Site icon ETHIO12.COM

“መጀመሪያ ሁሉም ነገር አስቸጋሪ ቢመስልም በስኬት እንደሚጠናቀቅ ጽኑ እምነት ነበረኝ”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ላደረጉት ብርቱ ጥረት ምስጋና እናቀርባለን መጀመሪያ ሁሉም ነገር አስቸጋሪ ቢመስልም በስኬት እንደሚጠናቀቅ ጽኑ እምነት ነበረኝ
– የናይጀሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ላደረጉት ብርቱ ጥረት ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛና የናይጀሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ተናገሩ።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የመንግስትና ህወሃት የሰላም ስምምነትን ተከትሎ የተገኘውን መልካም ውጤት ተከትሎ ለሰላም ሂደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ በአዲስ አበባ የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛና የናይጀሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ በኢትዮጵያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።

በሰላም ስምምነቱ አተገባበር መጀመሪያ ሁሉም ነገር አስቸጋሪ ቢመስልም በስኬት እንደሚጠናቀቅ ጽኑ እምነት ነበረኝ ሲሉ ተናግረዋል።

በሰላም ሂደቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተለየ መልኩ ለነበራቸው ቁርጠኝነትና ብርቱ ጥረት የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተደረሰው የሰላም ሰምምነት ስኬት ሁሉንም አፍሪካዊ ያኮራ መሆኑን ጠቅሰው ትጥቅ የፈቱ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት ሁሉም አካል እንዲደግፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የትምህርት ቤቶች ፣ ጤና ጣቢያዎች ዳግም ስራ መጀመር የትራንስፖርት አገልግሎት መከፈት የሰላም ሂደቱን ውጤታማነት የሚያሳዩ መሆኑን ጠቅሰው የሰላም ስምምነቱን ሙሉ ለማድረግ ቀጣይ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱን የተሟላ ለማድረግ ሁሉም አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባና በሰላም ስምምነቱ ያገኘነውን ስኬት ስናከበር ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በጦርነቱ ጉዳት የገጠማቸውና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ሁሉም አካላት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በህዝቦች መካከል ዕርቅ በማስፈን፣ የመልሶ ማቋቋም ተግባራትን በማፋጠን ሰላምን፣ ደህንነትንና ልማትን ማፋጠን ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የአፍሪካ መሪ ለመሆን የጀመረችውን ጥረት በስኬት እንደምታጠናቅቅ ያላቸውን ተስፋ መግለጻቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም መንግስትና ህወሃት ባደረጉት የሰላም ስምምነት መሰረት የእስካሁኑ የአተገባበር ሂደት በስኬት እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

በመርሐግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የኬኒያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version