ETHIO12.COM

በሕገወጥ የዶላር ዝውውርና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ

የጋራ ግብረ-ኃይሉ በሕገወጥ የዶላር ዝውውርና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ አሰታወቀ

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች መጋቢት 02 ቀን 2015 ዓ.ም በአካሄደው ኦፕሬሽን በሕገ-ወጥ የዶላር ዝውውር፣ በተለያዩ ሀገራት ሐሰተኛ ገንዘቦች እና በሐሰተኛ ብር ህትመት እንዲሁም በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኙ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለፀ፡፡

የጋራ ግብረ-ኃይሉ በአካሄደው ጠንካራ ኦፕሬሽን ለሕገ-ወጥ ዝውውር የተዘጋጀ በርካታ የአሜሪካን ዶላርና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ተይዘዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በግለሰብ ደረጃ ከ100 ሺህ ብር በላይ ለድርጅቶች ከ200 ሺህ ብር በላይ በቤትና በድርጅት ውስጥ እንዳያስቀምጡ ያስተላለፈውን ክልከላ በመተላለፍ ለዶላር ግዥ ሊውል የነበረ 601 ሺህ 760 ብር፣ በሦስት ቼኮች ተፈርሞ ለሕገ-ወጥ የዶላር ግዥ ሊውል የነበረ 4 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር፣ ሦስት ክላሽንኮቭና አራት ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶች ጋር በሕገ-ወጥ መንገድ ይዘው የተገኙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራ ይገኛል ብሏል፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች የቱሪስት ቪዛ እና ሌሎች ህጋዊ መንገዶችን በመጠቀም ወደ ሀገራችን ከገቡ በኋላ ሰወር ባሉ አካባቢዎች በሚገኙ ፔኒሲዮኖችና ሆቴሎችን በመከራየት ሐሰተኛ ዶላርና ብር በማተም የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማዳከም የተሰማሩ ተጠርጣሪዎች ለዶላሩና ለብሩ ማተሚያ ከሚጠቀሙባቸው ወረቀቶችና ኬሚካሎች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የገለፀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹ ይህንን ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙት አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀም እንደሆነም በምርመራ ተደርሶበታል ብሏል፡፡

የተጀመረው ኦፕሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሚካሄድባቸው በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ በእነዚህ አደገኛ የወንጀል ተግባራት ላይ የተሰማሩት ተጠርጣሪዎች ከነ-ኤግዚቢቶቻቸው በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት በኅብረተሰቡ ጥቆማና በጋራ ግብረ-ኃይሉ ጠንካራ ኦፕሬሽን በመሆኑ ኅብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቦ በየትኛውም አካባቢ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግና ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ጥሪውን አቅርቧል።

ENA

Exit mobile version