Site icon ETHIO12.COM

“በወልቃይት ምንም ጦርነት የለም፤ ከመከላከያ ጋር አብረን እየሰራን ነው” ኮሎኔል ደመቀ

አቶ ዮሃንስ ቧ ያለው መከለላከያን አጠልሽተው ክልሉን ለቆ እንዲወጣ በጠየቁ ማግስት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና የፀጥታ መምርያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በአካባቢው ምንም ዓይነት ጦርነት አለመኖሩን፣ ከመከላከያ ጋርም አብረው በስምምነት እየሰሩ መሆናቸውን አመለከቱ።

በክልሉ መደበኛ ጉባኤ መከላከያ የትህነግ ሃይል አማራ ክልል ላይ የፈጸመውን ወረራ ከህዝብ ልጆች ጋር ሆኖ እንዴት እንደመከተና ምን ያህል መስዋዕትነት እንደከፈለ በመዘንጋት ” ወራሪ፣ አተራማሽ” በሚል አቶ ዮሐንስ ያጠለሹትን የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ኮሎኔል ደመቀ ‹‹የአገር መከላከያ ሠራዊት የወልቃይት አካባቢን እየተከላከለና እየጠበቀ እንዳለ ነው የምናውቀው፤በአካባቢው ከመከላከያ ጋር ምንም ዓይነት ጦርነት የለም፣ ተባብረን ነው እየሠራን ነው፡፡ አካባቢው ሰላማዊ በመሆኑ ፋኖ በሚል ምክንያት ምንም ዓይነት ግጭትም ሆነ ጦርነት የለም፤›› ሲሉ በተለይ ለሪፖርተር አስታውቀዋል።  

አቶ ዮሐንስ ቧያለው ወልቃይት ጠገዴ ጠለምትን ጨምሮ የማንነትና የድንበር ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ ” ሕዝብ እንዲወስን ይደረጋል፣ በህጋዊ መንገድ ይቋጫል” የሚል ዝርዝር የሌለውና የቦታን ስም ያልጠቀሰ አቅጣጫ እንደተያዘ ፍንጭ መሰጠቱን ተከትሎ ” ህዝብ እንዲወስን የሚደረገው አማራ ጋር ሲደርስ ነው ወይ?” በሚል በምክር ቤት ተቃውሞ አሰምተዋል ህዝብ ካልወሰነ ማን እንደሚወስን ፍላጎት እንዳላቸው አላብራሩም።

በደቡብ ክልል የተለያዩ ውሳኔዎችን መወሰናቸውን በዋቢነት አንስተው ይህ መብት ለአማራ መነፈጉን ገልጸዋል። በደቡብ ክልል የክልልነትና የዞንነት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙት በህዝብ ውሳኔ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ ሪፖርት ማቅረቡም ግልጽ ሆኖ ሳለ የአቶ ዮሐንስ ማነጻጸሪያ ምን ይዘት እንዳለው ለበርካቶች ግራ አጋብቷል። በተለያዩ ማህበራዊ ገጾች በተሰራጨው የምክር ቤት ንግግራቸው ” የእን አምባቸው አጥንት ይወጋናል” ሲሉ መማጸናቸው ደግሞ አቶ ዮሐንስ እነ ዶክተር አምባቸውን ማን እንደገደላቸው ለሚያውቁ መነጋገሪያ ሆኗል። ብዙ ጉዳዮችን በወቀሳና በጉድለት ያስነሱት አቶ ዮሐንስ እግረ መንገዳቸውን እንኳን በአማራ ክልል አመራሮችና የጸጥታ ሃሎች ላይ የሚፈጸመውን ግድያ አላነሱም።

ይህ ንግግራቸው በተሰራጨ በማግስቱ ብረት አንስተው ሰሜን ሸዋ ከሚገኝ ክፍል አመራር ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚያሳይ የድምጽ ቅጂያቸው አደባባይ ወጥቷል። አቶ ዮሐንስ ባገኙት ስልክ እንደሚጠቀሙና ቋሚ ስልክ እንደሌላቸው ጠቅሰው ከጉዳቸው ጋር ሲነጋገሩ የተሰማው የታጣቂውን ሃይል አቋም ሪፖርት ሲሰሙና እሳቸውም በምክር ቤት ስለተደረገው ስብሰባ ሲያስረዱ ነው።

“ትልቁ ሰው” ያሉት ማንን እንደሆነ በግልጽ ባይታወቅም የሰላም ኮሚቴ መቋቋሙ፣ ከታች መዋቅር ጀምሮ ህዝብን የማነጋገር ስራ እንደሚጀመር አመልክተው “ጊዜ ይወስዳል። ለጊዜው ጥሩ ነው። ለመደረጃት ይጠቅመናል… የመደራደሪያ ሃሳቡን አዘጋጅቼ እንዲደርሳችሁ አደርጋለሁ” ሲሉ በስልክ ድምጻቸው ተሰምቷል። አቶ ዮሐንስ ቧያለው የኢትዮጵያን ደህንነት ዋጋ የሌለው እንደሆነ በተናገሩ ሰዓታት ውስጥ ድምጻቸውን መቅዳት ችሏል። ይህ እስከተጻፈ ድረስ አቶ ዮሐንስ “ድምጹ የእኔ አይደለም” የሚል ማስተባበያ አላቀረቡም። ከዚህ ቀደም የአቶ ግርማ የሺ ጥላን ግድያ አስመልክቶ የተደረገ የስልክ ምልልስ ይፋ መሆኑንን ተከትሎ “ፌክ” እንደሆነ ቢገለጽም፣ ድምጹን አጣርቶ “የተሰራ ነው” ያለው ድርጅት የተባለውን ማረጋገጫ አለመስጠቱን፣ ሰጠ በተባለው ማስረጃ ላይ ያለው የስልክ ቁጥር አገልግሎት ላይ ያለዋለና የማይሰራ እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል። ይህን በተመለከተ ሙሉ መረጃ በቀናት ውስጥ እናስነብባለን።

“የአማራና የትግራይ ክልሎች የሚዋሰኑባቸውንን የወልቃይት፣ የጠለምትና የራያ አካባቢዎች ይገባኛል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ላቀረቡት ጥያቄ የሚሰጠውን ውሳኔ እየጠበቅን ነው” ሲሉ የጉዳዩ ባለቤት ኮሎኔል ደመቀ አስታውቀዋል። ኮሎኔል ደመቀ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በቅርቡ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ሁለቱ ክልሎች የሚዋሰኑባቸውን አካባቢዎች “በሕዝብ ውሳኔና በሕጋዊ መንገድ መፍታት አለባቸው” ያሉትን እንዴት ተቀበላችሁ በማለት ለምክትል አስተዳዳሪው ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦላቸው ነው መልስ የሰጡት።

ጥያቄውን በማስተካከል መልስ የሰጡት ኮሎኔል ደመቀ ‹‹በወልቃይት ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እናደርጋለን ሲሉ በግልጽ አልሰማንም” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን “በህግ ይቋጫል” ንግግር ነቅሰው ወደ ፈለጉበት መንገድ ሲጎትቱ ለነበሩ መልስ የሚሆን አስተያየት ሰጥተዋል። “ነገር ግን” አሉ ኮሎኔሉ ” በሕጋዊ መንገድ ቢፈታ ይሻላል የሚለውን ምክር አዘል ነገር ለፓርላማው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ግን በዚህኛው ቀጣና በዚህኛው ዞን ብለው ሲያነሱ እኔም በግል አልሰማሁም፣ እኛም የምናውቀው ነገርም የለም፤›› በማለት እንደ ጉዳዩ ባለቤት “ሰማሁ” ያሉትን ጠቅሰዋል። አይይዘውም ‹‹ነገር ግን የወልቃይት ጉዳይ በየትኛው መንገድ ነው ሊፈታ የሚገባው የሚለውን ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ተናግረናል፡፡ ሊፈታ በሚገባው መንገድ እንዲፈታ ለመንግሥት አመልክተናል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ራያም፣ ጠለምትም፣ ወልቃይትም ስላሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለየትኛው እንደተናሩ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ገልጸው በግምት መልስ ለመስጠት ያስቸግራል ብለዋል፡፡ ‹‹ብዙ ሰው መላምት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የወልቃይት ጉዳይ ሊፈታ የሚገባበትን መንገድ ጠቅሰን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ስላቀረብን ውሳኔውን እየጠበቅን ነው፤›› ሲሉ መናገራቸውን ሪፖርተር አመልክቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅትም ሆነ አሁን ከማኅበረሰቡ ጋር እንዳሉ ገልጸው፣ ‹‹የአገር መከላከያ ሠራዊት የወልቃይት አካባቢን እየተከላከለና እየጠበቀ እንዳለ ነው የምናውቀው፤›› ያሉት ኮሎኔል ደመቀ፣ ‹‹በአካባቢው ከመከላከያ ጋር ምንም ዓይነት ጦርነት የለም፣ ተባብረን ነው እየሠራን ነው፡፡ አካባቢው ሰላማዊ በመሆኑ ፋኖ በሚል ምክንያት ምንም ዓይነት ግጭትም ሆነ ጦርነት የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡   

ትህነግ የሚመራው ኢህአዴ ዒትዮጵያን ሲቆጣጠር ወደ ራሱ ክልል ያካተታቸውን አካባቢዎች ከወረራው በሁዋል በመነጠቁ ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ “አካባቢዎቹ ይሰጡኝ” ሲል ጥያቄ ማንሳቱ ይታወሳል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር የክልሉ አስተዳደራዊ ወሰን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ፣ በጦርነቱ ምክንያት ከምዕራብ ትግራይና ከሌሎች የአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎቸ በአፋጣኝ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ አሁንም ጥያቄ እያቀረበ ነው።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር አባል ክንደያ ገብረ ሕይወት (ፕሮፌሰር) ከጥቂት ሳምንት በፊት በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የወሰን ጥያቄ ለምን ይነሳል አንልም፡፡ ነገር ግን ጥያቄው በሕገ መንግሥቱ መርህ ይፈታል ብለን ነው የምናምነው። የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትም የሚያስቀምጠውም ይህንኑ ነው፤›› ማለታቸው ሪፖርተር አስታውሷል። ጦርነት አማራጭ ባለመሆኑ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ክልላቸው እንደሚፈልግ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች በቅርቡ በባህር ዳር ያደረጉት ጉብኝትም ችግሩን በንግግር ለመፍታት በር የከፈተ እንደሆነ መግለጻቸውንም አመልክቷል።

ቀደም ሲል ኮሎኔል ደመቀ የአማራ ማንነት ከተከበረ፣ አካባቢው የአማራ መሆኑና በጉልበት በፖለቲካ ውሳኔ እንደተወሰደ ግልጽ ሆኖ በህግ ከተቋጨ እንኳን ቀደም ሲል ሲኖሩ የነበሩ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊመጣና ሊኖር እንደሚችል ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

በወልቃይት ጠገዴ ጸለምት ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች በአማርኛ መዝፈን፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ መያዝ፣ በአማርኛ መማርን የመርሳሰሉ ሰብአዊ መብታቸው ተገፎ፣ በርካቶች ከመኖሪያቸው ተፈናቀልውና በግፍ ተገድለው፣ ታስረው ወዘተ በስቃይ ሃያ ሰባት ዓመታትን ማሳለፋቸውን ምስክረነት መስጠታቸው ይታወሳል።

ይህንን ማስፈንጠሪያ ethio12news ተጭነው በቴሌግራም ገጻችን ይከተሉን

Exit mobile version