Site icon ETHIO12.COM

“የሕዳሴው ግድብ አብይ ሸጦታል” አቶ ጌታቸው

በጁላይ 25 ቀን 2023 ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ ” አብይ ህዳሴውን ሸጦታል። ግብጽ ሄዶ ተዋውሎ መጥቷል። ያለቀ ጉዳይ ነው” ብለው ነበር። ይህ ለአብነት የተጠቀሰ እንጂ እሳቸውን ተከትሎ ለቁጥር በሚታክት ደረጃ በገሃድና በህቡዕ ስም የግድቡ መሸጥ የየእለቱ የዜና ቁርስና ራት ነበር። መንግስት ” በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ድርድር የለም” ብሎ ቢናገር የማያምኑ አቶ ጌታቸውን አምነው ግድቡ ላይ ሟርት እየዘሩ ውለው ቢያድሩም በትግባር የሆነው ግን ሌላ እንደሆነ የግብጽ መገናኛዎች ይመስክሩ ነበር።

የህዳሴ ግድብ የጨበጣ ሪፖርት እየረበበት የዕድሜውን ግማሽ በልቷል። ከተራ የዛፍ ምንጣሮ ጀምሮ ሸፍጥና ሌብነት የተረባረቡበት “ጅግና” ብሎ ህዝብ በሾማቸው ባለሙያዎች ሳይቀር ተነግዶበታል። ህዝብን ሃሰት እየቀለቡ ክህደት ፈጽመውበታል። የህዳሴው ግድብ አገርን፣ ህዝብን፣ ብሄራዊ ጥቅምን፣ መንግስትንና ፓርቲን ዛሬ ድረስ መለየት ባልቻሉ “ወገኖች” ተራክሷል። ለተወሰኑ ቡድኖችና የውጭ ተልዕኮ ባነገቡ በክህደት እንደተሸጠ ተደርጎ አገሪቱ ላይ እዛም እዚህም በመናበብ ለሚለኮሰው ግጭት፣ አለመግባባት፣ ልዩነትና የብሄር ጥላቻ ማቀጣጠያ ተጨማሪ ነዳጅ እንዲሆን ተደርጓል። የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ደማቸውንና ህይወታቸውን እየገበሩ ስራውን ነብስ የዘሩበት ውድ ዜጎች ክብር ሊለገሳቸው ሲገባ በአደባባይ ተሰድበዋል። ሲሰደቡ አበባ የሚበትኑ ጥቂት ደነቋቁርቶች ዛሬም ያዩትን ከማመን ይልቅ መላምትና ቅዠትን ለሚቀለቧቸው ግብር ማስገባትን መርጠዋል።

አቶ ጌታቸው በራሳቸው አንደበትና በሚመሩት የዲጂታል ወያኔ መንጋ ዘፍነው ሲያዘፍኑበት የነበረውን፣ በምናብ ሸጠውት እጃቸውን እያጣፉ “አብይ ሸጦታል፤ አለቀ” በማለት በተዛበቱበት ያልተገራ ምላሳቸው የአዲስ ዓመት መግቢያ ላይ፣ እዛው ህዳሴ ግድብ አናት ላይ “እንቆቅልሽ” ሲጠየቁ፣ “ሃዳሴ ግድብ” ብለው ሲመልሱ ሰምተናል።

አባይ እገሌ ከገሌ ሳይባል በጀግኖች ብልሃት፣ በውድ ዜጎች ሙያዊ ብቃት፣ በቁርጥ ቀን ልጆች ደምና አጥንት አገሩ ምድር ላይ አርፎ በኩራት አረፋ ሲተፋና የግድቡ ጠርዝ ላይ ተጀንኖ ሲንሸራተት አቶ ጌታቸው አይናቸውን በጨው አጥበው ሲያዩት “ምነው መሬት ተስንጥቆ በዋጣቸው” ያሉ ህሊና ያላቸው ቢኖሩም ” ካድሬንት ጸያፍ ነው” በሚል የአቶ ጌታቸውን የሞራል ውድቀት የለኩ በዝተዋል። በተለይ ኮሽ ሲል “ፈነዳ፣ አወደመ” የሚሉ የሰበር ዜና መንደረተኞች ይህን ጉዳይ ዝም ብለው ማለፋቸው “በኢትዮጵያ ዜና በዜና አቅራቢዎችና በተፈጠሩበት ፍጥረታቸው የሚለካ እንጂ በዜና መስፈት አይደለም” በሚል የሚሰጠውን ትችት ገሃድ አድርጎታል።

ማይክራፎን ይዘው አቶ ጌታቸውን እዛው ግድቡ ስር ” ሙክት ያርዳሉ” እያሉ የሚጠይቁ ” ተሸጠ ብለው ነበር እኮ” በሚል የተቀደዱበትን ንግግራቸውን እያሰሙ ማብራሪያ መጠየቅና ውርደታቸውን በማጉላት፣ የትህነግን አካሄድ ኮርጀው አሁንም እየተቀደዱ ያሉትን ሊያስተምሩበት በተገባ ነበር። የመንግስቶቹ ባይችሉ እንኳን “የግል” የሚባሉት …

ከሁሉም በላይ የሚገርመው ኢትዮጵያን ቋሚ ባለዕዳ የሚያደርገው የህዳሴ ግድብ ስምምነት ላይ መንግስት የመፈረም ፍላጎት እያሳየች እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች እንደነገሯቸው ጠቅሰው የዘገቡት ሚዲያዎች ናቸው። አሜሪካ የምትደጉማቸው ሚዲያዎች ይህንን ቢሉም እውንውታው ግን ሌላ እንደ ነበር ጠንቀቀው የሚያውቁ ናቸው።

“የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈን አንሰጥም” መባሉን በስፍራው የነበሩት ቢመሰክሩም “ውስጥ አዋቂዎች ነገሩን” ያሉት ክፍሎች አላስተባበሉም ወይም አላስተካከሉትም። ምንም ሆነ ምን፣ አሳስተዋቸውን ይሁን በሌላ ዛሬ አባይ ተገደበ። የህዳሴው ግድብ ሙሌት የውስጥ ከሃዲዎችና የውጭ የተቀነባበረ ጫናዎችን ባሸነፉ ጀግኖች አራተኛው የውሃ ሙሌቱ ተጠናቀቀ። የኮርቻ ግድብና ከአርባ በላይ ደሴቶች መያዙ ተሰማ። ዝናብ እንኳን ቢቆም ኢትዮጵያ ጠጥታ የማትጨርሰው፣ ዓለምን ሁሉ መቶ ዓመት የሚያጠጣ ውሃ ኢትዮጵያ ከርስ ስር መሆኑ ተበሰረ። ዜናው የሰማው ህዝብ ደስታውን አሁን ድረስ እየገለጸ ነው።

የዜናውን ብስራት የሰሙ ” አቤት ሞገስ ” በሚል እናቱ ከርስ ላይ ሞልቶ ለተኛው ውሃ የቅምጥል ስም ሰጥተዋል። አባይን ሲረግሙ የነበሩና ሮሮ ሲያሰሙ የነበሩ የኪነ ጥበብ ውጤቶችም ቃናቸውን ቀይረው ለህዳሴው ሞገስ የሚሰጥ ስራ እንዲያቀርቡ የጠየቁ ጥቂት አይደሉም። “ማልቀስና ማውገዝ የሚያስቀር” ሲሉ አዳዲስ የውዳሴና የስኬት ታሪክን የሚዘክሩ ስራዎችን በፍጹም ኢትዮጵያዊነት እንዲያቀርቡ ነው የተጠየቀው። ችግኝ ሲተከል ተነስተው እርግማን የሚያሰሙ ” ወዴት ናችሁ” የሚያሰኘው የህዳሴው ገድል የጨዋ ኢትዮጵያዊያን የጥበብ ስራ ይጠብቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሜሪካ በፕሬዚዳንት ክሊንተን ተጸእኖ ፈጣሪነትና በዓለም ባንክ እጅ ጠምዛዥነት ሲደረግ የነበረውን ድርድር አስመልክቶ “የህዳሴ ግድብ ስምምነት ፊርማ እንዲዘገይ አመራር ሰጥቻለሁ” ሲሉ ምስክሮች ያሉበትን ሃቅ ለፓርላማ ገልጸው ነበር። ዶ/ር ዐቢይ ረቂቁን ተመለከቱ፣ የትራምፕን፣ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት እና የአሜሪካውን የገንዘብ ሚ/ር አነጋገሩ፤ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ በስልክ ንግግራቸው ተረዱ፤ ረቂቁ እንዳይፈረም ትዕዛዝ ሰጡ። እንዲያውም በውጭ አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሚሰጣቸው የሙያ ምክር ጠቃሚ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋና ሁሉ አቅርበው ነበር። ይህ ሊያስመሰግናቸውና ሲገባ ” የህዳሴው ግድብ ላይ ክህደት ፈጸሙ” ተብሎ በትህነግ መሪነት ተዘመተባቸው።

የዛሬው የትግራይ ክልል መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ “አብይ የህዳሴ ግድብን ሸጦታል” በሚል የትህነግ ” እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” ዘመቻ ማስፈጸሚያ አጀንዳ ተደርጎም ነበር። ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተእዛዝ በጫና የተጀመረው ንግግር እንዲቋረጥ መደረጉን አደባባይ ሲመሰክሩም የማጥላላትና የጥላቻ ዘመቻ የሚያካሂዱት ክፍሎችና ” ሚስጥር ሰማን” ያሉት ዜናቸውንም ሆነ መረጃቸውን ለማረም ፈቃድ አላሳዩም።

በዝርፊያ ዳዋ የተመታው፣ እውቀት በሌላቸው ሲመራ የነበረውና የቅጥፈት ሪፖርት እየቀረበበት ሌቦች ተጋምደው ሲያርመጠምጡት የነበረው የህዳሴ ግድብ በዚ ደረጃ እያለ ያተነፈሱ አልነበሩም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኮሚቴ አቋቁመው ችግሩን በመግለጥ ዳዋው እንዲጸዳ አድርገው ስራው ሲጀመር ነበር ጎን ለጎን ስም ማጥፋቱ የተጀመረው።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር አቡይ ላይ ትኩረት አድርጎ በቅብብሎሽ፣ በዲጂታል ወያኔ አዝማችነት ሲረጭ የነበረው ስም ማጥፋት በሕዳሴው ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ባበሰሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰበር ዜና መታተሙ የአዲሱ ዓመት በረከት ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያውያን ተባብረን በመሥራታችን ፈጣሪ ረድቶናል” ሲሉ በግል የበማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ምስጋናቸውን ሁሉን ለሚያውቅና ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላካቸው አቅርበዋል።

“በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በጸሎታቸው በሥራው ውስጥ የተሳተፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ፤ ይህ ኅብረታችን በሌሎች ጉዳዮቻችንም ሊደገም ይገባዋል” ሲሉም ” ህዳሴውን ግድብ ሸጡ፣ ኢትዮጵያን ባለዕዳ የሚያደርግ ስምምነት እንዲፈረም መመሪያ ሰጡ” በሚል የስም ማጥፋት ሲያካሂዱባቸው ለነበሩት ጭምር ጥሪ አቅርበዋል።

” ብዙ ፈተና ነበረው፤ ወደኋላ እንድንመለስ ብዙ ተጎትተን ነበር” ሲሉ እዚህ የተደረሰበትን መንገድ በጥቅሉ ያስታወሱት አብይ አሕመድ፣ “በውስጥ ፈተና በውጭ ጫና ነበረብን፤ ከፈጣሪ ጋር የመጣውን ሁሉ ተቋቁመን ለዚህ ደርሰናል፤ ነገር ግን የዳገቱ ጫፍ ላይ ደረስን እንጂ ዳገቱን ወጥተን አልጨረስነውም” ሲሉ መከራና ድሉን አጣቅሰው፣ የወደፊቱን እርምጃ አመላክተዋል።

“በቀጣዩ ጊዜ ያቀድነውን አጠናቅቀን ፈጣሪን እንደምናመሰግን እምነቴ ነው ” ካሉ በሁዋላ “ለግድቡ የምናደርገውን ማናቸውንም ድጋፍ እስከ ፍጻሜው እንድንቀጥል በዚሁ አጋጣሚ አደራ እላለሁ ” ሲሉም መልዕክት አስረተላልፈዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ዘጠና በመቶ ተጠናቋል። ቀሪው አስር በመቶ ብቻ ነው። ይህ በቅኝ ግዛት ወቅት በእንግሊዝ አደራዳሪነት በተደረገ የደባ ስምምነት ከኢትዮጵያ ተነጥቆ የነበር ሃብት አራተኛውን ሙሌት ተጠቆ ግድቡ አናት ላይ በኩራት ተኝቶ ማየት ልብን ያርዳል። አባይ ዘፈን መሆኑ ቀርቶ ህይወት ሆኗል።

ግብፅ 66 በመቶ፣ ሱዳን 22 በመቶ ድርሻ እንዲቀራመቱና ኢትዮጵያ የውሃው ባለቤት ሆና ሳለ በዜሮ እጇን ታጥባ ያለ አንዳች ድርሻ እንትቀመጥ ሆኗል። በዚሁ አይን ያወጣ የዝርፊያ ክፍፍል ከግብጽና ሱዳን የተረፈው 12 በመቶ የሚሆነው ውሃው የሚተን ሆኖ ግምት የወጣለት ነው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስጀምረውት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፣ሌብነቱን፣ የቴክኒክ ችግሩን ቀርፈው፣ ከውስጥ የጥላቻና የስም ማጥፋት ዘመቻውን ተቋቁመው፣ ከውጭ ባንዶች ጭምር የሚያሳድሩትን ጫና ተቋቁመው በሕዝብ ድጋፍ ህዳሴው ግድብ አፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ሲሽኮረመም አሳይተዋልና አገር ተደስቷል።

ሌት ከቀን ሰለቸኝ ሳይል ግንባታው እንዳይስተጓጎልና ተላላኪ ተምቾች ጉዳት እንዳያደርሱበት እንደ ንስር ነቅቶ ለጠበቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ዜጎች በማህበራዊ ገጾቻቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የህዳሴውን ግድብ ለመገናት የሚያስፈልገው ገንዘብ ቢለዋወጥም በወቅቱ ገበያ ቀደም ሲል ማለት ነው 80 ቢሊየን ብር (ከ4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ) መሆኑ ተምልክቶ ነበር። ግድቡ 145 ሜትር ከፍታ አለው። ወደ ጎን ደግሞ 1 ሺህ 780 ሜትር ይረዝማል።

ግድቡ ይይዛል ተብሎ የሚጠበቀውን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሙሉ በሙሉ ሲያከማች፣ የተጠራቀመው ውሃ የሚተኛበት አማካይ ስፍራ ርዝመቱ ከ246 ኪሎ ሜትር በላይ የደርሳል ተብሏል። ለዚህም ነው የህዳሴው ግድብ በቤኒሻንጉል ውስጥ የሚሰራ አንድ ትልቅ ከተማ የተባለው።

የዋናው ግድብ ውፍረት የግድቡ ግርጌ ላይ 130 ሜትር ሲሆን፤ የግድቡ ጫፍ ወይም የላይኛው ክፍል ደግሞ 11 ሜትር ነው። ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ስፋት ደግሞ 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሆኑን ጽሕፈት ቀደም ባሉት ዓመታት ማስታወቁ ይታወሳል። ግድቡ ሲጠናቀቅ ውሃ የሚተኛበት መሬት ርዝመት 246 ኪሎ ሜትር ነው።

የህዳሴው ግድብ በርካታ ደሴቶች ባለቤት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ የቱሪስት ኢንደስትሪ እንደሚስፋፋበት ተመልክቷል። ራሱን የቻለ አገር እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ግድብ የአሳ ምርት መጀመሩም ታውቋል። ሁለት ተርባይኖች ኤሌክትሪክ ማምረት የጀመሩ ሲሆን በቅርቡ በሙሉ ሃይሉ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን ያሳድጋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 6450 ሜጋዋት ኃይል የማምረት አቅም አለው። ከዚሁ ሃይል ውስጥ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከሚውለው ውጭ 2000 ሜጋዋት ሃይል ለጎረቤት አገራት የሚሸጥ ነው። ከዚህ ሽያጭ በወቅቱ ገበያ በዓመት እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝ ከሶስት ዓመት በፊት ተገልጾ ነበር።


Exit mobile version