Site icon ETHIO12.COM

ከህገወጥ የወርቅ የቅብብሎሽ ድራማ ውስጥ ነበሩ የተባሉ 32 የመንግስት ሃላፊዎችና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ታሰሩ

በሕገወጥ የወርቅ ምርት፣ ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ የነበራቸው 32 የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የጸጥታ መዋቅር አመራሮችና አምራቾች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ ወርቅ ሲያመርቱ፤ ሲያዘዋውሩ፣ በጥቁር ገበያ ሲሸጡ እንዲሁም ከውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅምን በሚጎዳ ዕኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ መሆናቸውን ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት 32 ግለሰቦች መካከል ስምንቱ የመንግሥትና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ሲሆኑ፤ ሰባቱ ደግሞ ሕጋዊ ፈቃድን ሽፋን አድርገው በሕገወጥ መንገድ ሲሠሩ የነበሩ አምራቾች እንዲሁም 17 አዘዋዋሪዎችና በሕገወጥ ድርጊቱ የተለያየ ተሳትፎ ያላቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከማዕድን ምርት ጋር በተያያዘ የሚታየውን ሕገወጥነት ለመከላከል የተቋቋመውና በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የሚመራው ሀገር ዓቀፍ ምክር ቤት በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በመሆን ሕገወጦችን የማደን ሥምሪት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በዚህም ከ15 ቀን በፊት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሕገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡

በጋምቤላና በደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልልም በተመሳሳይ ሕገወጥ ድርጊት የተሰማሩ ግለሰቦች መያዛቸው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

ይህን ተከትሎም አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከእነዚህ ሕገወጦች ጋር ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ግንኙነት የነበራቸውን ግለሰቦች ለመለየት ያልተቋረጠ ክትትልና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራዎች ሲያከናውን መቆየቱን መግለጫው አመልክቷል፡፡

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ባደረገው ክትትልና የመረጃ ስምሪትም በሕገወጥ የወርቅ ምርት ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ የነበራቸው የመንግሥት ኃላፊዎችና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ ወደ ጎን በመተው በወርቅ ማምረትና ዝውውር ውስጥ በቀጥታ ተሳትፎ እንደነበራቸው ተረጋግጧል፡፡

አንዳንዶቹ የመንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነትን እንደ ከለላ በመጠቀም የወርቅ ማምረትንም ሆነ ዝውውሩን አጣምረው በማካሄድ የሀገር ሀብት ሲዘርፉ መቆየታቸው እንደተደረሰበት መግለጫው ያሳያል፡፡

በዚህ መንገድ የዘርፉን የተለያዩ የሥራ መስኮች ባልተገባ መንገድ ጠቅልለው በመያዝ ሕጋዊ ስርዓቱንና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መብትን ሲያዛቡ እንደነበርም ታውቋል፡፡

በዚህ መሰረትም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኩምሩክ ወረዳ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ፅ/ቤት ኃላፊ ከማል መሀመድ፣ የግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ አብዱልከሪም ዬሚዳ፣ የወረዳው ፖሊስ አመራር ም/ኮ አብዱልሙንየም ሱሌማን እንዲሁም ምክትል አስተዳዳሪ የነበረው አሳይድ አልዕግብ በቁጥጥር ውለዋል፡፡

በጋምቤላ ክልልም የዲማ ወረዳ ማዕድን ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆነው ኡቦንግ ኡቶው ኡጉድ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምዕራብ ኦሞ ዞን የቤሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ከበደ ቡርጂ እና ሌሎችም ከሕገወጥ ድርጊቱ ጋር ትስስር የነበራቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ 21 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ420 መሰል ጥይቶች፣ 14 ሽጉጦች ከ62 መሰል ጥይቶች፣ 2 ኤፍ1 ቦምቦች፣ 250 የብሬን ጥይቶች፣ ወርቅ፣ 8 የወርቅ ሚዛን፣ 5 የወርቅ መፈተሻ ማሽን፣ 2 የወርቅ ማቅለጫ እንዲሁም የተለያዩ የወርቅ ናሙናዎች፣ ኬሚካሎች እንዲሁም በርካታ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችና የባንክ ደብተሮች በኤግዚብትነት መያዛቸው ታውቋል፡፡

ሕገወጥ የወርቅ ማምረትና ማዘዋወር ተግባሩ ሀገሪቱ ልታገኝ ይገባት የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማሳጣቱ በተጨማሪ የአካባቢው ማኅበረሰብ የበይ ተመልካች እንዲሆን አድርጎታል ያሉት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኩሙሩክ ወረዳ ነዋሪዎች፤ መንግሥት የጀመረው ሕግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ሥራቸውን በሕጋዊ መንገድ እያከናወኑ ያሉ በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦችም ህገ-ወጥነት በመበራከቱ ምክንያት ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ እንቅፋት ተፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ያለው ሕገወጥነት ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የአገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው በህገ-ወጥ ወርቅ ማምረትና ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦችን አገርን እየጎዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት በህገወጦች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለአገር ሰላምና ልማት ጠንቅ የሆነውን ህገወጥነት በማስቆም ረገድ ኀብረተሰቡ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም የአገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግስት ህገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይትን ለማስቆም እያከናወነ ያለውን ስራ ኀብረተሰቡ ሊደግፈው አነደሚገባም እንዲሁ፡፡

ከሰሞኑ ከማዕድን አምራቾችና ነጋዴዎች ጋር በአሶሳ ከተማ በተካሄደ ውይይት የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ በዘርፉ የሚስተዋለው ሕገወጥነት ሰፊ በመሆኑ በመደበኛው የሕግ ሥርዓት ብቻ ይስተካከላል ተብሎ እንደማይታመን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በመሆኑም ሕገወጥ እንቅስቃሴውን መስመር ለማስያዝ ካውንስሉ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እንዲሚወስድ ማረጋገጣቸውም እንዲሁ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በበኩሉ በዘርፉ የሚስተዋለው ሕገወጥነት ሰፊ መሆኑን በጥናት መለየቱን ጠቅሶ፤ በቀጣይ ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡

Exit mobile version