Site icon ETHIO12.COM

ከ44 ባለስልጣናት አንዱ ብቻ እውነተኛ ሆነው ተገኙ – የሙስና ኮሚሽን

Legal law concept image - gavel and handcuffs

ለራሱ ሌላ “ሌብነት አጣሪ ተቋም ሊቋቋምለት ይገባል” በሚል ሲወገዝ የኖረው የፌደራሉ የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ከአርባ አንድ ሀብታቸውን ካስመዘገቡ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች መካከል ትክክል ሆኖ የተገኘው የአንድ ብቻ መሆኑንን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ስም ለምን እንደማይጠቅስ አስተያየት ቀርቦበታል።

ሃብታቸውን አስመዘገቡ የተባሉትና ስማቸው በዜናው ይፋ ያልሆኑት ባለስልጣናት የተሳሳተ መረጃ እንደሰጡ ያመለከተው ኮሚሽኑ ” አንድ ብቻ ታማኝ ያላቸው ባለስልጣን ለምን ስማቸው አልተገለጸም” ሲሉ በደፋናው በተመሳሳይ ጥያቄ ያነሱ በርካታ ናቸው።

ባለፉት ስድስት ወራት አርባ አንድ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ያስመዘገቡትን ሀብት እውነተኝነት የማረጋገጥ ስራ አከናውኖ ትክክለኛ ሆኖ ያገኘው አንድ ብቻ መሆኑን የፌደራል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ማስታወቁን ገልጾ ዜናውን ያሰራጨው የኢትዮያ ፕሬስ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ የጠቀሳቸው የአስቸኳይ ሙስና መከላከል መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ገዛኽኝ ጋሻው እንደተናገሩት የተመዘገበውን ሀብት እውነተኝነት ለማረጋገጥ መሞከሩን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም ውስጥ ሃያ አራቱ ባለስልጣናት ያስመዘገቡት ከፍተኛ ልዩነት ሲያሳይ፣ አስራ ስድስቱ መካከለኛ ልዩነት ታይቶበታል። ትክክለኛ ሆኖ የተገኘው ደግሞ አንድ ብቻ ነው።

ሃያ አራቱ በከፍተኛ ልዩነት የተፈረጁት ፍጹም እንደሸመጠጡ የሚቆጠር ሲሆን የተቀሩት አስራ ስድስቱ ” ሻል ያሉ ሸምጣጮች” እንደሆኑ በተዘዋዋሪ ያመለከተው ዜና ጉዳዩም ለፍትህ አካላት ተልኮ የማጣራት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል። ነገር ግን ከማጣራቱ በሁዋላ ምን እርምጃ እንደሚወሰድ አላብራራም።

ቀደም ሲል ከሌብነት ጋር በተያያዘ ኮሚሽኑ ከወትሮው በተለየ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ፣ “ጥርስ የሌለው አንበሳ” በሚል የሚነሳበትን ትችት እንደሚቀይር፣ ህዝብ ተባባሪ እንዲሆን አዲሱ ኮሚሽነር መጠየቃቸው አይዘነጋም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአገሪቱ የተነሰራፋውን ሌብነት መታገስ የማይቻልበት ደረጃ መደረሱን ማመልክታቸው ይታወሳል።

በቀጣይ ስድስት ወራት በተመሳሳይ በሃምሳ አምስት ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ላይ የተመዘገበውን ሀብት የማረጋገጥ ስራ እንደሚከናወን ሃላፊው መናገራቸው ታውቋል።

Exit mobile version