Site icon ETHIO12.COM

በፕሪሚየር ሊጉ መጨረሻ- ኤቨርቶን ዳነ፣ ሌስተርና ሊድስ ተከለሱ፣ አርሰናል ችግሩን አሳበቀ፣ ቼልሲ አዲስ ሹመት ሰጠ

በፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ፍትጊያው ከአርሰናል አቅም መጨረስና የስነልቦና መዳከም ጋር ተያይዞ አክትሞ ነበር። በመርካቶ ቋንቋ የተበላ ዕቁብ ስለነበር፣ የመቋጫው ዕለት ድምቀት የነበሩት ላለመውረድ የሚፋለሙት ክለቦቭ ትንቅንቅ ሆነ።

ቀበሮዎቹን አምስት ጎል ያቃመው አረሰናል፣ በትክክልም በመጨረሻ ጨዋታዎች ወቅት የስነልቦናና የልምድ ማነስ እንደጎዳቸው የሚያሳብቅ ኳስ አሳይተዋል። እጅግ ተዛነንተው የታዩትና ማራኪ ኳስ ያሳዩት አርሰናሎች በዋንጫ ጉጉት ተወጥረው በጭንቀት ውስጥ ከርመው እንደነበር ባሳበቁበት ጨዋታ ከጫና ብዛት ካልሆነ በስተቀር ነጥብ ሊጥሉ እንደማይችሉ አሳይተዋል። አርቴታ ” ኮርቻለሁ” ሲል የሰጠው አስተያየትም ከዚሁ የመነጨ ይመስላል። ዎልቭስ ላይ ሲፈሱ የታዩት አርሰናሎች እንዴት በኤቨርቶን፣ ብራይቶን፣ ዌስት ሃምና ፓላስ በመሳሰሉ ቡድኖች ነጥብ ጣሉ? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ነዳጅ መጨረስ፣ ብቁ ተጠባባቂ ተጫዋች አለመያዝና ወደ ማጠቃለያው ላይ የተፈጠረ የሰንልቦና ስብራት እንደሆነ ማረጋገጫ ነው።

ምንም ይሁን ምን የእንሊግዝ ፕሪሚዬር ሊግ እሑድ ምሽት ተገባዷል። ኤቨርተን ሲተርፍ ሊድስና ሌስተርን ተከልሰዋል። በመጨረሻው የሊጉ አጓጊ ውድደር ቶተንሃም ሊድስ ላይ በርትቶበት ወደ ወራጅ ቀጣና ሲልከው፣ ሌስተር ዌስት ሃምን አሸንፎ ተረፈ ሲባል፣ ኤቨርተን መገባደጃው ላይ አሸናፊዋን ግብ አስመዝግቦ ተርፏል።

ደጋፊዎች እጃችውን ስላካቸው ላይ አድርገው በስጋትና ውጥረት የቡድናቸውን ውጤት ሲያሰሉ ነበር። በመሃል አዝናኝ መድረክ የነበረው የሊቨርፑልና ሳውዝ አምፕተን ጨዋታ ነበር። አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው ሳውዝአምፕተን ሊቨርፑል ላይ አራት ጎል አግብቷል። ዘንድሮ ጎሉን መጠበቅ የተሳነው ሊቨርፑል አራት አግብቶ 4-4 ቢለያዩም ጨዋታው ጎል በገባ ቁጥር በስላካቸው የሌሎችን ወራጅ ቡድኖች ዕድል እያዩ ለሚያሰሉ መዝናና ነበር።

የመውረድ ስጋት አሊያም የመቆየት ተስፋ የነበራቸው ቡድኖች ኤቨርተን፣ ሌስተርና ሊድስ ነበሩ።ከሶስቱ ቡድኖች ላለመውረድ የተሻለ ዕድል የነበረው ኤቨርተን በጉዲሰን ፓርክ ከቦርንመዝ የነበረውን ግጥሚያ በድል መውጣት ነበረበት። ሊድስ ከቶተንሃም፤ ሌስተር ደግሞ ከዌስትሃም ያደረጉት ጨዋታም የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር።

ከአርሰናል ቀጥሎ በሊጉ ለበርካታ ዓመታት የተጫወተው ኤቨርተን በአብዱላየ ዱኩሬ ጎል አስጨናቂውን ጨዋታ በድል ተወጥቷል። ኤቨርተን በእንግሊዝ ከፍተኛ ሊግ ለ69 ዓመታት የተጫወተ ሲሆን ከዱኩሬ ጎል በፊት ግን ይህ 70ኛ ዓመት ይደፍኑ ይሆን የሚለው አጠያያቂ ሆኖ ተገኝቷል። ኤቨርተን ከቦርንመዝ ያለምንም ጎል ሳለ፤ ሌስተር በሜዳው ዌስትሃምን መምራት መጀመሩ የጉዲሰን ፓርክ ተመልካቾችን አስጨንቋል።

ዱኩሬ ጎሏን ሲያስቆጥር ጉዲሰን ፓርክ በርችት አሸበረቀ። ደጋፊዎች መቆሚያ መቀመጫ አጡ። ቢሆንም ጨዋታው በኤቨርተን አንድ ለምንም ጎል መቀጠሉ፤ ሌስተር ደግሞ ዌስትሃምን 2-1 መምራቱ ሌላ ጭንቀት ሆነ። 90ኛው ደቂቃ ሲደርስ አራተኛው ዳኛ ተጨማሪ ደቂቃ ማሳያቸው ላይ ሌላ ጭንቀት አዝለው ከች አሉ። 10 ደቂቃ። ጨዋታቸውን በድል ያጠናቀቁት ሌስተሮች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ሜዳው መሃል ቁጭ ብለው የኤቨርተን ጨዋታ ማየት ጀመሩ።

በስተመጨረሻም 100 ደቂቃ የተፋለመው ኤቨርተን ጨዋታውን በድል ሲወጣ ሌስተርና በቶተንሃም 4-1 የተሸነፈው ሊድስ ወደታችኛው ሊግ መውረዳቸው እርግጥ ሆነ። በሌሎች ጨዋታዎች ቻምፒዮኖቹ ማንቸስተር ሲቲ ወደ ብሬንትፈርድ አቅንተው 1-0 ተረትተዋል። የዋንጫ ተፎካካሪ የነበሩት አርሰናሎች ደግሞ በኤሜሬትስ ዎልቭስን 5 ለምንም ረምርመዋል።

ምናልባት በአርሰናል ቤት የመጨረሻው ጨዋታ ሊሆን ይችላል የተባለለት ዣካ ሁለት ጎሎ ሲያስቆጥር፤ ሳካ እና ጋብርኤል እንዲሁም ተከላካዩ ኪዊዮር የአርሰናልን ጎሎች አስቆጥረዋል። አስተን ቪላ በሜዳው ብራይተንን በመርታት ከ13 ዓመታት በኋላ ወደ አውሮፓ እግር ኳስ ተመልሷል።

በዳግላስ ሉዊዝ እና ዋትኪንስ ጎሎች ታግዞ ድል የተጎናፀፈው ቪላ፤ ሰባተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ በሚቀጥለው ዓመት በአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ይጫወታል። በሌሎች ጨዋታዎች ቼልሲ ከኒውካስል፤ እንዲሁም ክሪስታል ፓላስ ከኖቲንግሃም ፎረስት በተመሳሳይ አንድ አቻ ጨርሰዋል።

ቶተንሃም ከሜዳው ውጭ ሊድስ ዩናይትድ 4-1 ቢረታም ስምንተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ በአውሮፓ ውድድሮች በቀጣይ የውድድር ዘመን አይታይም። ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ በኦልድ ትራፈርድ ፉልሃምን አስተናግዶ ድል ተቀዳጅቷል።

በ19ኛው ደቂቃ በቴቴ ጎል መሪነቱን የወሰዱት ፉልሃም ከ7 ደቂቃ በኋላ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ዴቪድ ዴ ሂያ የሚትሮቪችን ኳስ አድኗል። ዩናይትድ በመጀመሪያው አጋማሽ በሳንቾ፤ በሁለተኛው አጋማሽ በፈረናንዴዝ አማካይነት ባስቆጠራቸው ጎሎች አሸንፏል። ማንቸስተር ዩናይትድ ዘንድሮ በሜዳው ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች 15ቱን በድል ጨርሷል። ሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ክለቦች ዩናይትድ ከሲቲ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ በኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ይገናኛሉ።

የቀድሞው የቶተንሃም እና የፓሪስ ሴንት ዠርሜን አሰልጣኝ ፖቼቲኖ ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት ለመያዝ ሲነጋገሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

ሜትሮ ስፖርት እንዳስነበበው የ51 ዓመቱ አሰልጣኝ ቼልሲን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ከስምምነቱ በኋላ ፖቼቲኖ ቼልሲ በከፍተኛ ገንዘብ ወደ ክለቡ ባስፈረማቸው ተጫዋቾች ላይ ትኩረታቸውን እንደሚደርጉ እና ለአካዳሚ ወጣቶችም እድል እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡

እየታየ በሚታደስ ተጨማሪ አንድ አመትን ባካተተ በሁለት ዓመት ኮንትራት ክለቡን ለማሰልጠን የተስማሙት አርጀንቲናዊው አሰልጣኝ በመጪው የውድድር ዓመት የምዕራብ ለንደኑን ክለብ ወደ ተፎካካሪነት ይመልሱታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የውድድር አመቱን የጨረሰው ቼልሲ በሊጉ 12ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡

ፖቼቲኖ ለቼልሲ በአምስት አመታት ውስጥ ስድስተኛው ቋሚ አሰልጣኝ ሲሆኑ፥ ክለቡ በአዲሱ ባለቤት ቶድ ቦህሊ ባለቤትነት ከተያዘ በኋላ ደግሞ አራተኛው አሰልጣኝ ሆነው ክለቡን ይረከባሉ።

ዜናው ከተለዩ ሚዲያዎች ተወስዶ የዳበረ ነው

Exit mobile version