Site icon ETHIO12.COM

ባህርዳር፣ ላሊበላና ጎንደር በረራዎች መጀመራቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ

በቅርቡ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን እንደሚረከብና አድማሱን በማስፋት ዝናውን ጠብቆ እንደሚሰራ ያስታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች በጊዜያዊነት ተቋርጦ የነበረውን መደበኛ በረራ ከነገ ጀምሮ እንደሚጀምር አስታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት በአጭር ጊዜ የአማራ ክልልን ወደ ቀደመው ሰላሙ እንደሚመልስ ባስታወቀ አርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ነው አየር መንገዱ በጊዚያዊነት አቋርጦት የነበረውን አገልግሎቱን እንደጀመረ ያስታወቀው።

አየር መንገዱ በጊዜያዊነት ተቋርጦ የነበረውን መደበኛ በረራ ነገ ነሐሴ 4 ቀን 2015 ዓ.ም የሚጀምር መሆኑን በይፋዊ የመረጃ አውዱ ይፋ ማድረጉን ይፋ ሲያደርግ መንገደኞችም በአቅራቢያቸው በሚገኙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሽያጭ ቢሮዎች በመሄድ አገልግሎት እንደሚያገኙ አመልክቷል። ወይም ወደጥሪ ማዕከል (6787/+251116179900) በመደወል መስተናገድ እንደሚችሉ ይፋ አድርጓል።

በተያያዘ ዜና ኢትዮጵና ደቡብ ኮሪያ በሀገራቱ መካከል ያለውን የቀጥታ አየር በረራ ቁጥር ከፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በሀገራቱ መካከል በሳምንት ሰባት የነበረውን የቀጥታ አየር በረራ ቁጥር ወደ ዘጠኝ ለማሳደግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የደቡብ ኮሪያ የመሬት፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ይህም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡

ከኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ባለስልጣን ጋር በተገባው ስምምነት መሰረት በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት ላይ ከሚገኙት አራት የመንገደኞች እና ሶስት የካርጎ ሳምንታዊ በረራዎች በተጨማሪ ሁለት የመንገደኞች በረራ እንደሚጨመር ተገልጿል። ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ኮሪያ ቀጥታ በረራ የምታደርግ ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ የሚታወቅ ነው፡፡

በርካታ የደቡብ ኮሪያ መንገደኞች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሌሎች አፍሪካ ሀገሮች ለመጓዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደሚመርጡ ዮንሃፕ የተባለው የዜና ምንጭ ዘግቧል፡፡


Exit mobile version