Site icon ETHIO12.COM

የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከሶስት ሺህ በላይ ወንጀለኞችን መያዙን ገለጸ፤ የአልሸባብና አይሲስ አባላት ይገኙበታል

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሕገወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚያሳስብና እየትወሰደ ያለን እርምጃ ጠቅልሎ ያቀርበው የመረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ፣ በአማራ ክልልም ይሁን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ችግሮችን በስለማዊ መንገድና በውይይት ለመፍታት መንገዱ ዝግ ባለመሆኑ ተከታታይ ጥረቶች ጎን ለጎን እንደሚደረጉ ጠቁሞ የህግ ማስከበሩ ስራ መጀመሩን አመ፤ልክቷል።

በሽብር ቡድኖች፣ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና በሙስና ተሳትፈዋል የተባሉ ከ3 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡ ተቋሙ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ያሰራጨው መረጃ እንደሚከተለው ቀርቧል።

በሽብር ቡድኖች፣ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና በሙስና ተሳትፎ የነበራቸው ከ3 ሺ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዓመታዊ አፈፃፀሙን መገምገሙንና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ሀገራዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን የደኅንነት ሥጋቶችን አስቀድሞ የሚያከሽፍ፤ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆነ እንዲሁም ፕሮፌሽናል ተቋም ለመገንባት የሚያስችሉ ተከታታይ የሪፎርም ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ከእነዚህ ስኬታማ ተግባራት ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን የጸጥታ ችግሮች በመፍታት ፈተናዎችን እንድትሻገር ያስቻሉ የተልዕኮ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ መከናወናቸው ተገምገሟል።

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ አፈጻጸም በተገመገመበት መድረክ በበጀት ዓመቱ ከ9 ሺ በላይ መረጃዎች ተቀምረው እንደ አስፈላጊነታቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ተሰብስበውና ተተንትነው ጥቅም ላይ ከዋሉት ከእነዚህ መረጃዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ የተለያዩ የሽብር ቡድኖች እና ኢመደበኛ አደረጃጀቶች እዚህም እዚያም ለመፍጠር እየሞከሯቸው ያሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የዋሉ መሆናቸው በተቋሙ ዓመታዊ ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም በሽብር ቡድኖች፣ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በሙስናና በሌሎችም ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ የነበራቸው ከ3 ሺ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ተቋሙ በሸኔ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ ላይ ባደረገው መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ሁለት ሺ 327 የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና አንድ ሺ 849 ታጣቂዎች ላይም ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠሉን እንዲሁም በበርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉ በግምገማው ተመልክቷል፡፡ በቤህነን፣ ጉምዝ፣ ቅማንትና ሎሌች የታጠቁ ቡድኖች ላይም አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ተመሳሳይ የመረጃ ስምሪት ማከናወኑ በግምግማው ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ተቋሙ ከውጭ አቻ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት ጋር የመረጃ ልውውጥ በማድረግ በንፁሃን ዜጎች ላይ ሊፈፁሙ የነበሩ የሽብር አደጋዎችን በመቀልበስ በዚሁ ሴራ እጃቸው ያለበትን 165 የአልሸባብ አባላት እንዲሁም 121 የአይ ኤስ አባላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉ በግምገማ መድረኩ ተነስቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በተለያዩ ተቋማት ላይ ከተፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ መረጃዎችን አጠናቅሮ በማቅረብ 225 ተጠርጣሪዎች እንዲያዙ ሲደረግ፤ በ691 ተጠርጣሪ ግለሰቦች ላይ ደግሞ መረጃ መሰብሰቡንም በተቋሙ የበጀት አመቱ ዕቅድ አመጻጸም ተጠቁሟል፡፡

በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና የውጭ ምንዛሪ ዙሪያ በተደረገ ክትትልና እርምጃ ከ61 ሚልዮን 781 ሺ በላይ የኢትዮጵያ ብር፤ ከ1 ሚሊዮን 769 ሺ በላይ የአሜሪካ ዶላር፤ ከ509 ሺ በላይ ዩሮና ከፍተኛ መጠን ያላቸው የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ከሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተያየዘም 295 ግለሰቦች፤ ከሕገወጥ የገንዘብ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ደግሞ 117 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም የተቋሙን ዓመታዊ እቅድ አፈፃፀም ግምግማ ዋቢ በማድረግ መግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡

44 ኪሎግራም ወርቅን ጨምሮ በርከት ያለ መጠን ያላቸው ልዩ ልዩ ማዕድናት በአየር መንገድ በኩል ወደ ውጭ ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ነው የገለፀው፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ አጋር ተቋማት ጋር በትብብር በመሥራት እንዲሁም ከውጭ ሀገራት አቻ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሀገራዊ፣ቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊ ሥጋቶች እንዲወገዱ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉ በዓመታዊ አፈጻጸሙ እንደተመለከተ የጠቀሰው መግለጫው፤ ተቋሙ የሀገርን ጥቅምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም ከድርድርና ውይይት ይልቅ መንግሥታዊ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚጥሩ እንዲሁም አጋጣሚዎችን በማቀነባበር ዝርፊያ ለመፈጸም የሚፈልጉ የታጠቁ ቡድኖች፣ ፅንፈኛና አክራሪ ኃይሎች ከውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ሀገራዊ የጸጥታ ሥጋት ለመደቀን ሙከራ እያደረጉ መሆኑ ተገምግሟል፡፡ ሰሞኑን በአማራ ክልል እየታየ ያለው ሁኔታም ለዚህ አብነት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ቀደም ሲል ከኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል የተከሰቱ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት፣ከሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር ተከታታይ ጥረቶች ቢደረጉም ችግሩ በሚፈለገው መንገድ አልተፈታም ያለው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ፤ ለዘረፋ የተደራጁ ጥቂት ኃይሎች አሁን ላይ መንግሥታዊ መዋቅሮች እንዲፈርሱ፤የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት እንዲቋርጡ፤ አንዳንድ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚያገናኙ የመንገድ መሠረት ልማቶች እንዲዘጉ በማድረግ፤ ሕዝቡ ላይ ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ።

በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ በመደበኛው የሕግ ሥርዓት ሊታረም የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ችግሩን ለመፍታት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መደንገጉን ያስታወሰው መግለጫው፤ የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎትም ዐዋጁን የሚያስፈፅመው የጠቅላይ መምሪያ ዕዝን በማስተባበር የክልሉን ሰላምና ደኅንነትን በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ የሚያግዝ ስምሪት ወስዶ እየሠራ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በዚህ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰበው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ፤ አሁንም ችግሩ በውይይትና በድርድር የሚፈታበት መንገድ ዝግ ባለመሆኑ ተከታታይ ጥረቶች እንደሚደረጉ ጠቁሟል፡፡

ከዚህ መንገድ በማፈንገጥ ለዝርፊያ ከተደራጁ ቡድኖች ጋር የሚንቀሳቀሱ አካላት ካሉ በሚጠናቀሩ መረጃዎችና ማስረጃዎች አማካኝነት አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድባቸውና ሕግ የማስከበር ሂደቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ እነዚህ ለዘረፋ የተደራጁ ኃይሎች ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ለሀገር ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ጉልህ አስተዋጽዖ ሲያበረክት የኖረውን የአማራን ሕዝብ ታሪክ ለማጠልሸት ሞክረዋል፡፡

መላው የክልሉ ነዋሪዎች ግን መንግሥት እያደረገ ያለውን ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ በመደገፍ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ እየጣሩ ነው ያለው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ፤ ይህንንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡


Exit mobile version