Site icon ETHIO12.COM

ዘይላ ወደብን ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት የግዛቷ መሪ ንቅናቄ በይፋ ጥያቄ አቀረቡ

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት በይፋ እንደምትንቀሳቀስ ባሳወቀች ማግስት የአውዳል ግዛት ንቅናቄ በይፋ ጥሪ አቅርቧል። ሶማሌ ዳይጀስት እንደዘገበው ንቅናቄው ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ የመግባቢያ ስምምነት እንዲደረግም ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። ከመንግስት ወገን ለጊዜው የተባለ ነገር የለም።

በሶማሊላንዷ አውዳል ግዛት የሚገኘው The Awdal State Movement – ASM ኢትዮጵያ በቀይ ባሕሯ የዘይላ ወደብ እንድትጠቀም ፈቃዱን አሳውቋል። የ ASM ንቅናቄ ባለፈው አርብ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው በተለይም የዘይላ ወደብን ከግምት አስገብቶ በመጥቀስ ነው ለኢትዮጵያ የወደብ አማራጭ መሆኗን እንቀበላለን ያለው።

በዚህ መግለጫ ‘ጋዳቡርሲ’ የተሰኘው የአካባቢው ማህበረሰብ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ታሪካዊ እና ወቅታዊ ፋይዳ በመገንዘብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ታሪካዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥቷል። በበተጨማሪም ታሪካዊው የዘይላ ወደብ የኢትዮጵያ ሱማሌዎችን በመጥቀስ የኢትዮጵያ ህዝብ መጠቀማቸውን እንደሚደግፍ የገለፀ ሲሆን፣ ለስኬቱም ሁሉንም ወገን አሸናፊ በሚያደርግ የመግባቢያ ስምምነት ይደረግ ዘንድ በደስታ የምንቀበለው ነው ብሏል።

የአውዳል መንግስት ንቅናቄ ASM በሰሜን ምዕራብ ሶማሊላንድ የምትገኘውን አውላድ ግዛት እየመራ የሚገኝ ሲሆን፣ በቅርቡ(ከሳምንታት በፊት) ይፋ ባደረገውና ወደ ሶማሊያ/ሞቃዲሾ የመዋሃድ ውሳኔውን ለመተግበር ከራስ-ገዝ ሶማሊላንድ የተነጠለ አቋሙን እወቁልኝ ብሏል። ይህን ተከትሎም የሶማሊላንድ ጦር ከአውላድ ግዛት ለቅቆ እንዲወጣ ሆኗል። በምትኩም የአውላድ ንቅናቄ ኃይሎች የፀጥታ ኃላፊነቱን ተረክበዋል።

የ ASM ንቅናቄ ወደ ሶማሊያ በሚያደርገው ውህደት ውስጥ ከውጭ ዲያስፖራዎችም ም ሆነ ከሀገረ ሶማሊያ ዜጎችና ልሂቃን ሰፊ ድጋፍ እያገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ሂደት በተያያዘ የዘይላ ወደብን ኢትዮጵያ ትጠቀምበት ዘንድ ያቀረበው የግብዣ መግለጫው “ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተገቢውን ምክክር ያድርግ” ከሚለው በስተቀር ይህ ነው የሚባል ይፋዊ ተቃውሞ አልገጠመውም።

የአውላድ ንቅናቄ ተፈላጊነት አጥቶ በሚገኘው የዘይላ ወደብ ኢትዮጵያ ትጠቀምበት ዘንድ አመክንዮ ናቸው በማለት በይፋ የጠቀሳቸው የኢኮኖሚ፣ የታሪክና የሕዝብ ትስስር ጉዳዮች ቅቡላዊ መሆናቸው ግልፅ ቢሆንም፣ ከአዲስ አበባ ጋር እንዲፈረም ያቀረበው ምክረ ሐሳቡ፣ ከሐርጌሳ ሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና ጉጉት ጋር የሚቃረን እሳቤ ይኖረው ይሆን? የሚለውን ጊዜ የሚመልሰው ጥያቄ ነው የሚሆነው።

ኢትዮጵያ የዘይላ ወደብን ለማስመለስ በርካታ ጥረቶች ማድረጓ የሚታቅ ሲሆን በተለይም በቀዳሚ ኃይለ ስላሴ በኩል አስርት አመታትን የተሻገረው ጥረት በቅኚ ገዢዎቹ እንግሊዝ፣ ጣልያንና ፈረንሳይ የጥቅም ስሌት ሳቢያ ሳይሰምር ቀርቷል።

ሶማሊላንድ ውስጥ የእንግሊዝ ጥቅም ስር የሰደደ ሲሆን ዋሽንግተንም በተመሳሳይ ትብብር ላይ ነው የምትገኘው። እንግሊዝና አሜሪካ ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠት በተለይም ከአመት ወዲህ ሰፊ ስራ የጀመሩ ሲሆን ሀርጌሳም ይህን ለማሳካት ከመቸውም በላይ ጥረት በማድረግ ላይ ነው የምትገኘው። በአንፃሩ ከሶማሊያ ተነጥለው የቆዩ ግዛቶች (የአውላድ ግዛትን ጨምሮ) ወደ ቀድሞ ‘የግዛት አካልነታችን’ እንመለስ የሚሉ ፍላጎቶች እየበረቱ መምጣታቸው፣ በምዕራባዊያን ከሚደገፈው የሐርጌሳ መንግስት የእውቅና ፍላጎት ጋር መቃረኑ ተጠባቂ ተግዳሮት ይሆናል።

ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት ትሆን ዘንድ መሰል ቀና ፍላጎቶች መታየት መጃራቸው በራሱ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው። በተለይም ኢትዮጵያ አፍነው የቆዩ ባለ ወደብ ጎረቤቶቻችን ነባሩን ‘ወደብ ቋጣሪ’ አቋማቸውን እንደገና ይፈትሹ ዘንድ የሚያስገድድ ነው።

በየዓባይ:ልጅ


Exit mobile version