ETHIO12.COM

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ – መከላከያ በተመረጡ ከተሞች ስራውን አጠናቆ ቃርሚያ ላይ መሆኑን በምዕራፍ አንድ ሪፖርቱ አስታወቀ

– በጦርነቱ የንጹሃን ህይወት ማለፉ ከተለያዩ ምንጮች እየተሰማ ነው፤ የጉዳቱን መጠን በማስረጃ በሚታውቀ ገለልተኛ አካል እስካሁን አልተገለጸም፤ ነዋሪዎች ዝርዝር ባያቀርቡም ያዩትን መስክረዋል

” በአሁኑ ሰዓት ከተሞቹ ከዘረፊዉ መንጋ ስጋት ነጻ ሆነዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ ህግ አስከባሪ አካላት በየሥርቻው የተራረፈውን ዘራፊ በማጽዳት ላይ ናቸው። ማኅበረሰቡም መረጃ በመስጠት፣ አቅሙ በፈቀደው ሁሉ ለዚህ ስራ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ሽንፈት የተከናነበው የፅንፈኞች ቡድን በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ቅርስ ቦታዎችና የእምነት ተቋማት በመግባት ለመደበቅ እየሞከረ ነው “

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 03 ቀን 2015 ዓ.ም

ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ተግባራት ገምግሟል፡፡ የዕዙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዕቅድ በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ በደብረ ብርሃን፣ በላሊበላ፣ በጎንደርና በሸዋ ሮቢት አካባቢ የተሰባሰበውን በዘረፋ እና በጥፋት የተሰማራ ቡድን በመምታትና ከተሞቹን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ ነበር። እነዚህ አካባቢዎች የተመረጡት ብዙ ሕዝብ የሚኖርባቸው፣ ከፍተኛ የንግድና የቱሪስት እንቅስቃሴ ያለባቸው፣ የፖለቲካና የኢንዱስትሪ ማዕከላት በመሆናቸው ነው።

በዚህ መሠረት በስድስቱ ከተሞች ዙሪያ የመጣው የጥፋት ቡድን መሣሪያውን እንዲያስረክብና እጁን እንዲሰጥ የተሰጠውን ዕድል ባለመጠቀሙ እርምጃ ተወስዶበታል፣ የሕግ የበላይነትም እንዲከበር ተደርጓል። የክልሉ ሕዝብ በዚህ ዘራፊ ቡድኑ የተማረረ በመሆኑ፣ የህግ አስካባሪ አካላት ተልዕኮዋቸውን በስኬት እንዲወጡ ተገቢውን ድጋፍ አድርጓል። ጠቅላይ መመሪያ እዙም የክልሉ ህዝብ ላደረገለት ትብብር ምስጋናውን ያቀርባል።

በአሁኑ ሰዓት ከተሞቹ ከዘረፊዉ መንጋ ስጋት ነጻ ሆነዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ ህግ አስከባሪ አካላት በየሥርቻው የተራረፈውን ዘራፊ በማጽዳት ላይ ናቸው። ማኅበረሰቡም መረጃ በመስጠት፣ አቅሙ በፈቀደው ሁሉ ለዚህ ስራ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ሽንፈት የተከናነበው የፅንፈኞች ቡድን በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ቅርስ ቦታዎችና የእምነት ተቋማት በመግባት ለመደበቅ እየሞከረ ነው።

የመከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ ህግ አስከባሪ አካላት ህግ፣ ሥርዓትና ሞራልን ባከበረ መንገድ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛል። በቀጣይም የመጨረሻውን የማጽዳት እና የመልቀም ተግባር በማከናወን ከተሞቹ በአጭር ጊዜ ወደ ተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ይደረጋል።

በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የጠቅላይ መምሪያ ዕዙ እስካሁን 14 ተጠርጣሪዎችን በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን ወደፊትም እንደሁኔታው በቁጥጥር ሥር የሚያውላቸውን ግለሰቦች አስመልክቶ አስፈላጊውን መረጃ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ዕቅድ የተያዘው ከተሞቹን ከዘራፊ የጥፋት ቡድን የማጽዳቱ ተግባር እየተጠናቀቀ በመሆኑ፣

1. ከሐሙስ ነሐሴ 4 ጀምሮ ከላይ በተጠቀሱት ከተሞች መደበኛ የአውሮፕላን በረራ ይጀመራል፤

2. ከባጃጅና ከሞተር ሳይክል በስተቀር ሁሉም ዓይነት የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ወደ አገልግሎት ይገባሉ፤

3. የመንግሥት፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ የንግድ፣ የጤና፣ የፋይናንስ፣ ወዘተ. ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል።

በዚሁ አጋጣሚ የክልሉ ሕዝብ ራሱን ከዘራፊውና ከጽንፈኛው መንጋ በመነጠልና በመከላከል፣ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመሰለፍ ላደረገው ተጋድሎ ዕዙ በድጋሚ ምስጋናውን ያቀርባል።

ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓም

አዲስ አበባ

የአስቸይኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ያስተላለፈው ትዕዛዝና ክልከላ

ቁጥር 1

የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015 አንቀጽ 5 መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ የሚከተሉትን ትዕዛዞችና ክልከላዎች ደንግጓል።

1) በባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሸዋ ሮቢትና ላሊበላ የሕዝብ የአገልግሎት ሰጪ፣ የመንግሥት፣ የማኅበረሰብና የንግድ ተቋማት ከነሐሴ 4/2015 ጀምሮ ክፍት እንዲሆኑ ታዟል።

2) በባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሸዋ ሮቢትና ላሊበላ እስከ ነሐሴ 17፣2015 የሚቆይ የሠዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል፡፡ በዚህም መሰረት የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሰጪ ባለሞያዎች እና የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት ባልደረቦች ውጪ ለማንኛውም ሰው እና ተሽከርካሪ ከምሽቱ አንድ ሰዐት በኋላ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

3) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጪ በአማራ ብሔራዊ ክልል ከተሞች የአደባባይ ስብሰባ፣ ሰልፍ እና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ፈጽሞ የተከለከለ ነው። እንዲሁም በማንኛውም መልኩ የህዝብ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉል እና የትራንስፖርት አገልግሎትን የሚያሰናክል ድርጊት በጥብቅ የተከለከለ ነው።

4) በአማራ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ለጸጥታ ሥራ ከሚንቀሳቀሱ የህግ አስከባሪ አካላት እና ከነዚህ አካላት ፈቃድ ውጭ የጦር መሣሪያ ይዞ መዘዋወር ፈጽሞ የተከለከለ ነው።

5) በአማራ ብሔራዊ ክልል ከላይ በተራ ቁጥር አንድ በተገለጹት ከተሞች የባጃጅ እና የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ከነሐሴ 4 እስከ ነሐሴ 17፣2015 ድረስ ፈጽሞ የተከለከለ ነው።

6) ከባጃጆችና ከሞተር ሳይክሎች በስተቀር ሌሎች የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከነሐሴ 4 ጀምሮ ወደ ሥራ የመመለስ እና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸው።

7) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ትእዛዝ ውጭ ወቅታዊ ሁኔታን ሰበብ በማድረግ ግለሰቦችን ከመደበኛው ህግ አግባብ ውጪ ማሰር እና ማቆየት፣ የንግድ ቤቶችን ማሸግ እና መሰል እርምጃዎችን መውሰድ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

ከላይ የተዘረዘሩትን ትዕዛዞችና ክልከላዎችን በሚጥሱ ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ 7 መሰረት ሃይልን በመጠቀም፣ እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን እርምጃዎችን በመውሰድ ትዕዛዝና ክልከላዎችን እንዲያስፈጽሙ ለሁሉም የህግ አስከባሪ አካላት ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷል።

ነሐሴ 3 ቀን 2015 ዓም

አዲስ አበባ

የአስቸይኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ


Exit mobile version