Site icon ETHIO12.COM

“የሀገራችን የፖለቲካ ተዋናያን ከህገ ወጥ እና መርህ አልባ እንቅስቃሴ ሊቆጠቡ ይገባል”ብልጽግና ፓርቲ

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

“የሀገራችን የፖለቲካ ተዋናያን ከህገ ወጥ እና መርህ አልባ እንቅስቃሴ ሊቆጠቡ ይገባል”

የብልጽግና ፓርቲ የሁሉም አቋሞቹ እና ተግባሩ መነሻ እና መድረሻ የኢትዮጵያ ህልውና፣ ታላቅነት፣ ብልጽግና እና የህዝቦቿ ሰላም ብቻ ነው፡፡ በዚህ የማይናወጥ ሀገራዊ እና ህዝባዊ መሰረት ላይ ቆመን ለመላ የሀገራችን ህዝቦች የጋራ ደጀን ፣መከታ፣ ክንድ እና የማይታጠፍ አለኝታ የሆነ ሀገራዊ ሰራዊት ለመገንባት ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ ጥረቶች ማድረግ ከጀመርን ውለን አድረናል፡፡

በስድስተኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም የክልሎችን ልዩ ሃይል በህገ መንግስቱ መሰረት መልሰን እንደምናደራጅ አቋማችን ለህዝብ ግልጽ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡

ስለሆነም አሁን ላይ ለብዥታ እና ተገቢውን መስመር ለሳተ የትርጉም አንድምታ የተጋለጠው ልዩ ሃይሎቻችንን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴም አንዳንዶች በሚያሳዝን ሁኔታ አጣመው እንደሚለፍፉት እንግዳ ደራሽ የሆነ የቶሎ ቶሎ ቤት አይነት ውሳኔ ሳይሆን በብዙ ጥናት፣ በጥልቅ ውይይት፣ በሰከነ ንግግር እና በጋራ መግባባት የተደረሰበት ውሳኔ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከህዝባችንም የክልል ልዩ ሃይሎች ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ እና የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት በተሻለ መልኩ በሚያስጠብቅ አኳሃን መልሶ የማደራጀት ስራ መሰራት እንዳለበት በተለያየ መልኩ ለመንግስትና ለፓርቲያችን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ውሳኔው የህዝቡን ፍላጎት ከግምት ዉስጥ ያስገባና ህገመንግስታዊ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በህገ መንግስታችን ላይ በማያሻማ መልኩ እንደተመለከተው ሀገርን እና ህዝብን ከየትኛውም ጥቃት እና ጠላት የሚከላከል ሀገራዊ ሀይል የመገንባት ሃላፊነት እና ስልጣን የፌዴራል መንግስቱ ብቻ እንደሆነ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ የክልል መንግስታትም የክልላቸዉን ሰላምና ጸጥታ የሚያስጠብቅ ክልላዊ ፖሊስ አደራጅተዉ እንደሚመሩ በህገ መንግስቱ ተደንግጓል፡፡

በዚህም መሰረት የክልል ልዩ ሀይሎችን እንደገና የማደራጀት አስፈላጊነት ልክ ያልነበረን ጉዳይ ልክ የማድረግ ውሳኔ እና ጥረት እንጂ ሌላ ምንም አመክንዮ እንደሌለው በውል ሊታወቅ ይገባል፡፡

አንዳንድ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና መሪዎቻቸው እንዲሁም ማህበራዊ አንቂዎች ነን የሚሉ ግለሰቦች ጉዳዩን አንድን ክልል ብቻ ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ አድርገዉ የሚያቀርቡበትና ጉዳዩን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው ‹‹ማክሰም፣ ማጠፍ፣ ማፍረስ፣ መበተን…›› ወዘተ የሚሉት አገላለጾች ምንጫቸው- ከየት እና ምርጫቸው- እንዴት ሆኑ የሚለውን መተንተን ለዚህ አውድ ፋይዳው ብዙ ባይሆንም ግባቸው ግን ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ እና ህዝብን ለማሳሳት በመሞከር ጊዜያዊ ቅቡልነት ለማግኘት የመጣር ፍላጎት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ከዚህ ሀገርን ዋጋ ከሚያስከፍል ህገ ወጥ እና መርህ አልባ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ፓርቲያችን ያሳስባል፡፡

ፓርቲያችን በጽኑ መግለጽ የሚፈልገዉ ዋና ጉዳይ ልዩ ሀይልን ትጥቅ የማስፈታት ሳይሆን የተሻለ የማስታጠቅ፤ የመበተን ሳይሆን በጠንካራ መሰረት ላይ የማደራጀት ስራ ላይ የመሆናችንን የማያሻማ እውነት ነው፡፡ የሁሉም ክልል ልዩ ሀይሎች በብዙ ሀገራዊ ፈተናዎቻችን እና ድሎቻችን ውስጥ መቼም ሊደበዝዝ የማይችል ደማቅ አሻራ እንዳላቸው ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡

በምንም ስለማይተመነውና በነፍሳቸው ተወራርደው ስለሰጡት አገልግሎትም በተለየ አክብሮት እና ፍቅር ያመሰግናሉ፡፡

የልዩ ሀይሎቻችን በመከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊስ መዋቅሮች ውስጥ ተደራጅተዉ ሀገርን እና ህዝብን ማገልገል ለመላው የሀገራችን ህዝቦች የሚኖረው አስተዋጽኦ እጅጉን ሰፊ እና መሰረታዊ ለውጥ የሚያስገኝ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ልዩ ሀይሎቻችንን እስከዛሬ ስትሰጡት ከነበረው አገልግሎት በተሻለ አደረጃጀት፣ ትጥቅ እና ወታደራዊ ብቃት እንድታገለግሉ አስተማማኝ እድል የሚያጎናጽፋቸዉ በመሆኑ ህግ እና ስርዓትን በጠበቀ አኳሃን ለውሳኔው ተግባራዊነት የበኩላቸሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ይህ ውሳኔ በአማራ ክልል ላይ ብቻ የተወሰነ ውሳኔ አድርገው ለማቅረብ የሚጋጋጡ ዘገር ነቅናቂ ግጭት- ናፋቂ ሀይሎች የሚነዙት መርዛማ መረጃ ፍጹም ሀሰት እንደሆነ ፓርቲያችን በአጽንኦት ማሳወቅ ይፈልጋል፤ ውሳኔው ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተነጋግረው የተወሰነ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ የጊዜ መስመር በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚተገበር መሆኑን አበክሮ ያስታውቃል፡፡ የክልል ልዩ ሀይሎች ህገመንግስታዊ በሆኑት የጸጥታ መዋቅሮች ገብተው እንዲያገለግሉ መደረግ እንዳለበት ከብልጽግና እኩል (አንዳንዴም በላይ) ሀሳብ ሲያነሱ እና ሲሞግቱ የነበሩ ፓርቲዎችና አመራሮችም ጭምር ዛሬ ላይ ከስጋው ጾማለሁ ከመረቁ ስጡኝ አይነት መግለጫ ለማውጣት መጋጋጣቸው ፓርቲያችንን እጅጉን አሳዝኖታል፡፡

ሆኖም ግን ብልጽግና ፓርቲ በተግዳሮቶች ውስጥም ቢሆን ከህዝባችን እና ከሁሉም የልዩ ሀይል አመራሮቻችና አባላት ጋር በስክነት በመወያየት እና የተፈጠረውን የተግባቦት ክፍተት በመሙላት ለሀገር እና ለህዝብ ዘላቂ ሰላም በሚበጀው ጎዳና መጓዙን ይቀጥላል፡፡

በዚህ አጋጣሚም ሻማ እንዲሸጥላቸው ጨለማ የሚናፍቁ እና የሚጠብቁ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መሪዎቻቸው ነገሮችን ከማባባስ እና ሞትን ለመጥመቅ- ግጭት ከመጠንሰስ እንዲቆጠቡ በአጽንኦት ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

‹‹እዉነት እና ንጋት እያደረ ይጠራል›› እንደሚባለው ውሳኔው ነገ ከነገ ወድያ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ ሆኖ በታሰበው መሰረት ተፈጻሚ ሲሆን ለሚታይ ግልጽ ውሳኔ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በመክፈል ሰላማችን እንዳይደፈርስ መላው የአማራ ህዝብ እና የልዩ ሃይል አባሎቻችን ነገሮችን በሰከነ መልኩ እንዲያዩ እና ለዚህ ሀገርን እና ህዝብን ለሚጠቅም ቀና ውሳኔ ቀና ምላሽ እንዲሰጡ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ህብረ ብሄራዊ ክንዳችን- ለሁለንተናዊ ሰላማችን!

ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት

Exit mobile version