ETHIO12.COM

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ አደረገ፤ ይዘቱ ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚስችል የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ይፋ አደረገ። የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያውን አስመልክቶ የባንኩ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የዋጋ ንረትን በሁነኛ መልኩ እና በቀጣይነት ለመቆጣጠር የብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጠንካራ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ተናግረዋል።

ከውሳኔዎቹ መካከል የሀገር ውስጥ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ እንደሚገደብ ጠቅሰው፤ ይህም ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸው በዚህ የብድር ጣሪያ መሰረት እንዲስተካከል የሚያስገድድ መሆኑን አንስተዋል። ለመንግስት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር ባለፈው በጀት ዓመት ከተሰጠው ከአንድ ሦስተኛ እንዳይበልጥ የፖሊሲ ውሳኔ መተላለፉንም ይፋ አድርገዋል።

የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሰጠው ሙሉ መግለጫ

ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ ለሚወስዱት የብድር ፋሲሊቲ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል መወሰኑንም ገልጸዋል። ቁልፍ የሆኑ የወጪ ንግዶች ላይ የተሰማሩ ላኪዎች የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ከዚህ ቀደም ስራ ላይ የነበረው 70/30 የድርሻ ክፍፍል ወደ 50/50 እንዲሻሻል መደረጉንም ነው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የገለጹት። በውሳኔው መሰረት ከአጠቃላይ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ውስጥ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ እንደሚያስገቡ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይዘቱ ምንድን ነው? የኢኮኖሚክስ ማህበር ትንተና

1. ለመንግስት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር ባለፈው አመት ከተሰጠው ከ1/3ኛ እንዳይበልጥ ይደረጋል።

ምን ማለት ነው?

መንግስት የበጀት ጉድለት በገጠመው ቁጥር ከብሄራዊ ባንክ ቀጥተኛ ብድር እንደሚወስድ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ባለፈው በጀት ዓመት የመንግስት የበጀት ጉድለት ከፍተኛ የነበረ በመሆኑ ከበጀት ጉድለት መሙያ ስልቶች መካከል የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ፤ የብሄራዊ ባንክ ቀጥተኛ ብድር እና የብር ህትመት መሆኑ እንዳለ ሆኖ አምና መንግስት ከተበደረው (ምን ያህል እንደተበደረ ባላውቅም) አንጻር በዚህ በጀት ዓመት መበደር የሚችለው ከ30 ከመቶ መብለጥ የለበትም ማለት ነው፡፡

ለምሳሌ፡- ዓምና የመንግስት በጀት ጉድለት የነበረው 300 ቢሊየን ብር ቢሆን እና ከሱ ውስጥ 100 ቢሊየኑን ከብሄራዊ ባንክ ተበድሮ የበጀት ጉድለቱን አቃሎ ነበረ ብለን ብናስብ ዘንድሮ መበደር ያለበት አምና ወስዶት ከነበረው 100 ቢሊየን ብር ውስጥ 33 ቢሊየን ብር (1/3ኛ) መብለጥ የለበትም ማለት ነው፡፡

2.መንግስት ቅድሚያ የግምጃ ቤት ሰነድ አማራጭን አሟጦ እንዲጠቀምና አማራጭ ሳይኖር ሲቀር ብቻ የቀጥታ ብድር ይጠቀማል።

ምን ማለት ነው?

ከበጀት ጉድለት መሙያ ስልቶች መካከል የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ፤ የብሄራዊ ባንክ ቀጥተኛ ብድር እና የብር ህትመት (የውጪ ብድር እና እርዳታን ጨምሮ) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁሉም ስልቶች የየራሳቸው ተጽዕኖም እድልም ያላቸው ቢሆንም ከብሄራዊ ባንክ የሚወስደውን ብድር የመጨረሻ አድርገን እንጠቀማለን ማለት ነው (በኔ ሃሳብ ለመንግስት የመጨረሻ አማራጭ መሆን ያለበት ከብሄራዊ ባንክ ከሚወስደው ብድር ይልቅ አዲስ የሚታተም ብርን ማስቀረት ነው!)፡፡

3. በ2016 ዓ/ም በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የሃገር ውስጥ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ ይገደባል። ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚህ የብድር ጣሪያ መሰረት እንዲያስተካክሉ ይደረጋል።

ምን ማለት ነው?

ብድር የሚቀርበው በባንኮች በኩል መሆኑ ይታወቃል (የትርፋቸው መሰረታዊ መነሻም ከብድር ከሚገኝ ወለድ ነው) ስለዚህ በየዓመቱ ለማበደር የሚይዙት ተጨማሪ ጣሪያ ይኖራቸዋል ስለዚህ በቀጣይ በጀት ዓመት ዘንድሮ ካበደሩት አንጻር ተጨማሪ ለማበደር ሲያስቡ እስከ 14 ከመቶ ብቻ አድርጉ ማለት ነው (በአጭሩ ከፍተኛ መጠን ብድር ወደ ገበያ እንዳይለቁ ማለት ነው!)፡፡

4. ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከብሄራዊ ባንክ ከሚወስዱት ብድር የብድር ፋሲሊቲ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል።

ምን ማለት ነው?

ባንኮች ያላቸው ገንዘብ በደንበኞች እጅ እና በብሄራዊ ባንክ እንደሚቀመጥ ይታወቃል ስለሆነም ተጨማሪ ገንዘብ ፈልገው ከብሄራዊ ባንክ ሲበደሩ ወትሮ ይከፍሉ ከነበረው የ16 ከመቶ ወለድ ወደ 18 ከመቶ ወለድ ያድግባቸዋል ማለት ነው (በአጭሩ ወለዱን ፈርተው ተጨማሪ እንዳይበደሩ እና ለደንበኞቻቸው እንዳያበድሩ (ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዳይለቁ) ማለት ነው!)፡፡

5.ቁልፍ የሆኑ የወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዘርፎች በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ላኪዎችን ለማበረታታት ከዚህ ቀደም የነበረው የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ከ70/30 ወደ 50/50 እንዲሻሻል ይደረጋል። ላኪዎች 50 በመቶውን ለብሄራዊ ባንክ እንዲያስገቡ፣ 10 በመቶውን አብረው ለሚሰሩት ባንክ እንዲሰጡ እና 40 በመቶውን ለራሳቸው እንዲጠቀሙ ተወስኗል።

ምን ማለት ነው?

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ 70 በመቶውን ገቢ እንዲያደርጉለት ወስኖ የነበረ ሲሆን ቁልፍ ሴክተር አምራቾችን ለማበረታታት በማሰብ 50 ከመቶውን ብቻ አስገቡ 40 በመቶውን ለራሳቸው እንዲጠቀሙ ወስኗል፤ 10 ከመቶው ደንበኛ የሆኑበት ባንክ ይወስዳል ማለት ነው (በአጭሩ የውጪ ንግድ ላይ ተሳትፎ ያላቸው ከሚሰሩት የውጪ ምንዛሬ ማዘዝ የሚችሉት ከ30 ከመቶ በታች ከነበረው አሁን ወደ 40 ከመቶ አደገ ማለት ነው)፡፡

6. በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ የዋጋ ንረቱ ከ20 በመቶ በታች እንዲሆንና በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ ይሰራል፡፡

በኔ እምነት የዋጋ ንረት በኢትዮጲያ ገበያ በዋናነት መነሻው ከገንዘብ ፖሊሲ የሚመነጭ ባለመሆኑ በአንድ ዓመት ውስጥ የዋጋ ንረትን ከ10 ከመቶ በላይ ለመቀነስ ሊቸገር ይችላል።

በአጠቃላይ የብሄራዊ ባንክ ካለው ስልጣን መካከል መጠቀም ያለበትን እና የሚችለውን ነው የወሰነው፡፡ የብሄራዊ ባንኩ ውሳኔ የገንዘብ ፈሰስን ለመቀነስ ያለመ መሆኑ ግልጽ ነው! ነገር ግን ዋጋ ንረት ከፍተኛ ለሆነበት እና ከጦርነት ለማገገም ለሚጣጣር ኢኮኖሚ ገንዘብ አስፈላጊም ነው፡፡

የገንዘብ አስተዳደር ስራን ከባድ የሚያደርገው ያስፈልጋል የተባለ ገንዘብ ኢኮኖሚን ሊጎዳ ይችላል (በተለይ ምርታማነት ላይ ካልዋለ) በተቃራኒ ጉዳት አለው ተብሎ ከገበያ የተቀነሰ ገንዘብ አምራች ክፍሉን በካፒታል እጥረት አዳክሞ የምርት መጠንን በገበያ ሊቀንስም ይችላል፡፡ ነገር ግን የፊስካል ፖሊሲው ዋጋ ንረት ላይ ያለው ድርሻ ቀላል ባለመሆኑ ዋጋ ንረት በተገለጸው ቁጥር ልክ እንዲቀንስ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ተቋማት ርብርብ ሳይደረግ ለመሳካት መቸገሩ አይቀርም፡፡

Via the Ethiopian Economist


Exit mobile version