Site icon ETHIO12.COM

የዲፕሎማሲው አባት – ከተማ ይፍሩ

የጥር ወር የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ የሚሆንበት ወር ነው። ምክንያቱም የአፍሪካ ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ የሕብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ የሚካሄድበት መሆኑ ነው። ምንም እንኳን በዚህ ዓመት የሚካሄደው በየካቲት ወር መጀመሪያ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግን የጥር ወር አጀንዳ ነው። ወዲህ ደግሞ፣ በዚህ ዓመት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የዲፕሎማሲ ዓውደ ርዕይ የሰሞኑ አጀንዳ ሆኖ ይገኛል።

የታሪክ አጋጣሚ ሆነና እነሆ በዛሬው “ሳምንቱን በታሪክ”፣ የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉትና የዲፕሎማሲ አባት በመባል የሚታወቁት ከተማ ይፍሩ የዚህ ሳምንት ክስተት ሆኑ። ከ30 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 6 ቀን 1986 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቶ ከተማ ይፍሩ የዚህ ሳምንት ክስተት ናቸውና ለአፍሪካ ሕብረት የነበራቸውን ሚና እና ሌሎች ታሪኮቻቸውን በዝርዝር እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን እናስታውስ።

ከ205 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከዘመነ መሳፍንት አላቀው ለዘመናዊት ኢትዮጵያ መመስረት ፈር ቀዳጅ የሆኑት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ (መይሳው ካሳ) ተወለዱ።

ከ80 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም በፋሺስት ኢጣሊያ የአምስት ዓመታት የወረራ ጊዜያት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር አሰቃቂ መከራ ተቀብለው የተገደሉና በየቦታው ተቀብረው የነበሩ ኢትዮጵያውያን አፅማቸው ተሰብስቦ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በክብር እንዲያርፍ ተደረገ።

ከ19 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 7 ቀን 1997 ዓ.ም በኮሜዲ ሥራዎቹና በበጎ ፈቃድ ተግባራቱ ታዋቂ የነበረው ኮሜዲያን አለባቸው ተካ (አለቤ) አረፈ።

ከ27 ዓመታት በፊት ጥር 9 ቀን 1989 ዓ.ም ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ አረፉ።

ከ83 ዓመታት በፊት ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም ወራሪውን የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ ለማስወጣት የተቀጣጠለውን የሉዓላዊነት ዘመቻ በድል ለማጠናቀቅ እንግሊዝ የቆዩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከኢትዮጵያዊያን አርበኞችና ከእንግሊዝ ወታደሮች ጋር በመሆን ከሱዳን ድንበር ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው ኦሜድላ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ።

ከ63 ዓመታት በፊት ጥር 12 ቀን 1953 ዓ.ም ጆን ፊዝጄራልድ ኬኔዲ (ጆን ኤፍ ኬኔዲ) 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈፀሙ።

በዚሁ ቀን ከ15 ዓመታት በፊት ጥር 12 ቀን 2001 ዓ.ም ባራክ ሁሴን ኦባማ የመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈፀሙ። ኦባማ 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነበሩ።

በዝርዝር ወደምናየው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራቹና የዲፕሎማሲ አባቱ አቶ ከተማ ይፍሩ ታሪክ እንለፍ።

ዛሬ ‹‹የአፍሪካ ኅብረት›› በመባል የሚታወቀው አህጉራዊ ማኅበር ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት›› በሚል ስያሜ እንዲቋቋም ትልቁን ተግባር ያከናወኑት ከተማ ይፍሩ ደጀን የሚባሉ፣ በዲፕሎማሲ ጥበብ የመጠቁ ፓን አፍሪካኒስት ኢትዮጵያዊ ናቸው።

በ1922 ዓ.ም በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሀገር፣ ጋራሙለታ አውራጃ የተወለደው ከተማ ይፍሩ የተለያዩ የትምህርት ደረጃዎችን በማለፍ፤ በ1944 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቀለ። ከተማ ስለኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች የማወቅ ፍላጎቱ ከፍ ያለ ስለነበር የጽሕፈት ሚኒስቴር ለሁለት ተከፍሎ የውጭ ጉዳዮችን የሚመለከተውን ክፍል እርሱ እንዲመራው በመንግሥት መወሰኑን ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሲነግሩት ከተማ ሚኒስቴሩ መከፈል እንደሌለበት፣ እርሱም የውጭ ጉዳዮችን የሚመለከተውን ክፍል የመምራት ፍላጎት እንደሌለውና ስለኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች የበለጠ ማወቅ እንደሚፈልግ ነገራቸው።

ከተማ የጽሕፈት ሚኒስቴር ከተራዘመ ቢሮክራሲያዊ አሠራር ነፃ እንዲሆንና ለተመረጡ እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ክፍት መሆኑ ቀርቶ ከሁሉም የመንግሥትና የኅብረተሰቡ የሥራ ዘርፎች ጋር እንዲተሳሰር ከፍተኛ ትግል አድርጓል። ንጉሠ ነገሥቱ በዚህ የከተማ ሃሳብ በመጀመሪያ ሳይስማሙ ቢቀሩም ከአጭር ጊዜ በኋላ ግን ሃሳቡን ተቀብለዋል።

ከተማ በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ምክንያት ለእስር ተዳረገ። ነገር ግን ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጋር የተገናኘ ጥፋት የለበትም ተብሎ የቅርብ ወዳጁ፣ ምስጢረኛውና መካሪው በነበሩት በመከላከያ ሚኒስትሩ ሌተናንት ጀኔራል መርዕድ መንገሻ እገዛ የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ፀሐፊና የጽሕፈት ሚኒስትር ዴኤታ ሆኖ እንዲቀጥል ተወሰነ። ከተማ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ላይ ተሳትፎ እንደነበረውና እንዳልነበረው በንጉሠ ነገሥቱ ተጠይቆ ያስረዳበት መንገድም ንጉሠ ነገሥቱ መረጃዎቻቸውን በጥንቃቄ እንዲመረምሩ ያስገደዳቸው ነበር።

ሌተናንት ጀኔራል መርዕድ መንገሻ ከተማ ሚኒስትር ሆኖ እንደተሾመ መረጃ ደርሶት እንደሆነ ሲጠይቁት ‹‹ምናልባት የትምህርት ሚኒስትር ሆኜ ተሹሜ ከሆነ ከመንግሥት ፖሊሲ አውጪዎች ጋር የሚያጋጨኝ ቦታ በመሆኑ ስልጣኔን እለቃለሁ …›› ብሎ ነገራቸው። ሌተናንት ጀኔራል መርዕድም የትምህርት ሚኒስትር ሆኖ እንዳልተሾመና እውነተኛውን ዜና ከንጉሠ ነገሥቱ እስከሚሰማ ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅ ነገሩት።

ከተማ የትምህርት ሚኒስትር ሆኖ አለመሾሙን ሲያረጋግጥ ምናልባትም ምክትል ሚኒስትር ሆኖ ወደ ቀድሞ መሥሪያ ቤቱ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር) ሊመለስ እንደሚችል ገምቶ ነበር። ሥልጣን በዘር ሐረግ በሚሰጥባት ሀገር ውስጥ ከድሃ የገበሬ ቤተሰብ የተገኘ የ32 ዓመት ሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ሊሾም ከቻለ አስገራሚ ነገር እንደሆነ አስቦ ነበር።

ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመሾም ሌተናንት ጀኔራል መርዕድ መንገሻን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ሹማምንትን ሰበሰቡ። ሹማምንቱም የየራሳቸውን ሰዎች እጩ አድርገው አቀረቡ፤ ተከራከሩ። ክርክሩን በጥሞና ያዳመጡት ንጉሠ ነገሥቱ፣ እርሳቸው ከተማ ይፍሩን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እንደመረጡ በመናገር ሹማምንቱን አስገረሙ፤ አስደነገጡ። ‹‹የባላባት ዘር ነን›› ያሉ ሹማምንት ‹‹እንዴት ከድሃ ቤተሰብ የተገኘ ሰው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ይሾማል?›› ብለው ተቃወሙ። ንጉሠ ነገሥቱ ግን ‹‹ውሳኔዬ አይቀየርም›› አሉ።

ሹመቱ በአንድ በኩል አምባሳደር ከተማ ከታላላቅ ዓለም ፖለቲከኞች ጋር እንዲተዋወቁና አብረው እንዲሰሩ እድል የከፈተላቸው ቢሆንም በሌላ በኩል ግን በርካታ ‹‹የባላባት ዘር ነን›› የሚሉ ሹማምንትና አጋሮቻቸው የከተማ ጠላቶች ሆነው እንዲነሱ በር የከፈተ አጋጣሚም ነበር። ከተማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥራቸውን የጀመሩት ኢትዮጵያ ከአፍሪካዊያን ጋር እንድትቀራረብ ለማድረግ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ነው። ስለዚህ ጉዳይ አምባሳደር ከተማ በአንድ ወቅት ሲናገሩ …

‹‹… እ.አ.አ 1961 ዓ.ም ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንደገባሁ የመጀመሪያ አጀንዳዬ አድርጌ የያዝኩት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ጋር የበለጠ የምትቀራረብበትንና የምትተባበርበትን መንገድ መፈለግ ነበር። ይህንን ጉዳይ ለጃንሆይ ነገርኳቸው። ‹… ፋሺስት ኢጣሊያ በወረረን ጊዜ ወደ ዓለም መንግሥታት ማኅበር ሄደው የጮሁት ብቻዎን ነበር። ያ ጊዜ መደገም የለበትም። ከአረቦች ጋር ልንሆን አንችልም፤ ከአውሮፓውያንም ጋር መሆን አንችልም። የእኛ ተፈጥሯዊ ምንጫችን አፍሪካ ስለሆነ ከአፍሪካውያን ጋር ነው መተባበር ያለብን። በዚህ ጉዳይ መግፋት አለብን። ይህን ጉዳይ ያምኑበታል ወይ?› ብዬ ስጠይቃቸው ‹ዋናው የእኔ ማመን አይደለም። አንተ ታምንበታለህ?› ሲሉኝ ‹እኔማ አምኘበታለሁ› አልኳቸው። ‹እንግዲያውስ ካመንክበት ቀጥልበት› አሉኝ …›› ብለዋል። እንግዲህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረትን) የመመስረት እንቅስቃሴ የተጀመረው በዚህ ወቅት ነበር።

አምባሳደር ከተማ የኢትዮጵያ ዋነኛ ወዳጆች አፍሪካውያን እንደሆኑ ጽኑ እምነት ነበራቸው። ይህን እምነታቸውን በተግባር ለመተርጎም አፍሪካዊያንን በአንድ ጥላ ስር የሚያሰባስብ ሕብረት (ድርጅት) ለማቋቋም ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ። በወቅቱ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ የአፍሪካ ሀገራት የካዛብላንካ (‹‹የአፍሪካ ሀገራት በፍጥነት ተዋህደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል››) እና የሞኖሮቪያ (‹‹አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል››) በሚባሉ ጎራዎች ተከፋፍለው ነበር። ይህ ክፍፍል የአፍሪካዊያንን ኅብረት እንደሚጎዳው የተረዱት አምባሳደር ከተማ ይፍሩ፣ ኢትዮጵያ ሁለቱን ቡድኖች የማስማማትና አፍሪካዊያንን በአንድ ኅብረት (ድርጅት) ስር የማሰባሰብ ሥራ መሥራት እንዳለባት ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አጥብቀው ተናገሩ። ንጉሠ ነገሥቱም በአቶ ከተማ ምክረ ሃሳብ ተስማምተው እንቅስቃሴዎችን ጀመሩ። አምባሳደር ከተማ ስለዚህ ጉዳይ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር። …

‹‹… እኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደነበርኩ በሁለቱም ስብሰባዎች ላይ እንድንካፈል ጥሪ ቀረበልን። የሞኖሮቪያ ቡድን ጥሪ ቀድሞ ስለደረሰን፣ የሞኖሮቪያ ቡድን አባል የነበሩት ሀገራት በቁጥር በርከት ያሉና በወቅቱ በአፍሪካ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ስለነበሩ በእርሳቸው ሰብሳቢነት ሁሉም ወገኖች ተሰብስበው ወደ አንድ ሃሳብ እንዲመጡ በማሰብ በሞኖሮቪያ ቡድን ስብሰባ ላይ ተገኘን። ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴም በስብሰባው ላይ ተገኙ። ቀጣዩ የሞኖሮቪያ ቡድን ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበን ተቀባይነትን አገኘን። የካዛብላንካ ቡድን ጥሪ ሲደርሰን ‹በዚህ ዓመት መገኘት አንችልም፤ በሚቀጥለው ዓመት ግን እንገኛለን› የሚል ምላሽ ሰጠናቸው። የካዛብላንካ ቡድን አባላት ደግሞ በዚያው ሰሞን ስብሰባ ነበራቸው። የወቅቱ የጊኒ ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኮ ቱሬ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ተደረገና መለያየት ለአፍሪካዊያን እንደማይበጅና በአንድነት መቆም እንደሚሻል ተወያየንና ‹ኢትዮጵያና ጊኒ ቀጣዩ ስብሰባ የመላው አፍሪካዊያን ስብሰባ እንዲሆን ተስማምተዋል› የሚል የጋራ መግለጫ አወጣን። በዚህ መሠረት ቡድኖቹን የማግባባት ሥራ እንድንሰራ ተስማማን። ለመሪዎቹ ሁሉ ደብዳቤ ተፃፈ። በወቅቱ የእኔ ልዩ ፀሐፊ ከነበሩት ከአቶ አያሌው ማንደፍሮ ጋር በመሆን የንጉሠ ነገሥቱን ደብዳቤዎች ይዘን በየሀገራቱ ዞርን። ‹መሪዎቹ ምላሽ ሳይሰጡን ከተሞቹን አንለቅም› ብለን ወስነን ነበር። መሪዎቹም በአጭር ቀናት ውስጥ አዎንታዊ የሆነ ምላሽ ሰጡን። በመጨረሻም በግንቦት ወር 1955 ዓ.ም ጉባዔው ተካሄደና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ካበረከተቻቸው አስተዋፅኦዎች መካከል አንዱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም ያከናወነችው ተግባር ነው። ይህንን መካድ ታሪካችንን መካድ ነው። ››

አምባሳደር ከተማ በየሀገራቱ ሲዞሩ ‹‹ምላሽ ሳትሰጡኝ ከሀገራችሁ ለቅቄ አልሄድም፤ ንጉሡም አያስገቡኝም›› የሚሉ ማባበያዎችን ይጠቀሙ ነበር። የቱኒዝያው ፕሬዚዳንቱት ‹‹የሁለቱ ቡድኖች የጋራ አቋም ሳይኖር እንዴት አንድ ላይ እንሰበሰባለን?›› የሚል የእምቢታ ምላሽ ሲሰጧቸው አምባሳደር ከተማ በምላሹ ‹‹አፄ ኃይለሥላሴ ያለ እርስዎ ይህ ስብሰባ አይካሄድም ብለዋል›› በማለት ነገሯቸው። በወቅቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የነበራቸው ተሰሚነትና ተፅዕኖ ከፍተኛ ስለነበርም የቱኒዝያው ፕሬዚዳንት በአምባሳደር ከተማ ሃሳብ ተስማምተው አዲስ አበባ ተገኙ።

ከድርጅቱ ምስረታ ቀጥሎ የአፍሪካ ፖሊሲዎችን ማርቀቅ፣ ‹‹የድርጅቱ ፀሐፊ ማን ይሁን?›› እንዲሁም፣ ‹‹ዋና ጽሕፈት ቤቱ የት ይሁን?›› የሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎች ነበሩ። በአምባሳደር ከተማ አመራርነት ፖሊሲዎቹ ተዘጋጅተው ቀረቡ፤ በፖሊሲዎቹ ላይ አንዳንድ አለመስማማቶች ቢፈጠሩም ሰነዱ ተፈረመ። ከዚህ በተጨማሪም አምባሳደር ከተማ ‹‹ኢትዮጵያ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት መቀመጫ ትሁን›› የሚል ሃሳብ አቀረቡ። ጠንካራ ተቃውሞዎች ከብዙ አቅጣጫዎች ተደመጡ። ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገራት ‹‹የሴኔጋሏ ዳካር ከተማ የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እንድትሆን ተስማምተናል›› አሉ። ናይጀሪያ በበኩሏ የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ የሀገሬ አፈር ላይ መተከል አለበት ብላ አቋም ያዘች።

ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመመስረት በብዙ ደክማ አመድ አፋሽ መሆኗ ንጉሠ ነገሥቱንና አምባሳደር ከተማን ቢያስደነግጣቸውም ‹‹ሙያ በልብ ነው›› ብለው ኢትዮጵያ እንድትመረጥ የማግባባቱን ሥራ ጀመሩ። በወቅቱ ‹‹ኢትዮጵያን እንዳትመርጡ›› የሚሉ የቴሌግራም መልዕክቶች ጭምር ይሰራጩ ነበር። በመጨረሻም ከብዙ ማግባባትና ክርክር በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እንድትሆን ሀገራቱ (ከናይጀሪያ በስተቀር) ድምፃቸውን ሰጡ። በወቅቱ በድንበር ውዝግብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር አለመግባባት ውስጥ የነበረችው ሶማሊያ እንኳ ድጋፏን ለኢትዮጵያ እንደሰጠችና የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ‹‹ኢትዮጵያን እንዳትመርጡ›› ተብለው ከሌሎች ሀገራት የተላኩትን የቴሌግራም መልዕክቶች ለአምባሳደር ከተማ ያሳዩዋቸው እንደነበር ይነገራል።

አምባሳደር ከተማ በኔልሰን ማንዴላ ታሪክ ውስጥም ዐሻራ አላቸው። የማንዴላን የኢትዮጵያ ጉዞ ያሰናዱት አቶ ከተማ ነበሩ። ኔልሰን ማንዴላም ወደ ኢትዮጵያ በሄዱበት ወቅት ንጉሠ ነገሥቱና አምባሳደር ከተማ ስላደረጉላቸው ድጋፍ ‹‹… አዲስ አበባ ስደርስ መጀመሪያ ተቀብለው ያነጋገሩኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ። ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ። ከዚያም ኮልፌ ወደሚባለው አንድ የከተማው ክፍል ወሰዱኝ …›› በማለት በመጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል። ማንዴላ ከኢትዮጵያ ተመልሰው በደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ መንግሥት ቁጥጥር ስር ሲውሉ በኪሳቸው ውስጥ የአምባሳደር ከተማ ፎቶ ተገኝቷል።

ፓን አፍሪካኒስቱ ኢትዮጵያዊ አምባሳደር ከተማ ይፍሩ በመስከረም ወር 1954 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት በአስቸኳይ እንዲወገድና ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ገዢዎች ነፃ እንዲወጡ በአፅንኦት ጠይቀዋል። አፍሪካውያን ያለ ውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ችግሮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት መብት እንዳላቸውም የድርጅቱን ቻርተር ድንጋጌዎች በመጥቀስ ተከራክረዋል።

አምባሳደር ከተማ አራተኛው የምስራቅ፣ የማዕከላዊና የደቡባዊ አፍሪካ ፓን አፍሪካ ነፃነት ጉባዔ አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ንጉሠ ነገሥቱን በማሳመን ኦሊቨር ታምቦ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ሮበርት ሙጋቤ፣ ኬኔት ካውንዳ እና ሌሎች በርካታ ስመ ጥር የአፍሪካ ነፃነት ታጋዮች አዲስ አበባ መጥተው እንዲወያዩ ማድረግ ችለዋል። አምባሳደር ከተማ ኢትዮጵያን በመወከልና የኢትዮጵያን የልዑካን ቡድን በመምራት በበርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎች ላይ ተሳትፈዋል።

አምባሳደር ከተማ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ‹‹ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረና ገለልተኛ የሆነ›› እንዲሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል። ይህ ጥረታቸውም ኢትዮጵያ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ስኬታማ የሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲኖራት እንዳስቻላት የአቶ ከተማ ልዩ ፀሐፊና የቅርብ ወዳጅ የነበሩት አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ በጻፉት ማስታወሻ ላይ ገልጸዋል።

ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከዙፋናቸው ተወግደው ዓመታት ካለፉ በኋላ አምባሳደር ከተማ ‹‹… የአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ መሪዎች ትልቁ ችግር … በእኛም ላይ ደረሰ። መሪዎች በስልጣን ላይ በሚቆዩበት ጊዜ ተተኪውን ሥርዓትና ሰው ሳያዘጋጁ ጊዜው ይደርስና ሀገራቱ ስጋት ላይ ይወድቃሉ። የዴሞክራሲን መርሆች መከተል ሲቻል፣ ስልጣን የሰፊው ሕዝብ መሆኑ ሲታወቅና ሕዝብም መብቶቹን እያወቀ ሲሄድ ነው ወደ ሌላ መንግሥት በጤና መዛወር የምንችለው…›› ብለው ተናግረዋል።

ወታደራዊው መንግሥት ስልጣን ሲይዝ አምባሳደር ከተማ ታሰሩ። ከስምንት ዓመታት እስራት በኋላ ተፈቱ። ከዚያም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር፣ የአፍሪካ ቀጠና ልዩ አማካሪና ተወካይ ሆነው አገልግለዋል። አምባሳደር ከተማ ይፍሩ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች የተመሰከረላቸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራችና የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አባት ናቸው።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Exit mobile version