Site icon ETHIO12.COM

ኦሮሚያ ልዩ ሃይሉን አክስሞ ሃላፊነቱን ለመከላከያ አስረከበ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የልዩ ኃይል አደረጃጀት ስምሪት ማቆሙን አስታወቀ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በተለይም ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ የፌዴራሉ መንግሥት ባስተላለፈው መሠረት የልዩ ኃይል አደረጃጀት መዋቅርን በማፍረስ በተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች መልሶ የማደራጀቱ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል። በክልሉ ያለውን የፀጥታ ማስከበር ሥራንም የአገር መከላከያ ሠራዊት መረከቡን ነው ኮሚሽነሩ ለዶይቼ ቬለ ያረጋገጡት።

በኢትዮጵያ ሰሞነኛ ዐቢይ መነጋገሪያ የሆነው የየክልሎች የልዩ ኃይል መዋቅር እንዲፈርስና አባላቱን በተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች መልሶ የማደራጀት የፌዴራል መንግሥት ውሳኔ በተለይ በአማራ ክልል ብርቱ ተቃውሞ ሲያስነሳ፤ በሌሎች ክልሎች ግን የጎላ ተቃውሞ አልተሰማም። መዋቅሩን በማፍረስ አባላቱን በአገር መከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል መደበኛ ፖሊስ የማደራጀት ሥራን እያከናወንኩ ነው ካሉ ክልሎች የኦሮሚያ ክልል ይጠቀሳል። የልዩ ኃይል አደረጃጀት ቀድሞውኑም ለጊዜያዊ የፀጥታ ችግር ያለ ሕገ መንግስታዊ መርህ መመስረቱን የሚያነሱት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ለሁሉም ክልሎች በወጥነት ተላልፏል ያሉትን መዋቅሩን አፍርሶ በሌላ ፀጥታ ተቋማት የማደራጀቱ ሥራ እየተተገበረ ነው ብለዋል። «ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት የሚፈርስ የሚለው መልሶ ለመገንባት በሚል መወሰድ አለበት። እንደ ወንጀለኛ ፈርሶ የሚሳደድ አካል የለም። አደረጃጀቱ ስህተት ስለነበረበት በዚህ መደራጀት አለበት የሚል ነው መወሰድ ያለበት። አንድ ሕጋዊ ክፍተት መኖሩ ሲሆን ሌላው የሚገዳደር የተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች በአንድ አገር ውስጥ አያስፈልግም በሚል የፀጥታ ችግሮች በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልሎች መደበኛ ፖሊስ በየደረጃው እንዲሠራ በሁሉም ውይይት ተደርጎበት የተወሰነው።»

ውሳኔው ሁሉንም ክልሎች የሚመለከት ነው ያሉት ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በተደረገው ውይይትና በተደረሰበት ስምምነትም አተገባበሩም በአንድ ላይ እየተከናወነ ነው ብለዋል። ሂደቱንም የአገር መከላከያ እንደሚያስፈጽም መወሰኑን በማስረዳት። «የፌዴራል መንግሥት ውሳኔውን ያስተላለፈው ሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ነው። ከዚያ ውስጥ ኦሮሚያ አንዱ እንደመሆኑ መመሪያውን ተቀብለን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እያደራጀን ነው። ኦሮሚያ አላፈረሰም ለአንዳንድ ክልል ብቻ የተላለፈ ነው ሚለው እውነት አይደለም ብቻ ሳይሆን በሬ ወለደ እንደ ማለት ነው። ይሄ የሚደበቅም ስላልሆነ ምንም የተለየ ማብራሪያ አያሻውም። ንጹሑ ህዝብ ግን እንዳይደናገር ውሳኔው ማንንም የሚመለከት መሆኑን ቢገነዘሙ መልካም ነው።»

አሁን በክልሉ የሚሰማራ የልዩ ኃይል አደረጃጀት የለም ያሉት ኮሚሽነር አራርሳ፤ በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል መደበኛ ፖሊስ እንደየሚያስፈልገው መስፈርት እየተደራጁ ለስልጠና እየተሰማሩመሆኑንም ተናግረዋል። በሁሉም የፀጥታ መዋቅሮች አልደራጅም ያለ አሊያም በጡረታ መገለልም ያለበት በደንቡ መሰረት የመሸኘቱ ሥራ እየተተገበረም ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በክልሉ መንግሥት ባለፉት ዓመታት በልዩ ኃይል የተሠራ የፀጥታ ማስከበር ሥራ እውቅና የሚሰጠው ነው የሚል ግምገማ እንዳለ የጠቀሱት ኮሚሽነር አራርሳ፤ በመዋቅሩ አስፈላጊነትና ሕጋዊነት ላይ አሁን የተነሳው ጥያቄ ግን የህዝብ ፍላጎት የታከለበትና ችግሩን በወጥ አገራዊ የፀጥታ መዋቅር መፍታት አማራጭ ሆኖ በመታየቱ መልሶ ግንባታው አስፈልጓል ነው ያሉት። ኦሮሚያ ውስጥ በስፋት ለሚንቀሳቀሰው መንግሥት ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን የመንግሥትን ጥሪ በመቀበል እንቅስቃሴውን የሚያቆም ከሆነ በክልል ሌሎች የፀጥታ ሥራዎች በመደበኛ ፖሊስ እንደሚከወኑም በማመልከት፤ ለጊዜው ግን የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ መከላከያ ኃላፊነቱን መረከቡ ተነግሯል። በኦሮሚያ ላይ አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታው አስተማማኝ እንዳይደለ ያልሸሸጉት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር በተለያየ ስያሜ በመንቀሳቀስ ኅብረተሰቡን የሚያፈናቅሉ መኖራቸውን አመልክተዋል።

Exit mobile version