Site icon ETHIO12.COM

የተጠልፈቸው ጸጋ በላቸው ነጻ ሆነች፤ ጠላፊው አልተያዘም

ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን ከተጠርጣሪው ግለሰብ ማስጣል መቻሉን የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ። የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በተደረገው የተቀናጀ የፀጥታ ኦፕሬሽን በተጠርጣሪው ግለሰብ የተጠለፈችውን ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን ማስጣል መቻሉን ተናግረዋል።

ግንቦት 15 ቀን 2015 ከመደበኛ ስራዋ ወጥታ ወደቤቷ ስታቀና ተጠርጣሪው ግለሰብ ከግብረ አበሮቹ ጋር ያለፍቃዷ የሚኒባስ መኪና ውስጥ በማስገባት የጠለፋ ወንጀል መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

ጉዳዩ ለፖሊስ ከደረሰ ጀምሮ ግብረ ሀይል በማቋቋም ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን ለማስመለጥና ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቀናጀ ክትትል እና ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ለዚህም አጋዥ የሆነው በሀዋሳ ከተማ የየተተከለው ሴኩሪቱ ካሜራ በመታገዝ መቼና የት እንዴት አድርገው ድርጊቱን እንደፈጸሙት መረጃ በማግኘት ወደስራ መገባቱን ጠቅሰዋል።

ተጠርጣሪው ከነግብረ አበሮቹ ወደምስራቅ ጉጂ ቦሬ ከዚያም ጭሮ፣ ሻፋሞና አለታ ወንዶ ድረስ ወይዘሪት ፀጋን ይዞ አቅጣጫ ለማሳት ቢሞክርም የጸጥታ ሀይሉ በልጅቷ ላይ ጉዳት ሳይደርስ በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቀናጀ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪውና ግብረ አበሮቹ የተለያዩ የጦር መሳሪያ በመያዝ ለመሰወር ጥረት ቢያደርጉም በጸጥታ ሃይሎችና በማህበረሰብ ካደረጉት የክትትል ጥረት ማምለጥ አለመቻላቸውን ሲረዱ ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን መልቀቃቸውን ነው ያብራሩት።

እስከአሁን ድረስ ፖሊስ ባደረገው ኦፕሬሽን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የነበራቸውና የወንጀሉ ተጠርጣሪ የሆኑ 11 ግለሰቦችን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪ ግለሰቡ በአሁኑ ሰዓት በሻፋሞ ወረዳ ሹሮ በሚባል ተራራ ስር በሚገኝ ደን በፀጥታ ሀይል ከበባ ውስጥ መሆኑን ገልፀው እጅ እንዲሰጥ እየተጠየቀ መሆኑን ነው ያስረዱት።

አሁን ላይ ወይዘሪት ፀጋ በላቸው በሙሉ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ የገለጹት አቶ አለማየሁ በቀጣይ የማረጋጋትና የጤና ምርመራ ከተደረገላት ብኋላ ፍትህ እንድታገኝ የክልሉ መንግስት አበክሮ ይሰራል ነው ያሉት።

ወይዘሪት ፀጋ በላቸውን ከተጠርጣሪ ግለሰብ ለማስጣል በተደረገው ጥረት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ የፌዴራል ፖሊስ ፣ የክልሉ ፖሊስና ማህበረሰብ ላደረጉት ጥረት አመስግነዋል።

ወንጀለኘውን በህግ ጥላ ስር ለማዋልና ጉዳቱ የደረሰባትን ግለሰብ ለመካስ ፖሊስ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት ጉዳዩን ሌላ መልክ ለማስያዝ የሚጥሩ ስውር ዓላማ ያላቸው ግለሰቦችና አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያዎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አቶ አለማየሁ ማሳሰባቸውን ኢዜአ አመልክቷል።

Exit mobile version