ETHIO12.COM

የኮንትሮባንዲስት ፖለቲከኞች ሴራ አዲስ አበቤን እያነከተው ነው፤ የዚህ ሁሉ ሴራ ባለቤት ግን ማን ነው?

ፍጹም የሆነ አብሮነት መለያው የሆነው “አዲስ አበቤ” ያኮረፈ ሁሉ በትሩን የሚያሳርፍበት ህዝብ ከሆነ ከርሟል። በ”ፖለቲካ ኮንትሮባንዲስቶች” ሴራና ትዕዛዝ ምንጩ በውል በማይታወቅ ገንዘብ በሚሰማሩ ተከፋዮችና ያልገባቸው አንዴ ዙሪያውን ይዘጋበታል። ለዕለት ጉርሱ ባቶ የሚያድረው ህዝብ በነዚሁ ቁማርተኞችና የስልጣን ጥመኞች ውሳኔ እንዲራብ፣ እንዲጨነቅ፣ እንዲፈራ፣ እንዲማረር ይደረገጋል። የሚያሳዝነው ችግርና አደጋ የሚጠምቁት ክፍሎች ዞረው ችግሩን በማጉላት የሚዲያና የማህበራዊ ድሮች አድማቂ መሆናቸው ነው።

“ለመሆኑ” ያላሉ በርካታ ዝምታ የሚመርጡ ወይም “አድፋጭ” የሚባሉት አብዛኞች። ” ለመሆኑ ከዚህ ሁሉ መልኩን የሚቀያይር ሴራና አመጽ ጀርባ ማን ነው ያለው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ይኸው አዲስ አበባ ላይ መልኩን እንዲቀያየር እየተደረገ የሚጠመቀው አደገኛ ሴራ አንድ ቀን መልኩን ቢቀይር ” እኔ ተረክቤ ጸጥ አሰኘዋለሁ” የሚል አካል አለመሰማቱ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲቆጣ ሆን ተብሎ የሚነዛውና የሚሰራጨው መርዝ፣ ምንም ሳይገባቸው በሚያከፋፍሉ ምስኪን ዜጎች አማካይነትና ለዚሁ ዓላማ በተሰማሩ አማካይነት በደቂቃዎች ውስጥ ሲሰራጭ ህዝብ ” አሁን በዛ” በሚል የምሬትና ራስን መቆጣተር የማያስችል አድማ ውስጥ እንዲገባ ታስቦ እንደሚሰራ እዛው ሰፈር የነበሩና ወደ ቀላባቸው የተመለሱ መስክረዋል።

“የፖለቲካ ኮንትሮባንዲስቶች” ለተቀጠሩበትና ለስልጣን ሲሉ ተደራጅተው ከመታገል ይልቅ በአቋራጭ ደሃ እያስጨረሱ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት መትጋት ከጀመሩ ቆይተዋል። ይህንኑ ፍላጎታቸውን ከአንድ ተጀምሮ ከከሸፈ ዕቅዳቸው በሁዋላ ደጋግመው ሲያስተጋቡት ስለሚሰማ እዚህ ላይ ክርክር የለም። በዚሁ መነሻ የዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ተቋሞች መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ነዋሪዎች ለፖለቲካ ፍጆታ ያመች ዘንዳ እየተወቀጡ ነው።

ሰሞኑንን በጎሃጽዮን የፍተሻ ኬላ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል መታወቂያ እያየ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልከላቸውን በመግለጽ ” ጎጃም መሮት ጤፍ ወደ አዲስ አበባ መላክ አቆመ” የሚል ዜና መሰማቱን ተከትሎ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ የጤፍ ዋጋ በአማካይ 2500 እና 2000 ብር እንደ ጥራት ደረጃው ጭምሯል። ጥቁርና ሰርገኛ እስከ ስምንት ሺህ ሲሸጥ ነጭ ጤፍ አስር ሺህ እንደገባ እህል ንግድ ላይ የተሰማሩ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።

ጉዳዩ ማንን ለምን ለመቅጣት ታስቦ እንደሆነ ግራ ቢያጋባም ። “የተከበሩ” የሚባሉት አቶ ክርስቲያን ታደለ የራሳቸውን ምክንያት ዘርዝረው በፌስቡክ ገጻቸው “…የጎጃም ሕዝብ ጤፍ ወደ አዲስ አበባ አላስገባም አለ ብሎ መክሰስ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን የመደብደብ አይነት ነው። ይልቅ መንገድ ዘግተው ሕዝብ የሚያሰቃዩትን ነውረኞች መታገሉ ላይ እንበርታ” ሲሉ የትግል ጥሪ በማቅረብ ማዕቀቡ እንደሚቀጥል ፍንጭ ሰጥተዋል። በቅርቡ “ከመረጠን” ሲሉ ራሳቸውን እንደ ነጉሳዊው ዘመን ስያሜ አብዝተው በመሰየም ” ተመካከርን ቃል ተጋባብተናል” ያሉት አቶ ክርስቲያን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ቢሆኑም በኮድ የታሰሩ አሳቦችን በማስተላለፍ፣ አመጽና ግርግር ባሉባቸው ጉዳዮች ውስጥ የነቃ አስተባባሪ በመሆንና ከውጭው ሚዲያ አቋም ጋር የሚስማማ የቅሰቀሳ ስራ በመስራት የሚታወቁ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። እሳቸውም አይሸሽጉትም።

“በጎሃጽዮን የኦሮሚያ ፖሊስ መታወቂያ እያየ አዲስ አበባ እንዳይገቡ “አማራዎችን መርጦ ይከለክላል” በሚል ሰፊ ትችትና ቅሬታ ሲቀርብ ይሰማል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ሰሞኑንን በሰጠው መግለጫ የአደዋን ክብረ በዓል ለማወክ ሲንቀሳቀሱና ቀደም ሲል ሲዘጋጁ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ሺህ የሚጠጉ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ከ560 በላዩ የክልሉ ስም ሳይጠቀስ ለረብሻው ዓላማ ከሌላ ክልል እንደመጡ ነው ያስታወቀው

አቶ በሃይሉ ሃይሌ የሚባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ” መንግስትን መቃወም ያለ የነበረ ነው። ግን አሁን አሁን ጉዳዩ ከማይመለከተው ወይም አግባብነት በሌላቸው ቦታዎች፣ የዕምነት ተቋማት ሳይቀሩ የሚታየው ነውጥ አንደኛ ባለቤቱ ማን ነው? ሁለተኛ ዓላማው ግራ የሚያጋባ ነው” ሲሉ በሚያስተውሏቸው ጉዳዮች ሁሉ ግራ መጋባታቸውን ይገልጻሉ። ስጋት እንዳላቸውም ያስቀምጣሉ።

” ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ጤፍ መግዛት አቆማለሁ” ያሉት አቶ በሃይሉ፣ ከጤፉ መወደደና መጥፋት ይልቅ ነገሮች እንዳይካረሩ ስጋት አላቸው። አንዱ ክልል ሌላውን ክልል ወደ ማቀብ የማያመሩበት ዋስትና የለም። ” መንግስት ህግ ሲያስከብር መብት ጣሰ፣ ዝም ሲል ህግ አያስከብርም” በሚል ሲዘነጥሉት ውለው የሚያድሩት ወገኖች በትክክል ፍላጎታቸውን ቢያሳውቁ ደስተኛ ነኝ” ሲሉም የመብት ጥያቄ ያነሳሉ። አያይዘውም ” ባለቤቱ ፊትለፊት ወጥቶ ሃላፊነት የማይወስድበት ሁከትን አምኖ ተባባሪ መሆን አዲስ ፍራሽ ሳይገዙ አሮጌውን እንደመታል ነው” ሲሉም የቅዠት ህይወት እንደሰለቻቸው ይናገራሉ።

ነዋሪነቱ ወደ ደጀን እንደሆነ የሚናገረው የአዲስ አበባ ነዋሪ “አማራ ክልል ፖለቲካ፣ ሃይማኖትና ኮንትሮባንድ ተቀላቅሎበታል የሚል ግምት አለኝ” ሲል በተለይ ወደ ጎጃም ነገሮች በዚህ መልኩ ለምን እንደከረረ ሊገባው እንዳልቻለ ያስታውቃል። አክሎም እህል በኮንትሮባንድ ለማሻገር አዲስ አበባን ያሳደሙ እዛው ጎጃም ውስጥ በስፋት ጤፍ እየሸመቱ እንደሆነ መስማቱንም ይናገራል። ለማንና ወዴት እንደሚልኩት ለተጠየቀው ሲመልስ “ድሮ አንድ እግር ቡና ሳይኖረው ኤክስፖርት ሲያደርግ የነበረው ማን ነበር” በሚል በጥያቄ መልስ ሰጥቷል። በሰሜኑ ክፍል የቅባት ዕህል ሳይቀር በቀይ ባህር እንዲሻገር እየተደረገ መሆኑም እዚሁ ጋር አብሮ የሚጠቀስ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይመስላል በትህነግና በመንግስት በኩል የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በሁዋላ ደጋፊዎች የነበሩ ወዲያው ተቃዋሚ እንደሆኑ ተስተውሏል።

በኦሮሚያ በኩል ጎሃጽዮን ላይ የልዩ ሃይሉ መታወቂያ እያየ ሰዎች በገፍ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ማቀቡን ተከትሎ ጤፍ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ ከጎጃም በኩል ማዕቀብ መጣሉ ከተሰማ ወዲህ የታየው የዋጋ ንረት የሚያስገርም ነው። ቀደም ሲል የገዙትን ዕህል እስከ ሁለት ሺህ ብር በመጨመር እየቸበቸቡ ያሉት ነጋዴዎች፣ ይህን ያህል ዋጋ ለመጨመራቸው አመክኖ የተሞላው መልስም ምክንያትም የላቸውም።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም አማራና ኦሮሚያ ክልል ግልጽ ያልሆነ መተነኳኮስ ውስጥ ከገቡ ሰነባብቷል። በሁለቱም በኩል የቀደመውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መርህ ትንሳኤ ናፋቂዎች መኖራቸውም የሚገልጹ አሉ። እነዚህ ክፍሎች ብልጽግና ውስጥ ሆነው ለሌላ አሳብና ርዕዮት መጫወታቸው ነገሮች እንዳይሰክኑና መልክ እንዳይዙ አድርጓል። የአማራ ክልል መሪ ዶክተር ከፋለ “አማራ የሚበጠበጠው በውስጡ ባለ ሳይሆን ከውጭ ባለ ችግር ነው” ሲሉ የገለጹት ይህን ይሁን ሌላ ባይታወቅም ” የጣና ዳር” ፖለቲካ በግልጽም በሚስጢርም ክልሉን ሰላም እንደነሳው የሚናገሩም አሉ።

በኦሮሚያ በኩል ክልሉ ውስጥ ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ውይይት እተደረገና ወደ ስምምነት መቃረባቸው፣ ይሳካም አይሳካም አዲስ አበባ ዙሪያን ወደ አንድ ትልቅ ከተማ ለመቀየር አሳብ እንዳላቸው ማስታወቃቸው፣ መንግስት ትህነግን እያባበለ ዳግም ሊያደራጀው እንደሚፈልግ የሚነገረው አንድ ላይ ተዳምሮ ” የኦሮሚያ ኮንትሮባንድ ፖለቲካ” እየተባለ ነው። እንደውም ” ሰልቃጮች” የሚልም ስያሜ እየተሰጣቸውና ሰባት ቀን ያለማቋረጥ በየሚዲያው ከሩቅና ከውጭ እየተወቀጡ ነው።

ጎይቶም ሃይሌ የትግራይ ተወላጅ ሆኖ አዲስ አበባ ይኖራል። ዝርዝር አድራሻውን መናገር እንደማይፈልግ ገልጾ እንዳለው ” ኦሮሚያ ከአማራ ክልል የተፈናቀሉ ሁሉ ወደ ክልሉ እንዲመለሱ መስማማቱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከተናገሩ በሁዋላ በእንዲህ ደረጃ የለየለት ልዩነት መታየቱ አላማረኝም” ሲል ስጋቱን ይገልጻል። ” እውነት ለመናገር ትህነግ ከተሸነፈ በሁዋላ አማራ ክልል እየታየ ያለው ነገር በብዙ መልኩ አያስደስትም። ጀብደኛነት አብዘተዋል። ይህ ለትህነግም አልጠቀመውም” ይላል። ይህን ሲል ከቁጭት ምን ያህል እንደራቀ ተጠይቆ ” እኔ የሚቆጨኝ መገዳደላችን ብቻ ነው። ሌላ የሚቆጨኝ ነገር የለም። አማራ ክልል ግን እኛ ያየነውን በሚናፍቁ አንዳንድ ክፉዎች እየተተራመሰ ነው” ሲል የራሱን ማሳያዎች ያስቀምጣል። በሽሙጥ መልክ ” አማራ ክልል ዶክተር አብይን ለምን እንደሚጠሉት ሳስብ ይገርመኛል። ምን ያላደረገላቸው ነገር አለ?” ሲልም በገደምዳሜ ወልቃይት ጠገዴ ሁመራን አልሞ ይናገራል።

ሰለሞን ቸርነት የገላን ከተማ ነዋሪ ነው ” ኦሮሞ ከፈለገ ከተማዎቹን በሙሉ አዲስ ስም ቢሰጥ ሌሎችን ለምን እንደሚያበሳጭ አይገባኝም” ሲል ስለ ” ሰልቃጭነት” ውግዘት ምላሽ ይሰጣል። ኦሮሞ በክልሉ ውስጥ ህገ መንግስታዊ መብቱን ቢያራምድ፣ አደረጃጀት ቢቀይርና አዲስ መዋቅር ቢያደራጅ ባህር ዳርን እንደማያገባው ሲያስረዳ ” አንድም ክልል አልተቃወመንም፣ ተቃውሞውና ጩከቱ ከባህር ዳር ነው። ይህ አይጠቅምም። አግባብ የሚሆነው በየትኛውም ስፍራ የሚኖሩ ማናቸውም የሰው ልጆች ላይ አግባብ ያልሆነ ተግባር ሲፈጸም ብቻ ሊሆን ይገባል” ይልና “እርግጥ አንዳንድ ስህተቶች አሉ፣ ግን በመነጋገር እንጂ በአድማና አዲስ አበባ በሚኖር ደሃ ላይ የኑሮ ጫና በመጣል መፍትሄ የሚገኝ አይመስለኝም። ኦሮሚያ ያሉ ፖለቲከኞችም ሲከፋቸውና ሲያሴሩ አዲስ አበባን እንቆልፋለን የሚሉት አያስኬድም”

ካለፉት ሁለት ዓመታትና ሶስት ዓመታት ወዲህ ጎጃም ውስጥ የሚሰራው ፖለቲካ ከአማራ ምርጥ መሪዎች ግድያ ጀምሮ ለብዙዎች ግራ ነው። አስቀድመው ምን እንደሚሆን ፍንጭ ከሚሰጡት ጀርባ እነማን እንዳሉም ደፍሮ የሚገልጽ የለም።

በኢትዮጵያ ምርጥ ጀነራሎችና ግድያ ጀርባ እጃቸው እንዳለበት የሚነገርላቸውና ከረሃብተኞች ጉሮሮ መንትፈው የተሰወሩት ሻለቃ ዳዊት ” የጎጃም ድንበር ወለጋ ነው” በሚል ጥሪ ካቀረቡ በሁዋላ ሁሉም የአማራ ክልል አካላት በአብዛኛው ሰላም ቢሆኑም፣ ጣና ዙሪያ አያያዙ አያምርም።

ከአማራ ክልል ዓላማው በማይታወቅና በተራ የስልታን ጥማት ተደራጅቶ ያለውን አስተዳደር በምርጫ ከማስወገድ ይልቅ በአቋራጭ ወንበር ለመያዝ የሚረጨው የልዩነት ፖለቲካ በሰላም በመላው አገሪቱ የሚኖሩ ምስኪን የክልሉ ተወላጆችን ጣጣ ውስጥ ከመክተቱ ውጭ ምንም ፋይዳ እንዳላስገኘ አቶ በሃይሉ ይናገራሉ። አሁን ላይ የተጀመረው አዲስ አበባ ላይ የማደምና የማስራብ ሴራ ሌሎችን ለሌላ አድማና ውሳኔ እንዳይጋብዝ እንደሚሰጉ የገለጹት አቶ በሃይሉ፣ ኮንትሮባንዱን ትተው ፖለቲከኞቹ በቅጡ ፈጥነው እንዲያስብቡበት መክረዋል።

አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ቅጥ አንባሩ የጠፋ፣ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊና ህጋዊ አካሄድ ያላገናዘበ የሽግግር መንግስት ናፋቂነት ያዋታል ወይስ አያዋጣም በሚል አንድ ለልቡናው ያደረ ሚዲያ ክልሎችን ጠይቆ ሃቁን ቢናገር እየተሻለ እንደሆነ የሚመክሩ፣ ይህ በተደጋጋሚ ቢገለጽ በፖለቲካ ኮንትሮባንዲስቶችና በመለስ ፍልስፋና ናፋቂዎች ውስወሳ የሚነጉደውንና እንዲሞት የሚገፋውን የድሃ ልጅ ነበስ ማትረፍ እንደሚቻል ይናገራሉ።

አልሸባብ ወይም ሂዝቦላ ወይም ሌሎች ድርጅቶች አንድ ነገር ሲሆን ሃላፊነቱን እንደሚወስዱ ሁሉ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በአዲስ አበባ እየሆነ ላለው ነውጥና ሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር እግሩን ተክሎ እያሸበረ ያለው የሚናበበ ሁከት፣ በክብረ በዓላላትና ሰዎች ሰብሰብ ባሉበት ሁሉ የሚፈጸመው አመጽ ባለቤቱ ማን እንደሆነ በግልጽ እስካልታወቀ ድረስ እንዲሁ ከመተራመስና አገሪቱን ከማዛል ውጭ ፋይዳ የለውም። ለውጥም አያመጣም። ድሃውን ህዝብ በተለይ ያነክተዋል። ይህ ይብዙዎች ጥያቄ ነው። ይህ እስካልሆነ ድረስ መንግስት ለሚወስደው እርምጃ አመቺ ይሆንለታል። ለመከራከርና “ህግ ጥሰሃል” ለማለትም አይቻልም። ስለሆነም ህግ እንዳይጣስ በየጉራንጉሩና በየፌስ ቡኩ ከመጮህ በህጋዊ አግባብ ራስን ገልጾ መታገሉ ለደጋፊም ለተቃዋሚውም ነሳነት ይሰጣል። ሲደግፍ የሚሞት ቢኖር አውቆ ነውና አሁን እንደሚባለው ” ተሰዋ” ሊባልም ይችላል። ይህ የበርካቶች አስተያየት ጭማቂ ነው። ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ ውስጥ እየሆነ ያለውና የጣና ዳር ፖለቲከኞች ጉዳይ ሰክሮ ያሰከረንም ለዚህ ነው የሚሉ እየበረከቱ ነው።

Exit mobile version