Site icon ETHIO12.COM

የሽግግር ፍትህ!

የተሳከ የሽግግር ፍትህ ለማሳካት ከበርካታ መርሆች ዉስጥ የሚከተሉት መሰረታዊ ነጥቦች ናቸወ፡፡ እነርሱም ሀገራዊ ባለቤትነትን ማረጋገጥ፡ ሀገራዊ እሳቤዎች ላይ በተቀራረበ ሀሳብ መግባባት፤ ተገላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቃቶች ላይ ቅድሚያ የሚሰጠ ሲሆን እነዚህም የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች፤ አረጋውያን፤ አካል ጉዳተኞች እና ወጣቶችን፤ የተገፉ፡ የተገለሉና ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ልዩ ሁኔታና ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡

መግቢያ፡

በሀገረ መንግስት ግንባታ እና ለውጥ ዉስጥ በርካታ ኩነቶች ይከሰታሉ፡፡ የሰላም ጊዜ፤ የጦርነት ጊዜ፤ የድህነትና የብልጽግና ዘመን፤ ሁሉን ዓቀፍ እድገት፤ ሁሉን አቀፍ ውድቀት፤ የህግ የበላይነት የሰፈነበት በአንጻሩ የሰዎች የበላይነት የነገሰበት፤ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፤ ሰላምና መረጋጋት፤ በዜጎች መካከል መፈቃቀር እንዲሁም አለመግባበቶች ሊከሰቱ የሚችሉ የገሃዱ ዓለም እውነታዎች ናቸው፡፡

በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የትኛውም የሀገር መንግስት ተቀዳሚ ተግባሩ የመንግስትን እና የዜጎችን ሠላምና ደህንነት ማረጋገጥ፤ እውነተኛ ፍትህን ማስፈን ነው፡፡ በሰላምና ጸጥታ የማስከበር ሂደት ውስጥ አንድ በኩል አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት ሲያገኙ በአንጻሩ ሰላማዊ የሆኑ ዜጎች የጥፋት ሰላባ ሆነው ፍትህ ሲጠይቁ ይስተዋላል፡፡

በሰላም ይሁን በጦርነት ጊዜ አላግባብ ሰብዓዊ መብታቸውን የተገፈፉ፤ ፍትሕ ያጡ፤ የአካል እና የሞራል ውድቀት የደረሳባቸው ዜጎች የሽግግር ፍትህ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታታ በርካታ ሀገራት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን በመቅረጽ ተግበራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን የሽግግር ፍትህ ሥርዓትን ለመዘረጋት እና ተግባረዊ ለማድረገ ያለሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

ስለሆነም በዚህ ጽሁፍ ስጠቅላላ የሽግግር ፍትህ ጽንሰ ሃሳብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንሞክራለን፡፡

የሽግግር ፍትህ ምንነት

የሽግግር ፍትህ ማለት፡- በሽግግር ውስጥ ያለ ማህበረሰብ ከነበረበት ሁኔታ ሲወጣ ወይም ለመውጣት በሚያደርገው ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመው ፈተና ወይም የፍትህ እጦት ነዉ፡፡ የዚህ የሰላም እጦት መነሻ ምክንያቱ በእርስ በእርስ ግጭት፤ በውስጥና የዉጭ ጦርነት ወይም ሀገር ሰላም በነበረችበት ወቅትም ቢሆን የተፈፀመ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ጥቃቶች ናቸው፡፡ የሽግግር ፍትህ መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች በተሟላ መልኩ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ነው። በዋናነት ሙሉ ፍትህ የሚሰጥበትን መንገድ መዘርጋት፤ የህግ የበላይነት የሰፈነበት፤ ማህበረሰቡ ተመልሶ ወደቀደመ የፍትህ እጦት ሁኔታው ውሰጥ እንዳይመለስ ለማድረግ የሚያስችል ዘላቂ የሰላም እና እርቅ ስርዓቶችን መዘርጋት ነው፡፡

የሽግግር ፍትህ አስፈላጊነት

በአንድ ሀገር ውስጥ ውስብስብ በደሎች ይፈጸማሉ፡፡ በመደበኛዉ የህግ ሂደት አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የተላለፉ ቅጣቶች ቀጣይነት ያለዉ ሰላም እና እውነተኛ ፍትህን ለማምጣት በቂ አይደሉም፡፡ የተለያየ ሀገራት ተሞክሮዎችም የሚያሳዩት በመደበኛው ወንጀል ክስ አማካኝነት የአጥፊዎችን ተጠያቂነት በማረጋገጥ ላይ በማተኮራቸው ተጎጆዎችን በፍትህ አለመፈወሳቸው እንዲሁም ተጎጂዎችን እና ማህበረሰቡን ለማከም በቂ ትኩረት አለመስጠታቸው እንደ ክፍተት የታየ እውነት ነዉ፡፡

ስለሆነም ሌሎች አማራጮችን ማፈላለጉ የህበረተሰቡን መሰረታዊ የፍትህ ጥያቄ ሊመለስ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ከአፓርተይድ ሥርዓት ማብቂያ በኋላ /post-apartheid transitional justice/፤ በዳይና ተበዳይ ተቀራርበዉ በመነጋገር እርቀ ሰላም ያወረዱበትና ዘላቂ ሰላም የተገኘበት፤ እንዲሁም በሴራሊዮን፤ በላይቤሪያ፤ በኬኒያ በተደረገዉ የሽግግር ፍትህ በርካታ ጠቀሜታዎች መገኘታቸዉን መረዳት ይቻላልል፡፡ ለሆነም አጠቃላይ አስፈላጊነቱ ሲታይ

 የቆዩ የመንግስታዊ ጭቆና፤ አድሏዊነት፤ በደሎች እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭት በነበሩባቸው ሀገራት ሁሉንም አጥፊዎች ለፍርድ ማቅረብ የማይቻል በመሆኑ የተወሰኑትን ዋና ዋና ወንጀል ፈጻሚዎችን የሚቀጣ የፍትህ ሂደት በማስፈለጉ፤

 የተሳካ የሽግግር ፍትህ ሂደት ለሀገረ-መንግስት ግንባታ እና ቀጣይነት ላይ ከፍ ያለ ሚና የሚጫወት መሆኑ፡

 በጥፋተኞች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች ዘላቂ ሰላም እና እርቅ በመፍጠር ረገድ ተገቢ አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑ፤

 ከረጅም ጊዜ በፊት የነበሩ እና አሁን ላይ እተፈጸሙ ያሉ በርከት ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች ላይ ትኩረት በመስጠት አጥፊዎቸን ለህግ በማቅረብ መጠየቅ እንዲችሉ ማድረጉ፤

 የሽግግር ፍትህ ስልትን ተጠቅሞ ተጠያቂነትን ከማስፈን በተጨማሪ የሽግግር ፍትህ ሂደቱ እውነት የሚጣራበት፤ ለህዝብ ግልጽ የሚሆንበት እና ዘላቂ እርቀ ሰላም የሚረጋግጥበት መሆኑ፤

 ወንጀል ለተፈጸመባቸው ተጎጂዎች የካሳ ስርዓት በመዘርጋት ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ፤

 ከሽግግር ፍትህ ጋር አብሮ የዘመነ እና ይህን አስተሳሰብ የሚሸከም የተቋማትና የሰዉ ሀይል ለውጥ አስፈላጊ በመሆኑ፤

 በእውነት፡ በፍትህ፡ በሰላም እና በእርቀ ሰላም ላይ በመመስረት ማህበራዊ ግንኙነቶችን ማደስ እና የተቀራረብ ሀገራዊ እሳቢዎችን ማምጣት አስፈላጊ በመሆኑ ወዘተ የሚጠቀሱ ነጥቦች ናቸው

የሽግግር ፍትህ ተግዳሮቶች

 ተጠያቁነትን በተመለከተ ከየትኛዉ ጊዜ ጀምሮ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ምርመራና ክስ ይጀመር የሚለው ሀሳብ ላይ ወጥ የሆነ የግዜ ገደብ ማስቀመጥ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ፤

 የወንጀል ምርመራ ራቅ ካለ ጊዜ የሚጀመር ከሆነ የይርጋ ጊዜ የሚገድበው በመሆኑና በዚህም ምክንያት አላግባብ ወንጀል ፈጻሚዎችን የሚያስመልጥ መሆኑ፤

 የወንጀል ምርመራ ከቅርብ ጊዜ የሚጀመር ከሆነ የሽግግር ፍትህ ሁሉን አካታችና የእኩልነት መርህ የሚጻረር ሲሆን የተወሰነ አካል ብቻ የሚያስጠይቅ መሆኑ፤

 የሽግግር ፍትህ ማእቀፍ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ትኩረት ያደረገ ቢሆኑም ነገር ማካተት ያለበት ዓለም ዓቀፍ ይዘት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን ወይስ ሁሉንም ዓይነት ወንጀሎች የሚለው ሀሳብ በተለያዩ ምሁራን እና የህብረተሰበ ክፍሎች ወጥ የሆነ የሚያግባባ ሀሳብ ላይ አለመደረሱ፤

 የሽግግር ፍትህ ሊያስፈጽሙ የሚችሉ ተቋማት ሲቋቋሙ የገለልተኛነት ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ

 ተቋማዊ ማሻሻያ ሲደረግ ጊዜ የሚወስድና ወጭ የሚጠይቅ መሆኑ ወዘተ እንደ ተግዳሮት የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የሽግግር ፍትህ ሂደቱ ሊመራባቸው የሚገቡ መርሆች

የተሳከ የሽግግር ፍትህ ለማሳካት ከበርካታ መርሆች ዉስጥ የሚከተሉት መሰረታዊ ነጥቦች ናቸወ፡፡ እነርሱም ሀገራዊ ባለቤትነትን ማረጋገጥ፡ ሀገራዊ እሳቤዎች ላይ በተቀራረበ ሀሳብ መግባባት፤ ተገላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቃቶች ላይ ቅድሚያ የሚሰጠ ሲሆን እነዚህም የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች፤ አረጋውያን፤ አካል ጉዳተኞች እና ወጣቶችን፤ የተገፉ፡ የተገለሉና ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ልዩ ሁኔታና ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡ የሽግግር ፍትህ ሂደቱም የህዝብ ተሳትፎን ያረጋገጥ፡ በነፃነት፡ በገለልተኝነት፡ በብቃት፡ በአካታችነት እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራር ላይ የተመሰረት መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም የተሳካ የሽግግር ፍትህ ሂደት መርህ የሚደጋገፉ እና የሚመጋገቡ ስልቶች እንደሆኑ በመገንዘብ ተግባሪዊ ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህን መርሆች ተከትሎ ለመተግበር ጠንካራ መንግስት እና ተቋማት እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የሽግግር ፍትህ ሂደት ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተገቢዉን ክስ በማቅረብና በማስቀጣት፡ ሁለንተናዉ የሆነ እርቅን በማጠከር፡ ምህረትን በመስጠት፤ እውነትን በማፈላለግ፤ ማካካሻን በመስጠት፡ተቋማዊ ማሻሻያን እና ሌሎች ተገቢነት ያላቸው ጉዳዮችን በአንድነትና በተመጋጋቢነት ያካተተ ሁለንተናዊ አካሄድ ነው። ስለሆነም በኢትዮጵያ ለተጀመረዉ የሽግግር ፍትህ የፖለሲ አማራጭ ስኬታማነት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡

በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና የተዘጋጀ ministry of justice

Exit mobile version