነው” የሚሉ አሉ። ኦነግ ሸኔ ዋናው፣ ሸኔ በግልጽ አመራሩ የማይታወቅና የየሰፈሩ ሸኔ ናቸው። የየሰፈሩ ሸኔ የራሱ መሪ ያለው ሲሆን ዋና ኦነግ ሸኔ ሲያገኛቸው አርባ ይገርፋቸዋል። ከዛም በላይ ይቀጣቸዋል። ተደራጅተው በየአካባቢያቸው ግብር የሚጥሉት እነዚህ ክፍሎች ብዙም ስጋት አይደሉም ነው የሚባለው። በአንገር ጉቲን በኩል ምስራቅ ወለጋ ላይ ጥፋት የሚፈጽመው ሌላው ሸኔ ነው አሁን መነጋገሪያ የሆነው። ምን ነው? እንዴት ይረዳል? ዓላማው ምንድን ነው? ከእነ ማን ጋር ነው ተናቦ የሚሰራው? ትልቁ ጥያቄ ነው። ለሁሉም ግን ዕርቁ ሁሉንም ይግልጠዋል ነው እየተባለ ያለው።አሁን ያለው ሩጫና የትርምስ እሽቅድምድም የዚሁ ውጤት እንደሆነም የሚናገሩ እየበዚ ነው። ስሜት ከሚንጣቸው ጥቂቶች በቀር ይህ ዕርቅ ብዙ ጉዳይ እንደሚያፈነዳ ይጠበቃል። ሁለት ቦታ የሚጫወቱትንም…

የኦሮሞ ሕዝብ መብት አስከባሪ ድርጅት እንደሆነ የሚገልጸውና በዕድሜውም አንጋፋ የሆነው ኦነግ ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ጋር መንግስት ለመስረት ሲንቀሳቀስ ቆይቶ፣ በርካታ ደባ ተፈጽሞበት፣ በዕርቅ ስም ሰራዊቱ ካምፕ ገብቶ ትጥቅ ከፈታ በሁዋላ እንዲመታ ተደርጎ በመጨረሻም ቢሮው ተዘግቶ ከኢትዮጵያ ወጣ። በወቅቱ የኦነግ ሰራዊት ወደ ማሰለጠኛ ካምፖች በተለይም ሁርሶና ደዴሳ እንዲገቡ ያግባባው ሻዕቢያ ነበር። በስምምነቱ መሰረት ኦነግ ሰራዊቱን በሙሉ ሁርሶና ደዴሳ ሲያስገባ ከበው ትጥቁን አስፈቱና አቅመ ቢስ አደረጉት። ኦነግ ወደ አዲስ አበባ ከገባበት ጀምሮ እስከ ወጣበት ድረስ የሆነውን ሁሉ በድንገት ሳይሆን ሆን ተብሎ እንዲሆን ተደርጎ ለመሆኑ መከራከሪያ የሚያቀርቡ እምብዛም አይታዩም። የራሱ የድርጅቱ ድክመት እንዳለ ሆኖ።

ከዛም ትግሉን በውጭ አገር የቀጠለው ኦነግ መጨረሻ ላይ ከትህነግ ጋር ተመሳጥሮ በአስታራቂነት ካባ ጉድ ካደረገው የኤርትራ ገዢ ዘንድ መሽጎ አዲሱን የትጥቅ ትግል መጀመሩን አስታወቀ። በሻዕቢያ ድጋፍ የሚሳካ ነገር እንደማይኖር ቀድመው የተረዱ “አይሆን” ሲሉ ተቃወሙ። ብዙም ሳይቆይ ኤርትራ የመሸገው ኦነግ በተለያዩ ምክንያቶች መከፋፈል ጀመረ። እንዲሁ ሲከፋፈል ቆይቶ በመጨረሻ አምስት በኦነግ ስም የሚጠሩ ድርጅቶች ተፈጠሩ። ወይም አንዱ ኦነግ በተለያዩ ቅጥያዎች እየተሰየመ አምስት ሆነ። አቶ ገላሳ ዲልቦ፣ አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ አባ ነጋአ፣ ጀነራል ከማል ገልቹና አቶ ሌንጮ ለታ በየፊናቸው ኦነግ ሆነው በየግል ድርጅቶቻቸው ገፉበት። መጨረሻ ላይ አንጋፋዎቹና ኤሊት የሚባሉት የእነ ሌንጮና ዶክተር ዲማ፣ ሌንጮ ባቲ… “የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር” ODF የሚባል አዲስ ግንባር መቋቋሙን ከአሜሪካ የሚኖሶታ ጠቅላይግዛት  አስታውቀው ኦነግን በስም ለሌሎቹ ለቀቁ።

ለውጥ መጣና ሁሉም መንግስት ባደረገው ግብዣ አገር ቤት ገቡ። አቶ ዳውድ የሚመሩት ኦነግ ሸኔ በትጥቅ መፍታትና አለመፍታት ሲወዛገቡ ከቆዩ በሁዋላ የተወሰኑ ሃይሎች ወዳ ካምፕ መግባታቸው ተሰማ። ብዙም ሳይቆይ ቅሬታና ግጭት ይናፈስ ጀመር። ከዚያም የአቶ ዳውድ ኦነግ ሸኔ ለሁለት ተከፈለ።

አለመግባባቱ ስር ሰዶ September 13, 2020 የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ የድርጅቱን ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ከሊቀመንበርነታቸውና ከፓርቲው እንዲታገዱ ውሳኔ ማሳለፉ ተሰማ። አቶ ዳውድም በተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸውን አስታወቁ። አንዱ ሌላውን እያቀበና እየከሰሰ ዛሬ ድረስ አሉ። ቢኖሩም የሚሰማው ድምጽ የፖለቲካው ሳይሆን የጠብመንጃ ሆነ። ከጠብ መንጃው ትግል ጋር ተያይዞ የሚነሳው፣ የሚሰማው ሁሉ ለማመን የሚከብድ ሆነ። አሁን ድረስ!!

ለወራት በአመራር ደረጃ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የነበረ የኦነግ ሸኔ ሥራ አስፈጻሚ መግለጫ፤ የድርጀቱን ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከፓርቲው ማገዱንና አዲስ ምርጫ እስኪደረግ፣ እንዲሁም አዲስ መሪ እስኪመረጥ ድረስ የድርጅቱ ተወካይና መሪ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ እንዲኾኑ መሰየሙ ተሰማ። አቶ ዳውድ አገድናቸው የሚሏቸውን ማባረራቸውን ጠሰው መግለጫ አወጡ። ጉዳዩ ወደ ምርጫ ቦርድ ሄደ። እዚህ ላይ ይብቃና ቀልብ ወደ ሳበው የጠብ መንጃ ትግሉ ጎራ እናምራ።

ኦነግን “ሸኔ” በሚለው መለያ ይዘው የቆዩት ወገኖች መከፈላቸው ይፋ ከመሆኑ በፊት ሸኔ የሚባለው ሃይል ወታደራዊ ጥቃት እያደረሰ መሆኑ እንደዋዛ መሰማት ተጀምሮ ነበር። ባንኮች መዘረፋቸውም ተማሪዎች መታፈናቸውና የመንግስት ሃላፊዎች መገደላቸው ይፋ እየሆነ ሲሄድ “ማን ነው የዚህ ዓይነቱ ትግል ባለቤት” የሚል ጥያቄ በስፋት ሲነሳ “እኔ ነኝ” የሚል አካል አልተገኘም። ጃል መሮ የሚባሉት የሰራዊቱ መሪ ግን አልፎ አልፎ ብቅ እያሉ በቪኦኤና ቢቢሲ በኩል፣ ከመናገራቸው ውጪ ፕሮግራማቸው፣ የፖለቲካው አመራሮች፣ አላማቸው፣ ግባቸውና የትግሉ መሰረት በግልጽ ባለመቀመጡ ግራ መጋባቱ ከድርጅቱ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ አደገ። “እኛ ሸኔ አይደለንም። የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት ነን” ሲሉ የበረሃው ጃል መሮ በተደጋጋሚ መናገራቸው ” ሸኔ ታዲያ የማን ነው” የሚለውን ጥያቄ አጋለው። ዛሬም ድረስ ደፍሮ የሚያፈነዳ አካልና ሚዲያ ጠፋ እንጂ ቡሬና ድፍን ምስራቅ ወለጋ ላይ የሆነውንና እንዲሆን የሚፈለገውን ለሚያውቁ ነገሩ ግልጽ ነው። ለዚህ ነው አሁን የተሰማው የኦነግ ሸኔና የኦሮሞ ብልጽግና የሰላም ነገገር ጭምጭምታ ድንጋጤ የፈጠረው። የትርምሱን አጀንዳም እንዲከር ያደረገው።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በጨፌው ስብሰባ ላይ  “በዚህ በተከበረው ጨፌው ፊት በክልላችን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ማለትም ኦነግ ሸኔ በእርቅ ወደ ሰላማዊ መንገድ ተመልሶ እንዲገባ በክብር ጥሪ አቀርባለሁ” ማለታቸውን ተከትሎ ሰፊ ነቀፌታ የተሰማባቸው አቶ ሽመልስ፣ ይህን ካሉ በሁዋላ ባካሄዱት ሰፊ ቃለ ምልልስ ” ለሸኔ ማን ስንቅና ትጥቅ እንደሚያቀርብ ይታወቃል። ይህ በቅርቡ ይፋ ይሆናል” ሲሉ መድመጣቸው ከሚፈራው ጉዳይ ጋር ሲያያዝ የእርቁን አንገብጋቢነት በቀላሉ ለመረዳ ያስችላል።

ብዙውን ጊዜ ከኦሮሞ ታጣቂዎችና ፖለቲከኞች ጋር ቅርበት ያላቸው እንደሚሉት ከሆነ አሁን ላይ የተጀመረው የእርቅ አካሄድ እንደቀድሞው ዓይነት አይደለም። ወደፊት የሚገፋ ነው። ምክንያቱም ከትህነግ ጋር ሰላም ከወረደና የትህነግ ጡንቻ እንዲፈርስ ከተደረገ በሁዋላ ኦነግ ሸኔ ላይ የተጀመረው ዘመቻ ከሯል። ኬንያ ድንበር ዘግታለች። ቦርና መመሸጊያ ሊሆን አይችልም። በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በኩል ስንዝር መሬት ማግኘት አይቻልም። በወለጋ በኩል ቤጊ ሳይቀር ነጻ ወጥቷል። ከሁሉም በላይ ህዝብ ተሰላችቷል። በነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች እርቁ ተግባራዊ ይሆናል።

“ኦሮሚያ የሃይማኖት ተቋማት ምክርቤት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለኦነግ ሸኔ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ደገፉ” የሚለው ዜና ህዝብ ደጋግሞ የሚጠይቀውና ” ምንድን ነው የሚያባላችሁ” ለሚለው ወቀሳ ምላሽ እንዲሰጥ የታሰበውን የዕርቅ አካሄድ የሚያጎላው ሆኗል። “ኦነግ ሸኔ የኦሮሚያ መንግስት ጥሪ ተቀብሎ ምላሽ መስጠቱን ምክር ቤታችን ይደግፋል” ሲሉም የሂደቱን መጋልና ወደ ፍጻሜ መቃረብ አመላክተዋል።

የኦሮሚያ የሃይማኖት ተቋማት ምክር ቤት ምክር “እርቀሠላሙ እንዲሳካ የሚያደርጉ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ” ሲሉ ሁለቱንም አካላት ጥይቀዋል። የምክር ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቡነሳሪዮስ “አንድነት የሚያስፈልግበት ጊዜ በመሆኑ ሁሉም አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል። ለእርቁ መሣካት ሁሉም በእየፊናዉ የድርሻውን እንዲወጣ” ሲሉ አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል ኢትዮ12 የዕርቅ ንግግር መጀመሩን ጠቅሳ መዘገቧ ይታወሳል። ቀደም ሲል ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም በኦሮሞ ስም የሚጠሩ ድርጅቶች አንድ ትልቅ ፓርቲ እንዲመሰርቱ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ህብረቱን ሊፈጽሙ ተቃርበው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ የኦሮሞ አመራሮችን በአንድ ጥላ ስር የሚያሰባስብ “ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ” እንዲመሰረት ሲስማሙ  “የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመካከላቸው የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰለጠና አግባብ ለመፍታትና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መስማማታቸው በክልሉየተጀመሩ ሁለንተናዊ ውጥኖች ከግብ እንዲደርሱ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ተብሎ ነበር። ይህን አካሄድ ጠልፈው ስምምነቱን ወደ ግል ድርጅታቸው ለመሳብ በሞከሩ ብልጣ ብልጦች የታሰበው ሳይሳካ እንደቀረ ውጤቱ ያሳዘናቸው ተናግረው እንደነበር አይዘነጋም።

ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ እንደሚሉት በጣም ውስን ዝርዝር ጉዳዮች ሲቀሩ በአብዛኛው መግባባትና መተማመን ላይ እየተደረሰ መሆኑን አመልክተዋል። ጠበቅ ባለ ዲሲፒሊን እየተካሄደ ያለው የስምምነት ንግግር በአንድ ትልቅ አገር ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑም ተሰምቷል።

ይህን የዕርቅ ዜና የወደዱትና ተግባራዊ እንዲሆን የሚናፍቁ እንዳሉ ሁሉ፣ የነቀፉና አምርረው የኮነኑ አሉ። ኦሮሚያ ገዝፎ እየወጣ እንደሆነ የሚናገሩ ይህ ስምምነት ተግባራዊ መሆን እንደሌለበት እያመለከቱ ነው። ምክንያታቸው ብዙ ቢሆንም ፊትለፊት የሚናገሩት “ኦነግ ሸኔ በግፍ በርካቶችን ገሏል። እንዴት ከዚህ ወንጀለኛ ድርጅት ጋር በገሃድ ስምምነት ይፈጸማል” የሚል ነው።

በርካታ የንጹሃን ህይወት ማለፉን፣ በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸውን ሳይክዱ፣ ይህን የፈጸሙ ወደ ህግ መቅረብ እንዳለባቸው የሚያምኑ በበበኩላቸው ቀጣዩን አደጋ በዕርቅ ዘግቶ በገለልተኛ አካላት ወንጀል ተጣርቶ ህጋዊ ፍትህ እንዲሰጥ ሊደረግ ይጋባል ባይ ናቸው።

ከዚህ በተለየ ግን በተለይ ከጎጃም የሚነሱ ታጣቂዎችና ሸኔ የሚባለው ክፍል ግንኙነት እንዳላቸው መሰማቱ፣ ጃል መሮም በይፋ ይህን ቀደም ሲል መናገራቸው፣ መናገርም ብቻ ሳይሆን በገለልተኛ አካል እንዲጣራ መጠየቃቸው፣ ቡሬ አካባቢ የሚታዩ አንዳንድ ምልክቶችና ይህንኑ ተከትሎ በአማራና ኦሮሞ ብልጽግና መካከል በግልጽ ምክንያቱ ሳይጠቀስ በቅኔና በደምሳሳው የሚያካሂዱት የቃላት ጦርነት ፍጻሜ መቃረቡን የሚያሳይ በመሆኑ ዕርቁን በጉጉት እየጠበቁት ያሉት በርጋታ ነገሩን የሚመረምሩ ወገኖች ናቸው።

ዋናውና ትልቁ ጉዳይ ከሸኔ ጀርባ ያለው ድብብቆሽና የሸኔ የፖለቲካ ክፍሉ አመራሮቹ እነማን ናቸው? የሚለው ጉዳይ እንደሆነ ዕርቁ በሂደት ላይ እንዳለ የሰሙ የሚጠይቁት ጉዳይ ነው። መንግስትም ሆነ ክልሉ የሸኔ አመራርና ስላጎቱ እንደማይታወቅ በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸው፣ ኦነግም “እኔ ሸኔ አይደለሁም” ማለቱ ” ሸኔ ወይም ሸኔዎች እነማን ናቸ?” ሲሉ ዜጎች እንዲጠይቁ አስችሏቸዋል።

አሁን የተጀመረው ዕርቅ ይፋ ሲሆን ሁሉንም እንደሚገላልጠው የሚናገሩ፣ መጨረሻ ሸኔ የት እንደሚገኝ፣ ማን እንዳቋቋመው? ማን እንደሚረዳው? ማን እንደሚያስታጠቀው በራሱ አንድበት ይናገራል። ዕርቁ ለበርካታ የአገሪቱ ችግሮች መፍትሄ እንደሚያበጅ የሚናገሩ አሁን ላይ ኮሽ ባለበት ሆሉ ትርምስ እንዲሰፋና አገር እንድትበጠበጥ የሚፈልጉ ሃይሎች ሩጫ ይህንኑ ለመቀደም እንደሆነ አድርገው የሚያዩ ጥቂት አይደሉም።

Exit mobile version