Site icon ETHIO12.COM

አዲስ አበባ – ሙስና በገሃድ፤ የትራንስፖርት ፣ የመሬት፣ የካርታ፣ የግንባታ ፍቃድ ፣ የመታወቂያ … አገልግሎቶች ምሬት

” የጸረ ሙስና ኮሚሽን ራሱ ሌላ መረማሪ ተቋም ሊበጅለት ይገባል” እስኪባል ድረስ ተቋሙ የነተበ ስለመሆኑ ያቋቋሙት አቶ መለስ በህይወት እያሉ የተሰጠ አስተያየት ነበር። ዛሬም ድረስ ያው ነው። ህዝብ በገሃድ የሚያየውን ሰላዮቹ “አልታየንም” ሲሉ የሚነከባከቡት ሌብነት ጉዳይ የብልጽግና ፈተና ሆኗል። በዚህ አያያዝ ፓርቲው ራሱን በራሱ ሊበላ እንደሚችል እየተጠቆመ ነው።

በተቁማት ውስጥ በግልጽ “አምጣ” የሚል ጥያቄ ማቅረብ የተለመደና የአገልግሎቱ አንዱ አካል እስኪመስል ድረስ የማያሸማቅቅ ተግባር የሆነው ሌብነት በዚህ ደረጃ ሲታይ ተቆጣጣሪዎቹ ዝምታ መምረጣቸው “እነሱስ” የሚያሰኝ ነው።

በግንባታ ፍጥነት ክትትል የማይታማው የአዲስ አበባ አስተዳደር “አዲስ አበባን ጽዱ አደረጋለሁ” ምን ማለቱ እንደሆነ ከአዳነች አቤቤ በስተቀር ሊገባው የሚችል አካል ስለመኖሩ አሁን አሁን ጥርጣሬ አለ። ከተማን በአሰራርና አገልግሎት አበክቶ በግንባታና በማስዋብ ትልቅ ማድረግ ምሬት እያጥወለወለው ላለ ህዝብ ምኑም ነው። ለዚህ ይመስላል የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ከረር ያለ መረጃ ይፋ ያደረገው።

በሻጥር የኑሮ ውድነት እንዲለበልበው የሚደረግ ህዝብ በሌቦች የአገልግሎት አሰጣጥ አጥንቱ እየተጋጠ እንዲኖር የሚፈርድ የከተማ አስተዳደር አንድም ሌባ፣ አለያም የሌቦች አለቃ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። በየግንባታ ቦታው ዘጭ ዘጭ በማለት በሚዲያ ጋጋታ የግል ስብዕናን መገንባት ለአዲስ አበባ ህዝብ ተረት ነው። እጅግ እበርካታ የሚያስመሰግኑ ተግባራት ቢኖሩም ሌብነት ላይ አቋም እስካልተወሰደ ድረስ ምስጋናው ሰባራ ይሆናል። ከስር እምባ ጣባቂ ኮሚሽንን ጠቅሶ ቲክቨሃ ያሰፈረው ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ፤ የትራንስፖርት ፣ የመሬት፣ የካርታ፣ የግንባታ ፍቃድ ፣ የመታወቂያ … ሌሎችም አገልግሎት ለማግኘት ሲኬድ ከእጅ መንሻ ጋር እንደሆነ መረዳቱን ገልጿል።

– በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ሙስና እንደሚፈፀም ተገልጋዮች ተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርባሉ።

– ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት የሚጠየቁት ጉቦ በድብቅ ሳይሆን በግልፅ ነው።

– ለሙስና ተጋላጭ ናቸው የተባሉ ተቋማት ተለይተዋል እየተባለ ቁጥጥሩ ለምን እንደላላ ግራ የሚያጋባ ነው።

– ” ዛሬ አገልግሎት ፈልገህ ክፍለ ከተማ ብትሄድ እኮ በግልፅ የሚጠየቅበት (ጉቦ) ሁኔታ ላይ ደርሰናል። ከዚህ በፊት እንደውም በካኪ ታሽጎ ምናምን ነው ሲሰጥ የነበረው፤ ዛሬ በካኪ ታሽጎ የሚሰጠውን ገንዘብ እዛው ፊትለፊት ላይ የሚቀዱ የመንግሥት ሰራተኞች ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው ፤ ምንም እንኳን የየስራ ባህሪያቸው ቢለይም። “

– የስርዓት ለውጥ ነው የሚያስፈልገው፤ ሙስናን መሸከም የማይችል፣ ሙስናን ማስተናገድ የማይችል ስርዓት ፣የህግና የተቋም ስርዓት ነው መዘርጋት ያለበት።

– የስነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተሰጠው ኃላፊነት ሙስናን ለመከላከል በቂ አይደለም። ይህ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለአስፈፃሚው አካል ነው፤ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መስራት የሚያስችለው አይደለም። የተቋሙ ኃላፊዎች የሚሾሙት በአስፈፃሚው አካል ነው፤ ተጠሪናታቸውም ለዛ አካል ነው እንጂ ለምክር ቤት አይደለም። ሌላው እየሰራ ያለው መከላከል ላይ ነው፤ የህግ ማስከበሩን ለፍትህ ሚኒስቴር ነው የተሰጠው አሁን ካለው ከፍተኛ የሙስና ችግር አንፃር የህግ ማስከበሩንም የመከላከሉንም ስራ መስራት የሚችል ጠንካራ ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈልጋል።

– ጠንካራ ኮሚሽን ባልተቋቋመበት ሁኔታ ኮሚቴ እያቋቋሙ ሙስናን የመከላከል የሚቻልበት ሁኔታ የለም።

የህግ ባለሙያ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ምን ይላሉ ?

– ሙሰኞች ላይ የሚወሰድ እርምጃ ጠንካራ ስላልሆነ ሙስና ከመቀነስ ይልቅ እንዲጨምር ሆኗል።

– የፖለቲካ መዋቅሩ በራሱ አጥፊዎች እንዳይጠየቁ እድል የሚሰጥ ነው። ብሄርና ትውውቅን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በአጥፊውና በጠያቂው መካከል ልዩነት እንዳይኖር ሆኗል።

– ” ሰዎች ሙስና ሰርተው ሲያጠፉ በግልፅ ማስረጃ ቀርቦባቸው ጥፋተኛ መሆን ሲገባቸው እንደውም ከለላና ሽፋን ሲያገኙ ፣ ከበላበት ቦታ ወደሌላ ቦታ ዘወር ሲል ፣ ሃብትና ንብረት እንዲያገኙ ሲመቻችላቸው ይታያል። ይሄ ሁሉ የፖለቲካ ስሪቱ ነው። የፖለቲካ ስሪቱ ብሄርን መሰረት ያደረገ መሆኑነው። ይሄ ብሄርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት የሰላ ትግል እንዳይደረግና ተጠያቂነት እንዳይመጣ ያደርጋል። “

– የስነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን መክሰስም ሆነ የመመርመር ስልጣን ቢሰጠው አሁን ካለው ስራ የተሻለ ማድረግ አይችልም። ለ16 ዓመታት ይሄ ኃላፊነት ተሰጥቶት የሰራው ስራ ታይቷል።

– አሁን የሚበጀው አጥፊዎች የሚጠየቁበትን ህግ ማጠናከር ነው።

– ” ሰው በዚህ ሰመን በካልኩሌሽን መታሰር ጀምሯል። ለምሳሌ አንድ የሙስና ወንጀል የፈፀመ ሰው 10 ሚሊዮን ብር ቢያገኝ በቀላሉ 10 ዓመት ቢታሰር / ቢወሰንበት ምን ብሎ ያስባል ‘ ይሄን 10 ሚሊዮን ብር በ10 ዓመት ላፈራው አልችልም ደግሞ ማንኛውም ታራሚ አመክሮ ስላለው በ7 ዓመት / በ6 ዓመት ብወጣ ይሄን 10 ሚሊዮን ብር መብላቱ / መመዝበሩ የተሻለ ነው ፤ ምክንያቱም በ6/7 ዓመት ውስጥ ላፈራው አልችም ‘ ብሎ ሰው በካልኩሌሽን መታሰር የጀመረበትና የደረሰበት ዘመንና ሁኔታ ላይ ደርሰናል “

– መፍትሄው ሙስና የሚፈፅሙ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ህጉን ጠንካራ ማድረግ ብቻ ነው።

በስነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን  የጥቅም ግጭት መከላከል መሪ ስራ አስፈፃሚ መስፍን በላይነህ ምን ይላሉ ?

– የሙስና ጉዳይ በጣም እየጎላ መጥቷል።

– ሁሉም ዘርፍ ከሙስና ተግባር የፀዳ አይደለም ፤ ግን ደረጃው ይለያያል።

– የእኛ ኮሚሽን ሙስናን መከላከል እንጂ ከተፈፀመ በኃላ የመመርመር፣ የመክሰስና የማገድ ኃላፊነት አልተሰጠውም። ዋናው ተልዕኮ የስነምግባር ትምህርትን ማስተማር ነው።

– በአብዛኛው ዓለም ላይ ሶስቱንም ማለትም፦

• የማስተማር፣

• የመመርመር ፣

• የመክሰስ አውድ ይዞ ነው የሚኬደው ፤ እኛ ሀገርም ተሞክሯል ከ1993 – 2008 ተሞክሯል። ከ2008 በኃላ የሙስና ወንጀል ምርመራ ብሎም ክሱ ወደሌላ አካል ተለልፋል። ቅንጅት ከተፈጠረ ይህ መሆኑ ችግር የለውም። ፖሊስ ይመረምራል፣ አቃቤ ህግ ይከሳል፣ ፍርድ ቤት ፍርድ ይሰጣል። ህብረት ያስፈልጋል። ቅንጅቱ ግን ጠንካራ አይደለም።

– ብዙ ሀገራት ላይ ይህን ዘርፍ በአንድ ተቋም ነው የሚመሩት ፤ እኛ ሀገር በተለያየ ተቋም ነው የሚሰራው ይህንን የሚመሩ አካላት እንደ አንድ ተቋም ሊሰሩ ይገባል።

@tikvahethiopia

Exit mobile version